ሲምፕሰንስ 'አፑን' ጨምሮ ነጭ ያልሆኑትን ገፀባህርያት በነጭ ተዋናዮች ድምፅ አልጠቀምም አለ

የፎቶው ባለመብት, TCFFC
የአሜሪካው የአኒሜሽን ተከታታዩ ፊልም ሲምፕሰንስ አፑን ጨምሮ ነጭ ያልሆኑትን ገፀ ባህርያት የነጭ ተዋናዮች ድምፅ መጠቀም ለማቆም መወሰኑን የፊልሙ ፕሮዲውሰሮች አሳውቀዋል።
በፎክስ ኔትወርክ የሚታየው ሲምፕሰንስ ለአመታት ያህል በፊልሙ ላይ ያለው ህንዳዊ አሜሪካዊ ገፀ-ባህርዩ አፑን በነጭ ተዋናይ ድምፅ በመጠቀም ከፍተኛ ትችትን አስተናግዷል። ነጩ ተዋናይ ሃንክ አዛሪያም ገፀ ባህርዩን መጫወት ማቆም እንደሚፈልግም አሳውቆ ነበር።
የአሜሪካ ኢንተርቴይንመንት ኢንዱስትሪም ነጭ ላልሆኑ ተዋናዮች እድልም ሊሰጥ ይገባል በሚልም በርካታ ጊዜ ይተቻል።
በተለይም በነጭ ፖሊስ ተደፍቆ የተገደለውን ጆርጅ ፍሎይድን ሞት ተከትሎ በርካታ ተቋማት ፖሊሲዎቻቸውን እየከለሱ ይገኛሉ።
"ለወደፊቱ ሲምፕሰንስ ላይ ነጭ ላልሆኑ ገፀ-ባህርያት የነጭ ተዋናዮች ድምፅን አንጠቀምም" በማለት አዘጋጆቹ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
በጥር ወር ላይ ነጩ ተዋናይ አዛርያ ሃንክ አዛርያ በፊልሙ ላይ የመደብር ባለቤት የሆነውን ህንዳዊውን አፑ ናሃሳፒማፔትን መጫወት እንደሚያቆምም አሳውቆ ነበር። ገፀ ባህርዩን ለባለፉት ሰላሳ አመታትም ተጫውቶታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ሁላችንም ነን እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስነው። ሁላችንም ትክክለኛ ነገር ነው በሚለው ተስማምተናል" ብሎም ነበር።
የአኒሜሽን ፊልሙ በገፀ ባህርዮቹ የተለያዩ ዘሮችን አሉታዊ በሆነ መልኩ በማሳየትም ያወገዙት አልታጡም።
ሌሎች የአሜሪካ ተዋናዮችም እንዲሁ ነጭ ላልሆኑ ገፀ ባህርያትን በድምፅ እንደማይጫወቱ አስታውቀዋል፤ ከነዚህም መካከል ማይክ ሄንሪና ክርስቴን ቤል ይገኙበታል።
ማይክ ሄንሪ 'ፋሚሊ ጋይ' ለተሰኘው ተከታታይ የአኒሜሽን ተከታታይ ፊልም የጥቁር አሜሪካዊውን ክሊቭላንድ ብራውንን ገፀ ባህርይ ለባለፉት ሃያ አመታት ተጫውቶታል።
"ገፀ ባህርዩን በጣም ነው የምወደው ነገር ግን ጥቁር ተዋናይ ሊጫወተው ይገባል" በማለት ተዋናዩ ውሳኔውን አርብ እለት በትዊተር ገፁ አስታውቋል።
ክርስቲን ቤልም እንዲሁ በሴንትራል ፓርክ ላይ ሞሊ የተባለች የጥቁር ገፀ ባህርይ ወክላ የምትጫወት ሲሆን፣ ይህንን ማድረጓም "ግንዛቤ ያነሰ መሆኑን አሳይቶኛል" ብላለች።












