የጀርመኑ ባንክ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ጠፋብኝ አለ

የዋየርካርድ መጠቀሚያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ዋየርካርድ የተሰኘው የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት ሰጪ ባንክ ከሰሞኑ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ጠፍቶበታል በሚል ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገብቷል።

የሚደንቀው ገንዘቡ እምጥ ይግባ ስምጥ አለመታወቁ ብቻ ሳይሆን እንዴት ከባንኩ ሒሳብ እንደጎደለው እርግጡ አልታወቀም።

ይህን ተከትሎም የባንኩ ሥራ አስፈጻሚ አርብ ዕለት በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውን መልቀቃቸውን ይፋ አድርገዋል።

ይህ የጀርመን ኩባንያ ከ5ሺህ በላይ ሠራተኞች ያሉት ግዙፍ ባንክ ሲሆን ወረቀት አልባ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት ሰጪ ባንክ ነው።

መጀመሪያ አካባቢ ምናልባት ገንዘቡ በፊሊፒንስ ባንክ ውስጥ ጠፍቶ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን የፊሊፒንስ ማዕከላዊ ባንክ ግን እንዲህ ዓይነት ገንዘብ ወደእኔ ድርሽ አላለም ብሏል።

ጠፋ የተባለው ገንዘብ የባንኩን ጠቅላላ ሂሳብ አንድ እጅ የሚይዝ ነው።

የዚህን ኩባንያ ሒሳብ የመረመረው ግዙፉ ኦዲተር ኧርነስት ኤንድ ያንግ ኩባንያ በድርጅቱ ሒሳብ ውስጥ ጉድለቶች ስለተስተዋሉ የኦዲት ሥራውን ማገባደድ ተስኖት ቆይቷል።

ድርጅቱ የጠፋበትን ገንዘብ ተከትሎ የዋየርካርድ ባንክ የስቶክ ገበያ ግምት በ60 ከመቶ ወድቋል።

ይህ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ከባንኩ መሰወሩን ያጋለጠው ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ባለፈው ዓመት በተከታታይ የባንኩ የእሲያ ቅርንጫፍ ሒሳብ ጤና እንደራቀው ሲዘገብ ነበር።

ባንኩ የጠፋው ገንዘብ በእሲያ ሁለት ቅርንጫፍና አጋር ባንኮች ውስጥ መገኘት የነበረበት ነው ብሏል። ገንዘቡን ለአደጋ ጊዜ የመጠባበቂያ ገንዘብ ሆኖ የተቀመጠ ነበር።

ዋየርካርድ ይህ ጠፋ የተባለው ገንዘብ የት እንደገባ ለማወቅ ከኧርነስት ኤንድ ያንግ የተመሰከረላቸው የሂሳብ አዋቂዎች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እንደሚሰራ ቃል ገብቷል።

ዋየርካርድ የዲጂታል ባንክ አገልግሎትን በመስጠት የሚታወቅ ሲሆን ከበርካታ የዓለም መደበኛ የባንክ አገልግሎት ሰጪዎች ጋር በጥምረት ይሰራል።

አሁን ዋየርካርድን ከውድቀት ለማዳን የወጪ ቅነሳ ማድረግን ጨምሮ በከፊል ድርሻውን የመሸጥ ሐሳብም ቀርቧል።

ዛሬ በወጣ መረጃ ገንዘቡ ተሰውሮባቸው ሊሆን ይችላል የተባሉ ሁለት የፊሊፒንስ ባንኮች ዋየርካርድ ጭራሽ ከእኛ ጋር እንዲህ ዓይነት ግንኙነት አልመሰተም፣ የሥራ ግንኙነትም የለንም ብለዋል።