ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፓኪስታን 97 ሰዎች ያለፉበት የአውሮፕላን አደጋ ምክንያቱ 'የሰው ስህተት' ነው ተባለ
በፓኪስታን ባለፈው ወር ለ97 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የአውሮፕላን አደጋ በአብራሪውና በአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ስህተት ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን የአደጋው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት አመለከተ፡፡
የአቪየሽን ሚኒስተር የሆኑት ጉላም ሳርዋር ካን የአደጋውን የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖረት ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት "አብራሪውና የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪው መመሪያ መከተል አልቻሉም ነበር" ብለዋል፡፡
አክለውም አብራሪው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተረብሾ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ እንዳሉት የፓኪስታን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ኤር ባስ ኤ320 አውሮፕላን ምንም ዓይነት ችግር አልነበረበትም፡፡
"አብራሪው ከአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሚሰጠውን መመሪያ ችላ ብሎ ነበር፤ በሌላ በኩልም የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹ የአውሮፕላኑ ሞተር ችግር እንደገጠመው ለአብራሪው አላሳወቁም ነበር" ብለዋል ካን፡፡
የመንገደኞች አውሮፕላኑ በካራቺ በሚገኙ የመኖሪያ ቤቶች ላይ የተከሰከሰው ግንቦት ወር ላይ ሲሆን ከአደጋው የተረፉትም ሁለት መንገደኞች ብቻ ናቸው፡፡
ከላሆር ተነስቶ እየበረረ የነበረው የመንገደኞች አውሮፕላን በጂናህ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ለማረፍ ሲሞክር ነበር የተከሰከሰው፡፡
አደጋውም የተከሰተው አገሪቷ በወረርሽኙ ሳቢያ ጥለው የነበረውን እገዳ በማንሳት የንግድ በረራዎችን እንደገና ለመጀመር ከፈቀደች ከቀናት በኋላ ነው፡፡
በፓኪስታን ከዚህ ቀደምም በርካታ የአውሮፕላን አደጋዎች መከሰታቸው ይታወሳል፡፡
በጎርጎርሳውያኑ 2010 'ኤርብሉ' የተባለ የግል አየር መንገድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን በኢስላማባድ አቅራቢያ ተከስክሶ ተሳፍረው የነበሩ 152 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ ይህም በፓኪስታን ታሪክ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ያለፈበት አደጋ ነው፡፡
በጎርጎርሳውያኑ2012 በፓኪስታን 'ሆጃኤር' ንብረት የሆነ ቦይንግ 737-200 ባጋጠመው የአየር ጸባይ ለውጥ ሳቢያ ራዋልፒንዲ ለማረፍ ሲቃረብ ተከስክሶ ስድስት የበረራ ሰራተኞችና 121 መንገደኞች ሞተዋል፡፡
በጎርጎርሳውያኑ2016 እንዲሁ የፓኪስታን አየር መንገድ አውሮፕላን ከሰሜናዊ ፓኪስታን ወደ ኢስላማባድ በመብረር ላይ ሳለ በእሳት ጋይቶ ለ47 ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል፡፡