ደቡብ ኮሪያ ከኮሮናቫይረ ስርጭት ጋር በተያያዘ አንድ የሀይማኖት መሪ በቁጥጥር ስር አዋለች

ታትሟል

ደቡብ ኮሪያ ካጋጠማት ከፍተኛ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ አንድ የሐይማኖት ቡድን መሪን በቁጥጥር ስር አዋለች።

የ88 ዓመቱ ሊ ማን ሂ 'ሺንቼኦንጂ ቸርች ኦፍ ጂሰስ' የተባለ ቤተክርስቲያን መሪ ሲሆኑ ከ5 ሺ በላይ አባላቶቻቸው ደግሞ በኮሮረናቫይረስ መያዛቸው ተሰምቷል። ይህ ደግሞ በአገሪቱ ካለው የቫይረሱ ስርጭት 36 በመቶ ይሆናል ተብሏል።

በዚህም ሳቢያ የአገሪቱ ባለስልጣናት የሐይማኖት መሪው ስለቡድኑ አባላት እና ሲያደርጉት ስለነበረው ስብሰባ ለመንግሥት አላሳወቁም በማለት ከሰዋቸዋል።

ቤተክርስቲያኒቱ እንዳስታወቀችው የሐይማኖት መሪው የአባላቱን ግላዊ መረጃ ለመጠበቅ በሚል እንጂ ስለቫይረሱ ከመንግሥት መረጃ ለመደበቅ ብለው አይደለም።

በደቡብ ኮሪያ እስካሁን 14 ሺ 336 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋጋጠ ሲሆን 300 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት አካባቢ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሊ ማን ሂ ከዚህ በፊት ምርመራ ሲደረግባቸው እንደነበር ተገልጿል። አንድ የፍርድ ቤት ዳኛ እንደገለጹት በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ከኮሮረናቫይረስ ጋር የተያያዘ መረጃ ሆን ተብሎ እንዲጠፋ ተደርጓል።

የቤተክርስቲያኒቱ ኃላፊ ከዚህ በተጨማሪ 5.6 ሚሊየን ዶላር በመመዝበርና ፍቃድ ያልተሰጠው ሐይማኖታዊ ዝግጅቶችን በማካሄድም ክስ ቀርቦባቸዋል።

የሺንቼኦንጂ ቸርች ኦፍ ጂሰስ ቤተክርስቲያን ባወጣው መግለጫ ሊ ማን ሂ እንደውም ከመንግሥት በተደጋጋገሚ የአባላትን መረጃ አሳልፈው እንዲሰጡ መጠየቃቸው አሳስቧቸው እንደነበረ ገልጾ አሁንም ቢሆን ግን መሪው ምርመራውን ለማደናቀፍ ምንም አላደረጉም ብሏል።

"ፍርድ ቤቱ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማዘዙ ጥፋተኝነታቸውን አያረጋግጥም፤ በሚቀጥሉት የፍርድ ሂደቶች እውነታውን ግልጽ ለማድረግ የተቻለንን ነገር በሙሉ እናደርጋለን'' ብሏል በመግለጫው።

ሊ ማን ሂ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰውና እንደሚመጣ የተነገረው ፓስተር እኔ ነኝ የሚሉ ሲሆን ቤተክርስቲያኒቱን በአውሮፓውያኑ 1984 ነበር ያቋቋሙት።

ሺንቼኦንጂ የሚለው ስያሜውም አዲስ ገነት እና ምድር እንደማለት ነው።

ቤተክርስቲያኒቱ 230 ሺህ አባላት ያሏት ሲሆን በደቡብ ኮሪያ ከሐይማኖት ይልቅ እንደ ቡድን ነው የሚቆጠሩት። የሊ ማን ሂ ተከታዮች በዓለም ፍጻሜ ላይ ፓስተራቸው 144 ሺህ ሰዎችን ወደ ገነት ይዘው እንደሚሄዱ ያምናሉ።

በተጨማሪም ቤተክርስቲያኒቱ ከደቡብ ኮሪያ ውጪ እንደ ቻይና እና ጃፓን ባሉ አገራትም ጭምር እስከ 20 ሺህ የሚደርሱ ተከታዮች አሏት።

የሊ ማን ሂ ተከታዮች የካቲት ወር ላይ ትምህርት ለመከታተል በሚመጡበት ጊዜ እርስ በርሳቸው ቫይረሱን እንዳስተላለፉት የሚገመት ሲሆን ከሥነ ሥርዓቶች በኋላም ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሄደዋል።

መጋቢት ላይ ደግሞ ሊ ማን ሂ ለቫይረሱ ስርጭት ይቅርታ ጠይቀው ነበር።