ሶማሊያ፡ ከእሑዱ የአልሸባብ አጋች ታጋች ድራማ እንዴት አመለጥኩ?

መሃመድ ሞአሊሙ

የፎቶው ባለመብት, MOHAMED MOALIMU

ታትሟል

የቀድሞው ባልደረባችን የቢቢሲው መሐመድ ሙአሊሙ ሕይወቱ ተርፋለች፡፡

እሁድ ዕለት አልሸባብ ሞቃዲሾ ባህር ዳርቻ በሚኘው ኢላይት ሆቴል በር ላይ ያጠመደው ቦምብ አፈነዳ፡፡ ከዚያ ግርግሩን ተገን አድርጎ ሆቴሉ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ጥበቃ በመጣስ፣ ወደ ውስጥ በመዝለቅ እዚያ የሚገኙ ተስተናጋጆችን በቁጥጥር ሥር አውሏቸው ነበር፡፡

የመሐመድ ሙአሊሙ ነፍስ ግን ትረፊ ከተባሉት ውስጥ ናት፡፡ እንደ ሁልጊዜው፡፡

ባለፉት ሰባት ዓመታት ብቻ አራት አደገኛ የአልሸባብ ጥቃቶች ስለማምለጡ ይናገራል፡፡

ሙአሊሙ አሁን ለቢቢሲ አይሰራም፡፡ የሶማሊያ ጋዜጠኞች ፌዴሬሽን ሊቀ መንበር ነው፡፡

ለቀድሞ ባልደረባው ለቢቢሲው ባሳሊዮ ሙታሂ ከእሑዱ አደጋ እንዴት በተአምር እንደተረፈ እንዲህ አጫውቶታል፡፡

20 ጓደኞቼ ሞቱ- እኔ ተረፍኩ

እየተንቀጠቀጥኩ ነበር፡፡ ልቤ ልክ እንደ ከበሮ ይመታል፡፡ እግሬን ብርክ ያዘው፡፡ ድንገት ከባድ ቦምብ አጠገባችን ከፈነዳ በኋላ ነው እንዲያ የተሰማኝ፡፡

ሰዎች ይጮኻሉ፤ የተወሰኑ ሰዎች ቦምቡ አቁስሏቸዋል፤ የተወሰኑት ማየት አይችሉም፡፡ የተወሰኑት በስቃይ ያጓራሉ፡፡ አንዱ ሌላውን ለማየት ጭሱ ይጋርዳል፡፡

ጓደኛዬ አብዱልረዛቅ አብዲ ቶሎ ሮጦ ለማምለጥ ፈለገ፡፡ እኔ ደግሞ ላስቆመው ሞከርኩ፤ ምክንያቱም ከባድ የተኩስ ልውውጥ ይሰማ ነበር ከደጅ፡፡ አልሰማኝም፡፡ ዘሎ ከእጄ አመለጠና ወደ ዋናው በር ሮጠ፡፡

እኔ መውጣት ፈራሁ፡፡ ቢያንስ ተኩሱ በየትኛው አቅጣጫ እንዳለ ማጤን ፈለኩ፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ከዚህ በፊት ስልጠና ወስጄ አውቃለሁ፡፡

በዚያ ሁኔታ ውስጥ አጥርቶ ማሰብ ቢከብድም እኔ ግን ቢያንስ ተረጋግቼ ራሴን ለመቆጣጠርና ቀልቤን ለመግዛት ችዬ ነበር፡፡ ያ በመሆኑም ነው ምን እየተከናወነ መሆኑን ለመረዳት የቻልኩት፡፡ ያ በመሆኑም ነው ነፍሴ ልትተርፍ የቻለችው፡፡

አሁን በየት በኩል ማምለጥ እንደምችል ገብቶኛል፡፡ እንዴት መሽሎክ እንዳለብኝ ተረድቻለሁ፡፡

ተኩሱ ትንሽ ረገብ ሲልልኝ ሹልክ ብዬ ወደ ፎቅ ወጣሁና በዚግዛግ ሩጫ አመለጥኩ፡፡ የሆቴሉን አጥር ላይ ተንጠላጠልኩና ሆቴሉ ከባሕር ዳርቻ በሚጎራበትበት በኩል ዘለልኩ፡፡

ቲሸርቴን ለምን አወለቅኩ?

በአጥሩ ዘልዬ ወደ ደጅ ከወጣሁ በኋላ መሮጥ አልቻልኩም፡፡ ምክንያቱም ለማምለጥ እየሞከሩ ያሉ ሰዎች እየተተኮሰባቸው ሲወድቁ ተመክቻለሁ፡፡

ምን ማድረግ እንዳለብኝ አሰብኩ፡፡ ቢያንስ ደመቅ ያለ ቀለም ለትኩረት እንደሚዳርገኝ ገባኝ፡፡ ተኳሹ ኢላማ ውስጥ ባንዲራ እያውለበለቡ መሮጥ ነው የሚሆነው፡፡

ስለዚህ ቲሸርቴን አወለቅኩት፡፡ አረንጓዴ ደማቅ ቲሸርት ነበር የለበስኩት፡፡ ጫማዬን አሽቀንጥሬ ጣልኩና በባዶ እግሬ ዚግዛግ እየመታሁ እግሬ አውጪኝ አልኩ፡፡

ተኩሱ ያለማቋረጥ እየተንጣጣ በሆነ ተአምር መትረፍ ቻልኩ፡፡

ወዲያውኑ ማምለጤን ሳውቅ ያደረኩት ጓደኛዬ ዘንድ መደወል ነበር፡፡ ስልኩ አይሰራም፡፡

ነገሩ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ ወዳጄን ፍለጋ ሄድኩ፡፡ ሞቶም ከሆነ ልወቅ ብዬ ፈለኩት፡፡

የሰዎች ሬሳ በደጁም ውስጥም ወድቋል፡፡ አካባቢው ተተረማምሷል፡፡

የተኩስ ልውውጡ ባያበቃም አምቡላንስ በአካባቢው ደርሷል፡፡ አንድ የጋራ ጓደኛችን አብዱረዛቅ ቆስሎ ሆስፒታል መወሰዱን ነገሩኝ፡፡

ጥይቱ የመታው ከአሸባሪዎች መሀል ዝም ብሎ አንደመጣለት ጥይት ሲያርከፈክፍ በነበረው የአልሸባብ አባል ነበር፡፡ እግሩና ደረቱ ላይ ጥይት አግኝቶታል፡፡

ሆስፒታል እየከነፍኩ ደረስኩ።

እስከዚህ ሰዓት ድረስ ተኩስ አልበረደም፡፡ እዚያም እዚህም ሰዎች ይጮኻሉ፡፡ የተሸከርካሪ እንቅስቃሴ ተገድቦ ስለነበር መንገዱ ክፍት ነበር፡፡

ጓደኛዬ አብዱረዛቅ በማስታወቂያ ሚኒስትር ነበር የሚሰራው፡፡ ከቤት ወደ ሆቴሉ ይዞኝ የሄደው እሱ ነበር፡፡ ይተርፍ ይሆን? ተጨንቂያሁ፡፡

መኪና ስላልነበረ በሩጫ ወደ ሆስፒታሉ ፈጠንኩ፡፡

ዕድለኛ አልነበርኩም፡ ዕድለኛ አልነበረም፡፡ ጓደኛዬ አብዱረዛቅ ሕይወቱ እስከ ወዲያኛው አልፎ ነበር የደረስኩት፡፡

አስቀያሚ ቀን ነበር፡፡ ለኔ ከእንደዚህ አይነት መከራ ሳመልጥ አራተኛዬ ነበር፡፡ ካለምንም መቁሰል ሳመልጥ ደግሞ የመጀመርያዬ ነው፡፡

በ2013 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግቢ እያለሁ አጥፍቶ ጠፊ መኪናዬን አፈነዳት፡፡ እኔም ለጥቂት ተረፍኩ፡፡

በ2016 ሊዶ ባሕር ዳርቻ ሆቴል ውስጥ ሳለሁ አልሸባብ ጥቃት አደረሰና ፊቴ ክፉኛ ቆሰለ፡፡ ያን ጊዜ ፊቴ ለሰዓታት በደም ተነክሮ ነበር የቆየው፡፡ ሰዎች አውጥተው ሆስፒታል አደረሱኛና ነፍሴ ተረፈች፡፡

መዳን የቻልኩት ግን ናይሮቢና ሎንዶን ለረዥም ወራት ሕክምና መከታተል በመቻሌ ነበር፡፡

ባለፈው ዓመት የካቲት ላይ ደግሞ መካ አልሙከራማ ሆቴል ላይ ጥቃት ሲደርስ ቆሰልኩ፡፡ ያመለጥኩት አጥፍቶ ጠፊው በቆፈረው አንድ ትቦ ተሸሎክልኬ ነው፡፡

ስለነገ ምን አውቃለሁ? ምንም፡፡