የአሜሪካ ኢኮኖሚ በኮሮናቫይረስ ሰበብ በ30 በመቶ ያሽቆለቁላል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ኢኮኖሚ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከ20 እስከ 30 በመቶ ሊያሽቆለቁል እንደሚችል የፌደራል መንግሥቱ ግምጃ ቤት ሊቀ መንበር ተናገሩ።
ጄሮም ፓውል ለሲቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ እንዳመለከቱት የኢኮኖሚ መቀዛቀዙ በወራት ውስጥ የሚያበቃ ብቻ ሳይሆን እስከ ቀጣዩ የፈረንጆች ዓመትም ሊዘልቅ እንደሚችል ገልጸዋል።
ምናልባትም የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከወደቀበት ተነስቶ ወደነበረበት ለመመለስ ለወረርሽኙ ክትባት እስኪገኝ ድረስ መቆየት ሊያስፈልገው እንደሚችልም ጠቁመዋል።
በዚህም ምክንያት የግምጃ ቤት ሊቀመንበሩ ፓውል ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ተጨማሪ የኢኮኖሚ ማነቃቂያና እርዳታ እንዲያጸድቁ ጥሪ አቅርበው ነበር።
የኮሮናቫይረስ ባስከተለው ጫና ምክንያት ከመጋቢት ወር አጋማሽ ወዲህ ከ36 ሚሊዮን በላይ አሜሪካዊያን ሥራቸውን በማጣታቸው ምክንያት የመንግሥትን ድጋፍ ለማግኘት አመልክተዋል።
ጄሮም ፓውል ጨምረውም "የአሁኑ ወቅት ከባድ ችግር ያጋጠመን ጊዜ ነው። ዜጎች ያሉበትን ስቃይ በቃላት ለመግለጽ ያስቸግራል። ቢሆንም ግን ጊዜ ሊወስድ ይችላል እንጂ ኢኮኖሚው ማገገሙ አይቀርም" በማለት እስከ ቀጣይ ዓመት ድረስ ችግሩ ሊቀጥል እንደሚችል አመልክተዋል።
እስካሁን ያለው የሥራ አጦች ቁጥር እስከ 25 በመቶ ሊድረስ እንደሚችልና ተጎጂዎቹም "ዝቅተኛ ክፍያ የሚያገኙ ሰዎች" እንደሚሆኑና በተለይ ደግሞ ሴቶች በኢኮኖሚ ቀውሱ ክፉኛ ተጎድተዋል ብለዋል።
ነገር ግን የአገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓት ጤናማ በመሆኑና ወረርሽኙም ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውጪ ያጋጠመ "ውጫዊ ክስተት" በመሆኑ አሜሪካ የኢኮኖሚ ድቀት እንደማይገጥማት ተናግረዋል።
ሊቀ መንበሩ አክለውም ባለፉት ሦስት ወራት ኢኮኖሚው እስከ 30 በመቶ ቢያሽቆቁልም፤ ወረርሽኙ ለሁለተኛ ዙር ተመልሶ ጉዳት ካላስከተለ በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ውስጥ "በፍጥነት የማገገም ዕድል አለ" ብለዋል።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ የተመታችው አሜሪካ ከዓለም አገራት ሁሉ የላቀ ቁጥር ያለቸው ሰዎች በሽታው ከመያዛቸው በተጨማሪ ከፍተኛውን የሟቾች ቁጥር መዝግባለች።
በአንዳንድ ግዛቶቿ በእንቅስቃሴ ላይ ተጥሎ የነበረው ዕገደ ከመላላቱ ጋር ተያይዞ በሸታው ተመልሶ ለሁለተኛ ጊዜ ሊያገረሽ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።














