በሜክሲኮ በዕጽ ነጋዴዎችና በፖሊስ መካከል ውጊያ ተደረገ

ታትሟል

በሜክሲኮ በጓናህዋቶ ግዛት፣ ሴላያ በምትባል ከተማ የአደገኛ ዕጽ አስተላላፊዎች ከፖሊስ ጋር ባደረጉት ፍልሚያ ከባድ ጉዳት ደረሰ።

አደገኛ እጽ ነጋዴዎቹ የእውቁ ሳንታ ሮሳ ዴ ሊማ የአደገኛ ዕጽ ሰንሰለት ቡድን አባላት ናቸው።

ፖሊስ ከግጭቱ ጋር ተያይዞ 26 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል። ከእነዚህም መካከል የእዚህ አደገኛ ዕጽ ንግድ ሰንሰለት መሪ (ኤልማሮ) እናትና እህት ይገኙበታል።

ኤልማሮ የሳንታ ሮሳ ዴ ሊማ አደገኛ ዕጽ ንግድ ሰንሰለትን የሚመራ እጅግ የሚፈራው ጆሴ ዮፔዝ የተባለው የአገኛ ቦዘኔዎቹ አለቃ ቅጽል ስም ነው። ኤልቻፖ "አጭሩ" የሚል ትርጉም እንዳለው ሁሉ ኤል ማሮ "ቋጣሪው" የሚል ትርጉም ያለው ነው።

ይህ የአደገኛ ቦዘኔዎች ቡድን እሑድ እለት ከፖሊስ ጋር ባደረገው ውጊያ ስድስት ትልልቅ መደብሮችን ጨምሮ 20 መኪኖችን ነዳጅ እያርከፈከፈ አንድዷል። የሴሊያ ከተማዋም ከባድ ጦርነት ተደርጎባታል።

ይህ የዕጽ አዘዋዋሪ ቡድን ብዙዉን ጊዜ ነውጥ በማስነሳት የተቀነባበረ ዘረፋ ውስጥ የሚሰማራ ሲሆን በከተማዋ ብቸኛው የአደገኛ እጽ ሰንሰለት ቡድን ለመሆን እየታገለ ያለ ነውጠኛ ኃይል ነው።

ሆኖም የዚህ ቡድን አመራር ሕጋዊው ወራሽ እኔ ነኝ በሚል በጆሴ ዮፔዝ (ኤልማሮ) እና በኒው ላራ ቤልማን ወይም በቅጽል ስሙ "ፑማ" መካከል ከፍተኛ ጸብ አለ።

ከዚህ የይገባኛል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ከአንድ ሺ በላይ ሰዎች በዚህች ከተማ ተገድለዋል።

ባሳለፍነው ቅዳሜ ፖሊስ የዚህን አደገኛ ቡድን አለቃ በቁጥጥር ሥር አውላለሁ ብሎ በመነሳቱ የቡድኑ አባላት በቁጣ በርካታ መኪኖችንና ቤቶችን በእሳት አጋይተዋል።

ይህ ድንገተኛ ዘመቻ እየተካሄደ ሳለ የአደገኛ ቦዘኔው አለቃ ጆሴ ዮፔዝ ወይም በቅጽል ስሙ ኤልማሮ ራሱን ቪዲዮ በመቅረጽ ለደጋፊዎቹና ለፖሊስ መመሪያ አስተላልፏል። ይህም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በቀጥታ ተላልፏል።

ኤልማሮ እንዳስጠነቀቀው ፖሊስ የእርሱን አደገኛ ቦዘኔ የእጽ አዘዋዋሪዎች ቡድንን በመድፈሩ ዋጋ ይከፍላል።

ይህ የአደገኛ ቦዘኔዎች አለቃ እንባ እየተናነቀው ለቡድኑ አባላት ባስተላለፈው የቪዲዮ መልዕክት እርሱንና የእጽ አዘዋዋሪውን ቡድኑን ለማዳን ጓደኞቹ ለከፈሉት መስዋእትነት አመስግኗቸዋል።

እርሱ ግን እጅ እንደማይሰጥና እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ መንግሥትን እንደሚፋለምም ዝቷል።

ጎናህዋቶ በተባለችው የሜክሲኮ ግዛት ማነው የአደገኛ ቦዘኔዎች ወራሽ በሚል ከዚህ ቀደምም ውጊያ ሲደረግ ነበር።

ጆሴ ዮፔዝ በዚህ መንገድ ዛቻና ማስፈራሪያ በቪዲዮ ሲያስተላልፍ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ከዚህ ቀደም ምናልባትም ከሦስት ዓመት በፊት እርሱ እስከአፍንጫቸው ድረስ በታጠቁ ጠባቂዎቹ ታጅቦ ባስተላለፈው መልዕክት ጃሊስኮ የተሰኘው የአዲሱ ትውልድ የዕጽ አዘዋዋሪ ቡድን ከጋናህዋቶ ክፍለ ግዛት እንዲወጣ ያስጠነቀቀ ሲሆን አለበሊዘያ ግን እልቂት እንደሚከተል ዝቶ ነበር።

በሜክሲኮ ዕጽ አዘዋዋሪዎች የመንግሥት የነዳጅ ማስተላለፊያ ኩባንያ ከሆነው ፔሜክስ የነዳጅ ቱቦዎች በሕገ ወጥ መንገድ ነዳጅ በመስረቅ ከፍተኛ ገንዘብ ያጋብሳሉ።

የፕሬዝዳንት አንደሩስ ማኑኤል ሎፔዝ ኦብራዶር አስተዳደራቸው የሳንታ ሮሳ ዴ ሊማ የዕጽ ዝውውር ሰንሰለትን ድምጥማጡን እንደሚያጠፋውና ይህም የመንግሥታቸው ተቀዳሚ ተግባር እንደሚሆን በ2019 ዝተው ነበር።

የሳንታ ሮሳ የዕጽ ሰንሰለት ቡድን መሪ ጆሴ ዮፔዝን ለመያዝ ሜክሲኮ በርካታ ሙከራዎችን ብታደርግም አልተሳካላትም።

ከዚህ ቀደም ፖሊስ እርሱን ለመያዝ ጫፍ በደረሰበት ወቅት በመሬት ስር በተቆፈረለት ቱቦ በኩል ሾልኮ መውጣቱ ተዘግቧል።

በዕጽ ዝውውር ታሪክ የ1990ዎቹ ገናና ኮሎምቢያዊው የአደገኛ ዕጽ ንጉሥ ፓብሎ ኤስኮባርን የሚያህል የለም። ከኤስኮባር በኋላ ስሙ የገነነው ኤል ቻፖ ነበር።

ከመንግሥት በታች ራሱን የቻለ መንግሥት ፈጥሮ ነበር የሚባልለት ኤልቻፖ ከጥቂት ዓመታት በፊት በብዙ ድካም በቁጥጥር ሥር ውሎ በከፍተኛ ጥንቃቄ ለአሜሪካ ተላልፎ መሰጠቱ አይዘነጋም።