ኮሮናቫይረስ፡ በበይነ መረብ የተካሄደው ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ

ታትሟል

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በርካታ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ከስረ መሰረቱ ቀይሯል። ከአሁን በፊት ልንጠቀምባቸው ያልመረጥናቸው መንገዶችን የቫይረሱ መከሰት አሁን እንድናጤናቸው ግድ ብሏል።

በአሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት ታውሰን ዩንቨርሲቲ በስፓርት ቢዝነስና ቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ጋሻው አብዛ የኮሮናቫይረስ መከሰትን ተከትሎ ስራቸው በቤት ውስጥ ከሆነ ሰነባብቷል። ነገር ግን አንዳንድ ስራዎቻቸው የግድ በአካል መገኘትን የሚጠይቁ በመሆናቸው፣ ቅርጻቸውን መቀየር ግድ ብሏቸዋል።

ዶክተር ጋሻው በሞያቸው ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጋር በመገናኘት የተለያዩ ሥራዎች ይሰራሉ። ነገር ግን ኮሮናቫይረስ ይህንን ሥራቸውን በአካል ተገኝተው እንዳይሰሩ አግዷቸዋል። ከዚህም ባለፈ ኮሮናቫይረስ በተማሪዎቻቸው ላይ የጤና፣ የሥነ ልቦናና የኢኮኖሚ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ "እንደ መምህር ያ ያሳስበኛል" ይላሉ።

ከቤት ሳንወጣ እንድንሰራ መገደዳችንም ተጽዕኖ ያሳድራል ያሉት ዶ/ር ጋሻው፣ ከህዝብ ጋር መገናኘት አለመቻልና ውጪ ላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ አለመቻልም ሌላኛው ችግር መሆኑን ያብራራሉ።

አገር ቤት መኖሪያቸውን ያደረጉ አትሌቶችን ማማከርና ማስተማር የተጓዳኝ ስራቸው ነው። በስፖርቱ ዘርፍ ያካበቱትን እውቀት አገር ቤት በመመላለስ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ያካፍላሉ፤ ነገር ግን የኮሮናቫይረስ መከሰት ይህንን ከማድረግ አግዷቸዋል። በዚህም ምክንያት ወረርሽኙ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ያብራራሉ።

"አትሌቶች ከመላ አገሪቱ ተሰባስበው መቀመጫቸውን አዲስ አበባ በማድረግ ነው ልምምድ የሚያደርጉት" የሚሉት ዶ/ር ጋሻው፤ በቫይረሱ ምክንያት በመላው ዓለም ኦሊምፒክን ጨምሮ ሁሉም ውድድሮች በመሰረዛቸው የገቢ ምንጫቸው ተዘግቶ ከግማሽ ዓመት በላይ የቆዩ በመሆናቸው፤ የምጣኔ ሃብት ቀውሱ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ይላሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ የአትሌቶች ዋነኛ የገቢ ምንጭ በመላው ዓለም ተዘዋውረው በሚያደርጓቸው ውድድሮች የሚያገኙት ሽልማት ነው። ያንን አሁን ባለው ሁኔታ ማድረግ ስለማይቻልም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ እየገቡ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ዶ/ር ጋሻው በተጨማሪም በየዓመቱ በአሜሪካ ዋሽንግተን የሚካሄድ "ታላቁ የአፍሪካ ሩጫን" ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች ፍላጎት ያላቸውም የሚሳተፉበት ዝግጅት ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ጀምረዋል።

በፈረንጆቹ 2018 ሃሳቡ ተጠንስሶ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ የመጀመሪያ ውድድሩን ያካሄደው ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ፤ በአዋቂዎች̀ 2 መቶ ሰዎች የተሳተፋበት የ5 ሺህ ሜትር እና 200 ታዳጊዎች የተሳተፉበት የህጻናት ውድድር መካሄዱን ይገልጸሉ።

በዚህ ዓመትም ዝግጅቱን ሰፋ በማድረግ በተመሳሳይ ቦታ አሜሪካ ዋሺንግተን፣ በዚህ ወር ላይ ለማካሄድ ታስቦ የነበረ መሆኑን የሚገልጹት ዶ/ር ጋሻው፣ የወረርሽኙ መከሰት ግን ይህ እንዳይሳካ አድርጓል ይላሉ።

በመሆኑም የኢንተርኔት አማራጭን በመጠቀም በተለያዩ የዓለም ክፍል የሚገኙ ታዋቂ ኢትዮጵያዊያንን በማሳተፍ በአይነቱ ለየት ያለ ሩጫ ማካሄዳቸውን ይገልጻሉ።

"የኢትዮጵያ ቨርቹዋል ሩጫ" በሚል ደራርቱ ቱሉ፣ የዲባባ ቤተሰቦች፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ፋጡማ ሮባ እና በላይነህ ዲንሳሞ የመሳሰሉት እውቅ አትሌቶች የተሳተፉበት የዙም ሩጫ ማካሄዳቸውን የተናገሩት ዶክተር ጋሻው፤ ተሳታፊዎቹም ከጀርመን፣ ከእንግሊዝ፣ ከዱባይ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከደቡብ አፍሪካና ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

በ'ዙም' የተደረገው ሩጫ፣ በተለያዩ ብዙሃን መገናኛዎችና የዩቲዩብ ቻናሎችም በቀጥታ መተላለፉን ዶ/ር ጋሻው ተናግረዋል።

የሩጫው ዓላማም ኢትዮጵያውያን ወገኖችን በያሉበት "አይዟችሁ፤ ይህም ጊዜ ያልፋል" ለማለት እና ጎን ለጎን ደግሞ በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጡ ወገኖችን ማሰብ እና ለቫይረሱ መከላከያ የሚሆን ገቢ ማሰባሰብ ነበር ብለዋል።

በማከልም ከዚህ ውድድር የተገኘውን ገቢም ቫይረሱን ለመከላከል እንዲያስችል ለሁለት በጎ አድራጎት ድርጅቶቾ ማበርከታቸውንም ገልጸዋል።

በኮቪድ-19 ምክንያት ለወራት ያክል ከቤት ሆነው ሥራቸውን ሲያከናውኑ፣ኢንተርኔትን በመጠቀም ራት አብሮ መብላት፣ ስብሰባዎችን ማካሄድ፣ ልደት ማክበርና ሥራን በአግባቡ የትም ቦታ ሆኖ በኢንተርኔት መከወን እንደሚቻል ወረርሽኙ በደንብ አስተምሮናል ይላሉ።

በወረርሽኙ ምክንያት ባለፈው ግማሽ ዓመት የተፈጠሩትን አዳዲስ ነገሮችንም "የማይመስል፣ ነገር ግን በኮቪድ-19 ምክንያት የመጣ እውነት ነው" ብለውታል።

"ኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ብቻ አይደለም፤ የአኗኗር ዘይቤያችንን ስር ነቀል በሆነ መልኩ የሚቀይር ጉልበት እና ሃይል ሆኗል" በማለት የኢንተርኔትን ጠቀሜታ ያብራራሉ።

"ኢንተርኔት የዘመናችን ልዩ ስጦታ፣ በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ደግሞ አደጋ ነው" የሚሉት ዶክተር ጋሻው፣ ቴክኖሎጂው በሁሉም ዘርፍ አዲስ ነገር ለማበርከት ምቹ በመሆኑ፣ በተለያየ የሙያ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የአተያይ አድማሳቸውን በማስፋት እና በመቀየር ለማህበረሰባቸው ፈጠራ የታከለበት አስተዋጽዖ ማድረግ ስለሚችሉ ይህንን ትኩረት እንዲያደርጉበት ይመክራሉ።

በሚቀጥለው ዓመት ነገሮች ይስተካከላሉ በሚል ተስፋ ዘንድሮ የተቋረጠውን የታላቁ አፍሪካ ሩጫን ለማካሄድ አቅደዋል። በውድድሩም በርካታ ተሳታፊዎችና የኦሊምፒክ አሸናፊ አትሌቶች እንዲሳተፉ እቅድ መያዙን ዶክትር ጋሻው ገልጸዋል። በፈረንጆቹ 2021 ሰኔ ወር ላይ ዝግጅቱ እንዲካሄድ ጊዜያዊ እቅድ ተቀምጦለታል።