ሶርያ፡ የእስራኤል አየር ኃይል የሶርያ ጦር ሰፈርን ደበደበ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የእስራኤል አየር ኃይል የሶሪያ ወታደራዊ ሰፈሮችን ዒላማ በማድረግ መደብደቡን ጦሩ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
በሶሪያ መንግሥት ቁጥጥር ስር የሚገኙ መገናኛ ብዙኃኖች ከዋና ከተማዋ ደማስቆ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ ጥቃት መፈፀሙን አረጋግጠው መጠኑን ያልገለፁት "የቁሳቁስ ውድመት" መድረሱን ዘግበዋል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ጥቃቱን የፈፀመው የቦምብ ጥቃት ለመፈፀም ሙከራ መደረጉን ተከትሎ አፀፋ ለመስጠት መሆኑን አስታውቋል።
መከላከያ ኃይሉ አስቀድሞ እሁድ እለት እስራኤል በምትቆጣጠረው የጎላን ተራሮች ላይ ፈንጂ ለመቅበር የሞከሩ አራት ግለሰቦችን መግደሉን ተናግሮ ነበር።
በቅኝት ካሜራ የተቀረፀ ምስል እንደሚያሳየው ቡድኑ በፍንዳታ ተመትቷል።
የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል ቃል አቀባይ ሌተናንት ኮሎኔል ጆናታን ኮንሪከስ፣ ግለሰቦች የአንድ ቡድን አባላት ናቸው ብሎ ለመናገር ጊዜው ገና ነው ነገር ግን የእስራኤል መንግሥት "የሶሪያ መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋል" ብለው ነበር።
ሰኞ እለት ጥቃት የተፈፀመበት የሶሪያ ወታደራዊ የጦር ሰፈር በቁአኒትራ እንደሚገኝ የገለፀው የእስራኤል መከላከያ ኃይል "ቅኝት ማድረጊያ፣ የመረጃ መሰብሰብያ መሳሪያዎች፣ ፀረ አውሮፕላኖች እና ማዘዣና መቆጣጠሪያ ስርዓቶች" ላይ ድብደባ ተፈጽሟል ሲል ተናግሯል።
"የእስራኤል መከላከያ በሶሪያ ምድር ለሚከናወኑ ነገሮች ሁሉ የሶሪያ መንግሥትን ተጠያቂ የሚያደርግ ሲሆን፣ የእስራኤልን ሉአላዊነት የሚጋፋ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ለመመከት ዝግጁ ነው" ሲል አስታውቋል።
የሶሪያ ዜና ወኪል በበኩሉ ከሰኞ ተሲያት በኋላ ጀምሮ የሶሪያ አየር ኃይል በደማስቆ አካባቢ በነበረው ጥቃት የተነሳ በተጠንቀቅ እንደሚገኝ ተናግሯል።
ይህ በእንዲህ እያለ የሶሪያን የሰብዓዊ መብት አያያዝ የሚከታተለው ድርጅት እንደገለፀው በኢራቅ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ቡካማል ከተማ በደረሰ የአየር ጥቃት 15 ሰዎች መሞታቸውን ገልጿል።
በሶሪያ እና እስራኤል መካከል እስራኤል ከሁለት ሳምንት በፊት የሂዝቦላን ተዋጊ በአየር ጥቃት ከገደለች ወዲህ ውጥረት ነግሷል።
እስራኤል በኢራን የሚደገፈው የሊባኖሱ ቡድን አፀፋ ለመስጠት ይዘጋጃል ብላ ገምታለች።












