የራፐር ቢአይጂ ዘውድና የቱፓክ የፍቅር ደብዳቤዎች ለጨረታ ሊቀርቡ ነው

ራፐር ቢጂአይ

የፎቶው ባለመብት, SOTHEBY'S

ታትሟል

የኖቶሪየስ ቢአይጂ (ቢጊ) ዘውድ እንዲሁም የቱፓክ ሻኩር የፍቅር ደብዳቤዎች ለጨረታ ሊቀርቡ ነው።

ጨረታው መስከረም 15 ኒው ዮርክ ውስጥ የሚካሄድ ሲሆን፤ ከሚገኘው ገንዘብ የተወሰነው በኒው ዮርክ ለሚገኝ የማኅበረሰብ ፕሮጀክት ይውላል ተብሏል።

ቢጊ ዘውዱን አድርጎ ፎቶ የተነሳው ከመገደሉ (እአአ መጋቢት 9፣ 1997) ሦስት ቀን ቀደም ብሎ ነው። ፎቶግራፉን ያነሳው ደግሞ ባሮን ክሌይቦርን የሚባል ባለሙያ ነው።

በወቅቱ ራፐሩና ፎቶግራፉን ያነሳው ግለሰብ ዘውዱ ላይ ፈርመውበታል። ፎቶግራፈሩ ባሮን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ዘውዱን እንደ ማስታወሻ ጠብቆ አቆይቶታል።

ዘውዱ ከ200 000 እስከ 300 ሺህ ዶላር ድረስ ሊሸጥ እንደሚችል ተገምቷል።

ቢጊ ፎቶውን በተነሳበት ወቅት አብሮት የነበረው የሙዚቃዎቹ አሳታሚ ኃላፊ ፎቶው ከሂፕ ሆፕ ንጉሥ ይልቅ የበርገር ኪንግ ማስታወቂያ መሰለ በሚል ስጋት ገብቶት ነበር።

ነገር ግን ፎቶው የቢጊን ምስል ከፍ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ እንደነበር ፎቶግራፈሩ ተናግሯል።

“የኒው ዮርክ ከተማ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን የሂፕ ሆፕ ሙዚቃም ንጉሥ” በማለት የፈጠረውን ተጽዕኖ ይገልጸዋል።

ሌላው ለጨረታ የቀረቡት ቱፓክ በአስራ ስድስት ዓመቱ በፍቅር ለከነፈላትና አብራው ትማር ለነበረችው ካቲ ሎይ የጻፋቸው 22 የፍቅር ደብዳቤዎች ናቸው።

ቱፓክ በደብዳቤቹ እናቱ ለረዥም ሰዓታት እንደሚሰሩና የአክስቶቹን ልጆች በመንከባከብ አንደሚያግዛቸው ጽፏል።

በዓለም ድንቅ ከሚባሉ ራፐሮች አንዱ የሆነው ቱፓክ፤ በወቅቱ ሙዚቃን ስለመተው ያስብ እንደነበርም ከደብዳቤዎቹ በአንዱ ገልጿል።

“የድሮ ኃላፊዬ ራፕ እንድተው እንደማትፈልግ ነግራኛለች። ግን የማቆም መሰለኝ። ምክንያቱም ተቀባይነት አለማግኘትን አልችለውም። ጊዜም የለኝም. . .”

ቱፓክ ደብዳቤዎቹን የጻፋቸው ለሁለት ወራት በዘለቀ የፍቅር ግንኙነታቸው ነው። በደብዳቤዎቹ ፊርማውንም አኑሯል።

እነዚህ ደብዳቤዎች ከ60 ሺህ እስከ 80 ሺህ ዶለር ድረስ ተተምነዋል።

ቱፓክ በ25 ዓመቱ፤ በ1996 መስከረም ወር ላይ ላስ ቬጋስ ውስጥ በተተኮሰበት ጥይት መሞቱ ይታወሳል።