ኒው ዚላንድ፡ መስጂድ ውስጥ 51 ሰዎችን የገደለው ግለሰብ እድሜ ይፍታህ ተፈረደበት

በኒው ዚላንድ ሁለት መስጂዶች 51 ሰዎች የገደለው አውስራሊያዊው ብሬኖን ታራንት የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት። ግለሰቡ መቼም ቢሆን በይቅርታ አይፈታም ተብሏል።
በኒው ዚላንድ መሰል ቅጣት የተላለፈበት የመጀመሪያው ሰው ነው።
የ29 ዓመቱ ብሬኖን በሽብር ወንጀል ከተከሰሰ በኋላ 51 ሰዎችን መግደሉንና ሌሎች 40 ሰዎችን ለመግደል መሞከሩን አምኗል።
ዳኛው ድርጊቱ “ኢ ሰብዓዊ ነው። ምንም ርህራሔ አላሳየም” ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ ጥቃቱ ሲሰነዘር መላው ዓለምን አስደንገጦ እንደነበር ይታወሳል።
“ወንጀልህ እጅግ የከፋ ከመሆኑ የተነሳ እስክትሞት ድረስ ከማረሚያ ቤት አትወጣም” ሲሉ ዳኛ ካሜሮን ማንደር ተናግረዋል።
በምንም አይነት ሁኔታ በይቅርታ እንዳይለቀቅ መወሰኑን አስመልክተው “ይህ የሚፈረደው በከፉ ገዳዮች ላይ ብቻ ነው” ብለዋል።
በኒው ዚላንድ የፍትሕ ሥርዓት የሞት ፍርድ የለም።
የኒው ዚላንድ ጠቅላይ ሚንስትር ጃሲንዳ አርደን “ከዚህ በኋላ ስለእሱ አናስብም፣ አንሰማምም” ብለዋል።
ግለሰቡ መስጂድ ውስጥ ሰዎችን ከገደለ በኋላ በአገሪቱ ጥብቅ የመሣሪያ ሕግ ወጥቷል።
ፍርዱ ከመተላለፉ በፊት ግለሰቡ የገደላቸውን ሰዎች ባጠቃላይ ዳኛው ሲያስታውሱት ነበር።
“ግለሰቡ ሀፍረት አልተሰማውም” ሲሉም ዳኛው ተናግረዋል።
ግለሰቡ በጠበቃው በኩል ፍርዱን እንደማይቃወም ገልጿል።
በፍርድ ሂደቱ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ቀናት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ምስክርነት እንዲሰጡ ነበር የተደረገው።
ወደ 90 የሚሆኑ ሰዎች እያለቀሱ ሲወቅሱት፤ የ29 ዓመቱ ብሬኖን ምንም ስሜት አልታየበትም።
አብደልፈታህ ቃሲም የተባለ አባቷን በጥቃቱ ያጣችው ሳራ ቃሲም “ፈርቶ ይሆን? የመጨረሻ ሐሳቡ ምንድን ነው? እንደው እጁን ጨብጬ ምንም አትሆንም ብለው ተመኝቼ ነበር” ብላለች።
ግለሰቡ ባለፈው ዓመት በሁለት መስጂዶች ውስጥ ተኩስ ከፍቶ ነበር። መጀመሪያ ላይ አል ኑር የተባለው መስጂድ ውስጥ ተኩሶ፣ ከሠላሳ ሰከንዶች በኋላ ከመኪናው ሌላ መሣሪያ አውጥቶ በድጋሚ መተኮስ ጀምሯል።
ጥቃቱ በፌስቡክ በቀጥታ እየታየ ነበር።
ከዚያም ሊን ውድ የተባለ መስጂድ ውስጥ ጥቃት አድርሷል። አንድ አማኝ ከተኳሹ መሣሪያ አንዱን ወስዶ ካባረረው በኋላ ሁለት ፖሊሶች በቁጥጥር ስር አውለውታል።
ከታሰረ በኋላ አላማው መስጂዶቹን ማቃጠል እንደነበር ተናግሯል።
ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ባያውሉት ኖሮ ሌላ መስጂድ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር አቅዶ ነበር።
በነጭ የበላይነት የሚያምነውን ግለሰብ የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚንስትር ስኮት ሞሪሰን፤ “አክራሪ፣ ቀኝ ዘመም አሸባሪ” ሲሉ ገልጸውታል።
ተከሳሹ የተወለደው አውስትራሊያ ውስጥ ሲሆን፤ አባቱ ቆሻሻ በመሰብሰብ እናቱ ደግሞ በማስተማር ይተዳደራሉ።
አባቱ ከሞቱ በኋላ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ተዘዋውሯል። አያቱ እንደሚሉት፤ እነዚህ ጉዞዎች ናቸው የቀየሩት።
“የምናውቀው ሰው አልነበረም” ብለዋል።














