ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሶማሊያ፡ የህፃናትንና አስገዳጅ ጋብቻን የሚፈቅድ ነው በሚል አንድ ረቂቅ ህግ እያወዛገበ ነው
በቅርቡ በሶማሊያ በጋብቻ ላይ አንድ ረቂቅ ህግ መቅረቡን ተከትሎ አወዛጋቢ ሆኗል።
ሶማሊያውያን ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ረቂቅ ህጉ የህፃናትንና አስገዳጅ ጋብቻን የሚፈቅድ በመሆኑ ፓርላማው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ውድቅ ሊያደርገው ይገባል እያሉ ነው።
በፓርላማው ላይ ጫና ለመፍጠር ፊርማም እያሰባሰቡ ነው። እስካሁን ድረስ 6 ሺህ ያህል ሰዎች ረቂቁን በመቃወም ፈርመዋል።
የቀረበው ረቂቅ ህግ የአገሪቱን ህገ መንግሥት እንዲሁም አለም አቀፍ ስምምነቶችን የሚጥስ ነው እያሉ ነው።
"የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት የሰብዓዊ መብትን እንዲሁም የህፃናትን መብት በሚጥስ የግንኙነት ረቂቅ ላይ ድምፅ ለመስጠት በዝግጅት ላይ ነው። ይህ ረቂቅ በሶማሊያ የሚገኙ ሴቶችና ህፃናት በሰውነታቸው ላይ እንዳያዙ የሚፈቅድ ነው" ይላል የተቃውሞው ፊርማ ላይ የሰፈረው ፅሁፍ።
በሶማሊያ የዩኬ አምባሳደር ቤን ፌንደር ረቂቁን በጥልቀት እንደተመለከቱት ገልፀው "ይህ ረቂቅ ህፃናት ዕድሜያቸው ሳይደርስ ጋብቻን የሚፈቅድ ነው" በለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አስገዳጅ ጋብቻ ተብሎ የቀረበው ትርጉም የተጋቢዎች ቤተሰብ ፈቃድ ካልተገኘ ነው የሚል ነው። በዚህ ላይ የተጋቢዋ ፈቃድ መገኘት የለበትም የሚል ትርጓሜም ሰጥቷል" በማለት በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ረቂቁን ከፍተኛ ችግር ያለበት በሚል ተችቶታል።
ረቂቁ አዲስ ሳይሆን ለሁለት አመታት ያህል ሲንከባለል የነበረ ነው ተብሏል።
በሶማሊያ ወሲባዊ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ ቢጨምሩም በሰፈነው ባህላዊ ነውርነት ምክንያት ተጠቂዎች ሪፖርት ከማድረግ ወደ ኋላ እንደሚሉ ሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች ይናገራሉ።