የቀድሞው የቦሊቪያ ፕሬዝደንት በመድፈር ክስ ተመሰረተባቸው

የቦሊቨዒያ ቀድሞ ፕሬዝደንት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የቦሊቪያ ፍትህ ሚኒስቴር በስደት ላይ በሚገኙት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኢቮ ሞራሌዝ ላይ በመድፈርና በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ክስ መሰረተ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ክሱን የመሰረተው አንድ የአገሪቱ ብሄራዊ መገናኛ ብዙሃን የ60 ዓመቱ የቀድሞ መሪ ከአንዲት ታዳጊ ጋር ሆነው የሚያሳይ ምስል ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ነው።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ የሰጡት አስተያየት የለም።

ኢቮ ሞራሌዝ ከአውሮፓውያኑ 2006 እስከ 2019 ድረስ ቦሊቪያን በፕሬዝዳንትነት የመሩ ሲሆን ባሳለፍነው ዓመት ሕዳር ወር ላይ ከምርጫ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ አለመግባባት ወደ አርጀንቲና መሰደዳቸው የሚታወስ ነው።

ግራ ዘመሙ መሪ የባለፈውን ዓመት ምርጫ ተከትሎ በደረሰባቸው ከባድ የህዝብ ተቃውሞና ጫና ተከትሎ ነው ስልጣናቸውን ለቅቀው ቀኝ ዘመሙ መሪ ስልጣኑን የተረከቡት።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት በስደት ላይ እያሉ በርካታ ክሶች ሲቀርቡባቸው ነበር።

አሁን በቀረበባቸው ክስ ላይ ኢቮ ሞራሌዝ በምጽሀረ ቃል 'ኤን ኤም' በሚል ስያሜ ብቻ ከቀረበቸውና በአሁኑ ሰአት የ19 ዓመት ወጣት ጾታዊ ግንኙነት ነበራቸው በሚል ነው።

በቦሊቪያ ፍትህ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር የሆኑት ጉዊዶ ማላር ሐሙስ ዕለት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ የቀድሞው ፕሬዝዳንትና ታዳጊዋን የሚያሳየው ምስል በሞባይል ስልክ የተነሳ እንደሆነና ፎቶውን ያነሳውም ግለሰብ የታዳጊዋ ዘመድ እንደሆነ ገልጸዋል።

ታዳጊዋ በወቅቱ 14 ዓመት የነበረች ሲሆን ፕሬዝዳንቱ ወደተለያዩ ቦታዎች ጉዞ በሚያድርጉበት ወቅት አብራቸው ትጓዝ እንደነበረ የስፔኑ የዜና ወኪል 'ኢኤፍኢ' ዘግቧል።

የታዳጊዋ ቤተሰቦች በጉዳዩ ላይ ስላላቸው ተሳትፎና ታዳጊዋ እንዴት ያለእነሱ ይሁንታ ወደተለያዩ አገራት መጓዝ እንደቻለች በተመለከተ ደግሞ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ምክትል ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

አክለውም መንግስት ታዳጊዋ በአሁኑ ሰአት የት እንደምትገኝ እንደማያውቅና ቤተሰቦቿ ግን የቀድሞው ፕሬዝዳንት የሚኖሩበት አርጀንቲና ውስጥ ለጉብኝት መሄዳቸውን የሚያመለክት መረጃ እንዳላቸው አስታውቀዋል።

በቦሊቪያ ሕግ መሰረት የመድፈር ወንጀል ከሁለት እስከ ስድስት ዓመት በሚደርስ እስር የሚያስቀጣ ሲሆን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ደግሞ 15 ዓመት ድረስ ያስቀጣል።

ሞራሌዝ ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ የጸጥታ ኃይሎች ደጋፊዎቻቸው ላይ "የዘር ጭፍጨፋ" እያደረጉ እንደሆነ ተናግረው የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እርዳታ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው።

የወቅቱ የቦሊቪያ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ጀኒኔ አኔዝ የቀድሞው ምርጫ ውጤጥ ተሰርዞ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ አገራዊ መግባባት ይፈጥራል ብለው ነበር።

በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2006 ላይ መንበረ ሥልጣን የጨበጡት የቀድሞው አርሶ አደር ሞራሌስ፤ የቦሊቪያን ምጣኔ ኃብት በማበልጸግ ቢመሰገኑም፤ ከሕግ ውጪ የሥልጣን ዘመናቸውን በማራዘማቸው ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር።

በተካሄደው ምርጫ ሞራሌስ በጠባብ የድምጽ ልዩነት አሸንፈዋል ቢባልም፤ ታዛቢው 'ኦርጋናይዜሽን ኦፍ አሜሪካን ስቴትስ' ምርጫው መጭበርበሩን ይፋ አድርጓል።

ሞራሌስ ሌላ ምርጫ ለማካሄድ ቢስማሙም በምርጫው ሁለተኛ ደረጃ ያገኙት ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ካርሊስ ሜሳ፤ ሞራሌስ ሥልጣናቸውን ይልቀቁ የሚል አቋም አንጸባርቀዋል። ይህንን ተከትሎ በተነሳ አለመረጋጋር ሳቢያ ሞራሌስ ሥልጣን ለቀው መሸሻቸው ይታወሳል።