ቻይና፡ ክብደታችሁን እየተመዘናችሁ በመጠናችሁ እዘዙ ያለው ሬስቶራንት ይቅርታ ጠየቀ

ታትሟል

በማዕከላዊ ቻይና የሚገኝ አንድ ምግብ ቤት ደንበኞቹ ክብደታቸውን መዝነው በመጠናቸው እንዲያዙ ጠይቋል። ይህንንመ አስመልክቶ ተገቢ እንዳልሆነ ተረድቻለሁ በማለት ይቅርታ ጠይቋል።

ቻይና የምግብ ብክነትን ለመቀነስ አገራዊ ዘመቻን የጀመረች ሲሆን የሬስቶራንቱ ፖሊሲም ከዚያ ጋር ተያይዞ ነው ተብሏል።

የበሬ ስጋ በማቅረብ የሚታወቀው ይህ ምግብ ቤት በመግቢያው በር ላይም ደንበኞች ተመዝነው እንዲገቡ በሚል ሁለት ትልልቅ ሚዛኖችም ተቀምጠው ነው።

የሬስቶራንቱ ተጠቃሚዎች ሲገቡም ኪሏቸውን በክብደት መተግበሪያው (አፕሊኬሽን) እንዲያሰፍሩ ይደረጋል። መተግበሪያውም የደንበኞችን ክብደት በማጤን ምን ምግብ ማዘዝ እንዳለባቸው አስተያየት ይለግሳል።

በሬስቶራንቱ ውስጥም ምግባቸውን ጥርግ አርገው እንዲበሉ፣ 'ባዶ ሰሃን አስቀሩ' የሚሉ መልእክቶችም ተለጥፈው ነበር።

ይህ ሁኔታ በርካታ ቻይናውያንን አላስደሰተም፤ ቁጣቸውንም ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ወስደውታል።

ሬስቶራንቱም ጋር ተያይዞ ፖስት የተደረጉ ሃሽታጎች በዌይቦ ማህበራዊ ሚዲያ 300 ሚሊዮኖች ተጋርተውታል።

ትችቶችንም ተከትሎ ሬስቶራንቱ አገሪቱ የምግብ ብክነትን ለመቀነስ "ሰሃን ባዶ እናስቀር" የሚለው ዘመቻ በዚህ መንገድ መተርጎሙ እንዳሳዘነው ገልጿል።

"የመጀመሪያ አላማችን የነበረው የምግብን ብክነት ማስቆምና ደንበኞቻችን በጤነኛ መንገድ ምግብ እንዲያዙ ለማድረግ ነው። ደንበኞቻችን እንዲመዘኑ አላስገደድንም" በማለት ሬስቶራንቱ በበይነ መረብ ላይ ባወጣው ይቅርታ አስፍሯል።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ በዚህ ሳምንት በአገሪቱ እየተከሰተ ያለው የምግብ ብክነት "አስደንጋጭና አሳሳቢ" ነው በማለት ዘመቻውን ይፋ አድርገዋል።

የፕሬዚዳንቱንም መልዕክት ተከትሎ የውሃን የምግብ አቅራቢ ኢንዱስትሪ ማህበር ምግብ ቤቶች ደንበኞቻቸው የሚያዙትን የምግብ መጠን እንዲገድቡ ትዕዛዝ አስተላልፏል። በቡድን የሚመጡ ደንበኞች ከቁጥራቸው በአንድ ያነሰ ምግብ እንዲያዙም ፖሊሲዎችን አስተዋውቋል።

የቻይናው የዜና ወኪል ሲሲቲቪ በበኩሉ በቀጥታ ስርጭት በአንድ ጊዜ ብዙ ምግብ በአፍ የመጉረስ ትእይንት የሚያሳዩ ግለሰቦችም ለዚህ ብክነት አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሆነ ገልጿል።

''ሙክባንግ' በመባል የሚታወቁት እነዚህ የቀጥታ ስርጭቶች በብዙ የቻይና አካባቢዎችና እስያ አገራት ተወዳጅ ናቸው።

ቻይና ይህን መሰል የምግብ ብክነትን የመከላከል እንቅስቃሴ ስትጀምር ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም። በጎርጎሳውያኑ 2013 እጅግ የተጋነኑ የምግብ ድግሶችን እና የባለስልጣናት ግብዣዎችን ለማስቀረት ስራዎችን አከናውና ነበር።

አንድ ቻይና ውስጥ የሚንቀሳቀስና አካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰራ ድርጅት እንዳስታወቀው በጎርጎሳውያኑ 2015 በአገሪቱ ከ17 እስከ 18 ሚሊዮን ቶን ምግብ ተርፎ ተደፍቷል።