ታዋቂው አሜሪካዊ የፊልም ተዋናይ ኪውባ ጉዲንግ የመድፈር ውንጀላ ቀረበበት

ኪውባ ጉዲንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

አንዲት ሴት ታዋቂው አሜሪካዊ የፊልም ተዋናይ ኪውባ ጉዲንግ ጁንየር ሁለት ጊዜ እንደደፈራት አስታውቃለች።

ከሰሞኑ ማክሰኞ እለትም ክሷን እንዳስገባች ታውቋል።

የኦስካር ተሸላሚው ተዋናይ ጥቃቱን ያደረሰባት በጎርጎሳውያኑ 2013 ኒውዮርክ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ መሆኑንም ስሟ ያልተገለፀው ግለሰብ አስረድታለች።

የተዋናዩ ጠበቃ ማርክ ጄይለር በበኩላቸው ውንጀላው በፍፁም ሃሰት ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

ኪውባ ከዚህ ቀደምም ጉንተላ አድርሶብናል የሚሉ በርካታ ሴቶች ቢቀርቡም በመድፈር ሲወነጀል የመጀመሪያው ነው።

ስሟ ያልተጠቀሰው ግለሰብ ከተዋናዩ ጋር የመጀመሪያ ትውውቃቸው በጎርሳውያኑ 2013 ማንሃተን መጠጥ ቤት መሆኑም ተገልጿል።

በመቀጠልመም ኪውባ አቅራቢያው የሚገኝ ሆቴል ውስጥ አብራው እንድትጠጣው እንደጋበዛት ተናግራለች።

ሆቴሉም ከደረሱ በኋላ ልብሱን ሊቀይር እንደሚፈልግና አብራውም ክፍሉ እንድትመጣ ጠየቃት።

ግለሰቧም ተከትላው ክፍሉ ከገባች በኋላ እንደደፈራት አስረድታለች። "ፍትህን እሻለሁ ያለችው" ግለሰብ ለደረሰባት ጉዳትም ካሳ እንዲከፈላት እንደምትሻም ተነግሯል።

ማርክ ጄይለር በበኩላቸው ክሱን "ፍፁም ሃሰትና የደንበኛዬን ስም የሚያጠለሽ ነው" ማለታቸውን ኒውዮርክ ታይምስ አስነብቧል።

በባለፉት ሰባት አመታትም ተመሳሳይ ውንጀላዎች እንደቀረቡ የተናገሩት የህግ ባለሙያው ሁሉም ክስ ላይ ሳይደርሱ ቀርተዋል ብለዋል።

በኒውዮርክ በሚገኝ የምሽት ክበብ ውስጥ ጉንተላ አድርሶብናል ያሉ ሶስት ሴቶች ባለፈው አመት ከሰውት የነበረ ሲሆን ተዋናዩም ጥፋተኛ አይደለሁም ብሏል።

ክሱም መቋጫ ያላገኘ ሲሆን በዚህ አመትም ሚያዝያ ላይ መካሄድ ቢኖርበትም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሟል።

ኪውባ ጉዲንግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ኪውባ በኒውዮርክ የፍርድ ቤቱ ሂደት ከመጀመሩ በፊት የብላክ ላይቭስ ማተር ጭምብልም አጥልቆ ታይቷል።

የ52 አመቱ ተዋናይ ጄሪ ማጉየር በተሰኘው ፊልሙ በጎርጎሳውያኑ 1997 በረዳት ተዋናይ ዘርፍ የኦስካር ሽልማትን ወስዷል።

ከዚህም በተጨማሪ 'ኤ ፊው ጉድ ሜን'ና ዘ በትለር በሚሉት ፊልሞቹም ከፍተኛ ዝናን ተጎናፅፏል።

በጎርጎሳውያኑ 2016 "ፒፐል ቨርሰስ ኦጄ ሲምሰን" በሚለው ተከታታይ ፊልም ለኤሚ ሽልማት ታጭቶ ነበር።

ከሁለት አመታት በኋላም በ"ቢሊ ፊሊ"ን ላይ ተውኗል።