ቻይና በአደንዛዥ እፅ ማምረት ክስ በካናዳዊው ላይ የሞት ፍርድ አስተላለፈች

ኬታማይን

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library

የምስሉ መግለጫ, ኬታማይን የተባለው እፅ ለተዝናኖት በመዋል ይታወቃል
ታትሟል

የቻይና ፍርድ ቤት 'ኬታማይን' የተባለ አደንዛዥ እፅ በማምረት ክስ በአንድ ካናዳዊ ላይ የሞት ፍርድ አስተላለፈ።

ኬታሜን የተባለው ይህ አደንዛዥ እፅ ድብርትን ለማስወገድ ለእንስሳት የሚሰጥ ከባድ መድሃኒት ሲሆን ሰዎች ለመዝናናት ይጠቀሙበታል።

በጉዋንዡ የሚገኘው ፍርድ ቤትም ዡ ዌሆንግ የተባለው ይህ ግለሰብ በዚህ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የሞት ፍርድ የወሰነበት ሲሆን፤ ተባባሪው ዌን ጉዋንዦንግ ደግሞ የእድሜ ልክ እስራት በይኖበታል።

ግለሰቡ ቻይና በቅርቡ የሞት ፍርድ ካስተላለፈችባቸው ግለሰቦች መካከል ሦስተኛው ካናዳዊ ነው ተብሏል።

የክሱ ዝርዝር ባይገለፅም፤ በደቡባዊ ቻይና ጉዋንዡ የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን ግለሰቦቹ አደንዛዥ እፁን ማምረት የጀመሩት ከአራት ዓመታት በፊት መሆኑን ጠቅሰው፤ በኋላ ላይ ከዡ መኖሪያ ቤትና ከሌላ ቦታ 120 ኪሎ ግራም የሚመዝን አደንዛዥ እፅ በፖሊስ መያዙን ዘግበዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት የሁዋዌ የፋይናንስ ኃላፊ የሆኑት ሜንግ ዋንዡ በአሜሪካ ጥያቄ መሰረት ካናዳ ቫንኩቨር ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሯል።

ይሁን እንጅ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ጉዳዩ አሁን ካለው የቻይናና የካናዳ ግንኙነት ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

"የቻይና የፍትህ ባለሥልጣናት ጉዳዩን በገለልተኝነትና ጥብቅ በሆነው የአገሪቷ ሕግ መሠረት ያዩታል" ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዘ ወንጀል የሚተላለፈው የሞት ፍርድ መሰል ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለማስቆም ይረዳል ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ሌሎች ሁለት ካናዳዊያን ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዘ የሞት ፍርድ ተበይኖባቸዋል።

አንደኛው ሮበርት ለሎይድ ሸለንበርግ የተባለው ግለሰብ በአደንዛዥ እፅ ዝውውር ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሲሆን፤ ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ ሌላኛው ፋን ዌ የተባለው ግለሰብ 'ሜታምፌታሚን' የተባለ አደንዛዥ ዕፅ በማዘዋወር በሞት ተቀጥቷል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ቻይና ሲሰልሉ ነበር ስትል የከሰሰቻቸውን ሁለት ካናዳዊያንንም በቁጥጥር ሥር አውላለች።