የናይጄሪያ ግዛት በህፃናት ደፋሪዎች ላይ የማኮላሸት ህግን ልታፀድቅ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የናይጄሪያዋ ካዱና ግዛት ከአስራ አራት አመት በታች ያሉ ህፃናትን የሚደፍሩ ግለሰቦች በህክምና እንዲኮላሹ የሚያዝ ረቂቅ ህግን አሳልፋለች።
ረቂቁ ህግ ሆኖ እንዲፀድቅ የግዛቲቷ አስተዳዳሪ ናስር አህመድ ኤል ሩፋይ መፈረም ይኖርባቸዋል።
አስተዳዳሪው ከዚህ ቀደም ደፋሪዎች ተግባራቸውን እንደገና እንዳይፈፅሙ ብልታቸው ሊኮላሽ ይገባል ሲሉም ነበር።
የናይጀሪያ ፌደራል መንግሥት ደፋሪዎችን ከአስራ አራት አመት እስከ እድሜ ልክ እስራት ቢቀጣም ግዛቶች ግን የራሳቸውን ህግ ማውጣት ይችላሉ።
የተደፈሩ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ በማህበረሰቡ ካለው ተጠቂዎችን ጥፋተኛ ከማድረግ እሳቤ አንፃር ብዙዎች ደፍረው ወደ ህግ ቦታ አይሄዱም።
ደፍረው ሪፖርት ያደረጉትም ቢሆን ክስ ተመሰርቶ የሚፈረድባቸውም ጥቂቶች ናቸው።
በሰኔ ወር ላይ በርካታ የናይጄሪያ ግዛት አስተዳዳሪዎች እየጨመረ የመጣውን የሴቶች መደፈርና ጥቃት አስመልክቶ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስተላልፈው ነበር።
በናይጄሪያ ከጎርጎሳውያኑ 2015 ጀምሮ የተፈረደባቸው 40 ደፋሪዎች ብቻ እንደሆኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
አገሪቷም ህጓን አሻሽላለች።
የመድፈር ክስን አስቸጋሪ የሚያደርገው አቃቤ ህግ ማስረጃ ማምጣት ስለሚኖርበት አድካሚና ቴክኒካል ጉዳዪ የተወሳሰበ እንደሚያደርገው ይነገራል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የተጣለው የእንቅስቃሴ መገደብም የሚደፈሩ ሴቶችን ቁጥር እንዲያሻቅብ አድርጎታል።
በሃምሌ ወር የ22 አመት እድሜ ያላት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ተደፍራ መገደሏ ከፍተኛ ቁጣን ፈጥሯል።
ይህንንም ተከትሎ ናይጄሪያውያን ንዴታቸውን ለመግለፅ ጎዳና ላይ ወጥተዋል፤ 'ዊ አር ታየርድ' (ደክሞናል) በሚልም በትዊተር ላይ ዘመቻ ተጀምሮም ነበር።
በርካቶችም የሞት ቅጣትን ጨምሮ ጠበቅ ያለ ህግ እንዲወጣም ጠይቀዋል።
"ደፋሪዎችን የመኮላሸት ቅጣት ህግ በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ያለውን መደፈርን ይቀንሰዋል ብለን እናምናለን" በማለት የካዱና ምክርቤት አባል ሼሁ ዩኑሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"የካዱና አስተዳዳሪ ከፈረሙና ህጉም ከፀደቀ በኋላ ቀጣዩ ደፋሪ የሚሰለብ ይሆናል" ብለዋል።
የስርዓተ-ፆታ መብት ተሟጋችና የመደፈር ጥቃት የደረሰባቸው ዶሮቲ ንጄዝማንዜም ህጉ እንዳስደሰታቸው ገልፀው በሌሎች ግዛቶችም ተግባራዊ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
"በዚያን ወቅት የደፈሩኝ ቢኮላሹ ኖሮ ሌሎች ደፋሪዎች አይፈጠሩም ነበር፤ ብዙዎችም ከዚህ ጥቃት ይተርፉ ነበር" ብለዋል።
በህክምና የመስለብ ቅጣት በአንዳንድ አገራት ተግባራዊ ቢሆንም አወዛጋቢ ነው።












