የአፍጋኒስታኑ አሰቃቂ ጥቃት፡ “የመጡት እናቶችን ሊገድሉ ነበር”

የፎቶው ባለመብት, EPA
(ይህ ጽሑፍ አሰቃቂና አንባቢዎችን የሚረብሽ ሊሆን ይችላል)
አፍጋኒስታን ውስጥ 24 ሴቶች፣ ታዳጊዎችና ጨቅላ ሕፃናት በሆስፒታል ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል።
አጥቂዎቹ፤ ካቡል የሚገኘው ዳሻት-ኢ-ባርቺ ሆስፒታል ውስጥ ካሉት የሕክምና ክፍሎች መካከል የእናቶችና ሕፃናት ክፍልን መርጠው ነበር ጥቃት የሰነዘሩት።
ሌሎች ሕክምና መስጫዎች ለሆስፒታሉ መግቢያ ቅርብ ቢሆኑም አጥቂዎቹ አልፈዋቸው ሄደዋል። ፍሬደሪክ ቦኖት እንደሚለው ድርጊታቸው፤ የእናቶችና ሕፃናት ክፍል ላይ ጥቃት ለማድረስ ወስነው እንደመጡ ያሳያል ይላል።
ፍሬድሪክ አፍጋኒስታን ውስጥ የሚገኝ የድንብር የለሽ ሐኪሞች ፕሮግራም ኃላፊ ነው።
“በእናቶችና ሕፃነት ክፍል ያየሁት ነገር የታቀደ ተኩስ እንደነበር አመላክቶኛል። ሴቶቹን አልጋቸው ላይ ሳሉ ነው ተኩሰው የገደሏቸው” ይላል።
“በቃላት ለመግለጽ ይከብዳል”
ጥቃቱ ሲደርስ አሚና ከተወለደች ገና ሁለት ሰዓት ብቻ ነበር የተቆጠረው።
ጨቅላዋ የቢቢ ናዚያ እና ባለቤቷ ራፊላህ ሦስተኛ ልጅ ናት። ቢቢ አሚናን ለመውለድ ወደ ሆስፒታል የሄደችው ከእናቷ ጋር ነበር።
ሁለት ሰዓት ላይ ልጇን በሰላም ተገላገለች። ቤተሰቡ ደስታውን ማጣጣም እንኳን ሳይጀምር አራት ሰዓት ላይ ጥቃት ተሰነዘረ።
ሆስፒታሉ አቅራቢያ ፍንዳታ ይሰማ ነበር። ራፊላህን ጨምሮ ሆስፒታሉ ውስጥ ቤተሰብና ጓደኛ ያላቸው ወደ ሆስፒታሉ በሩጫ አመሩ።
የራፊላህ የአጎት ልጅ ቅጽበቱን እንዲህ ያስታውሰዋል. . .
“ከወዲያ ወዲህ ይሯሯጥ ነበር፤ ምንም ማድረግ ግን አልቻለም፤ ወደ ውስጥ እንዳይገባም ከለከሉት።”
የእናቶችና ሕጻናት ክፍሉ 55 አልጋ አለው። ሦስት ታጣቂዎች ጥቃት ያደረሱትም በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ ነበር።
26 እናቶች እና ነፍሰ ጡሮች በክፍሉ ውስጥ የነበሩ ሲሆን፤ ማምለጥ የቻሉት አስሩ ብቻ ናቸው። ቢቢን ጨምሮ 16 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ከ16ቱ እናቶች ሦስቱ የተገደሉት ማዋለጃ ክፍል ሳሉ ነው። ገና ልጆቻቸውን አልተገላገሉም ነበር።
ቢቢ ናዚያ ሕይወታቸውን ካጡ ስምንት እናቶች አንዷ ናት። ጨቅላዋ አሚና እግሯ ላይ በጥይት ተመትታለች። አምስት ጨቅላዎች፣ ሁለት ታዳጊ ወንዶችና አዋላጅም ተገድለዋል።
ከዲጃ የተባለች ሴት ለሮይተርስ እንደተናገረችው፤ ከታጣቂዎቹ አንዱ ሽጉጥ ደግኖባት ነበር። ከዚያም ወደሌሎች ሁለት ሰዎች ዞረ።
በታጣቂዎቹና የአፍጋኒስታን የጸጥታ ኃይሎች መካከል ለአራት ሰዓታት የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል። በዚህ ወቅት የእናቶችና ሕፃናት ክፍል ሠራተኞችና ታካሚዎች በያገኙበት ለመደበቅ ሞክረዋል።
በስተመጨረሻ ሁሉም ታጣቂዎች ተገድለዋል።
ለኤኤፍፒ ምስክርነቷን የሰጠች አዋላጅ እንደተናገረችው፤ አንዲት አብራት ተደብቃ የነበረች ነፍሰ ጡር ድምጿን አፍና ባለችበት ቦታ አምጣ ወልዳለች።
“ክፍሉ ውስጥ ከሶፍትና ከስካርቭ ውጪ ምንም አልነበረም፤ ባዶ እጃችንን ረዳናት። ልጁ ሲወለድ እትብቱን የቆረጥነው በእጃችን ነው፤ እናትና ልጅን በስካርቫችን ጠቀለልናቸው።”
ፍሬድሪክ እንደሚለው፤ በሆስፒታሉ የአደጋ ጊዜ ክፍል ውስጥ የነበሩ ሰዎች ተኩስና ፍንዳታ ይሰማቸው ነበር። ውጥንቅጡ ጋብ ሲል ያዩትንም ያስተውሳል. . .
“ግድግዳው በጥይት ተበሳስቶ ነበር። መሬቱ ደም ለብሶ ነበር። የተተኮሰባቸው መስኮቶችና የተቃጠሉ መኪናዎችም ነበሩ። እጅግ ያስደነግጣል። ከዚህ በፊትም እዚህ አካበቢ ጥቃት ተሰንዝሮ ያውቃል። የእናቶችና ሕፃናት ህክምና ክፍል ላይ ጥቃት ይደርሳል ብለን ግን አስበን አናውቅም።
“የሚየሳዝነው ይቺ አገር እንዲህ ያሉ ጥቃቶችን ተላምዳለች። ማክሰኞ ዕለት የደረሰውን ግን በቃላት ለመግለጽ ይከብዳል።”
ባለፈው ዓመት ቢቢሲ በሠራው የምርመራ ዘገባ መሠረት፤ ነሐሴ ላይ በየቀኑ በአማካይ 74 ወንዶች፣ ሴቶችና ታዳጊዎች ተገድለዋል። አንድ አምስተኛው ንጹሀን ዜጎች ናቸው።
ማቆሚያ ያጣው ጥቃት
በሆስፒታሉ ላይ ጥቃት ከደረሰ ከሰዓታት በኋላ በሌላ ስፍራ በአጥፍቶ ጠፊ 32 ሰዎች ተገድለዋል። ሰዎቹ ናንጋርሀር በምትባል ግዛት በአንድ ፖሊስ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ነበሩ።
በሌላ በኩል ባልካህ በተባለ ግዛት በአሜሪካ የአየር ድብደባ ቢያንስ አስር ሰዎች ተገድለዋል። የአካባቢው ነዋሪዎችና ታሊባን እንዳሉት ሁሉም ንጹሀን ዜጎች ነበሩ።
ወታደራዊው ኃይል በበኩሉ የተገደሉት ታጣቂዎች ናቸው ብሏል።
ከሁለት ቀናት በኋላ ፓኪታ በተባለች ግዛት ቢያንስ አምስት ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል። እነዚህ ግድያዎች የተፈጸሙት አገሪቱ ወደሰላም ስምምነት ታመራለች ተብሎ በተጠበቀበት ወቅት ነው።
አሜሪካ ከታሊባን ታጣቂዎች ጋር የካቲት ላይ ስምምነት ተፈራርማለች። ለ18 ዓመታት አፍጋኒስታንን ያመሰቃቀላት ጦርነት ያከትማል የሚል ተስፋም ነበር።
በስምምነቱ መሠረት ታሊባን ከአፍጋኒስታን መንግሥት ጋር ለመነጋገር ፍቃደኛነት አሳይቶ ነበር። ሆኖም ግን አሁንም አገሪቱ በጥቃት እየተናጠች ነው። የሰላም ስምምነቱ ያጫረው ተስፋም እየጨለመ ይመስላል።
ሆስፒታሉ ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ ፕሬዘዳንት አሽራፍ ጋሀኒ ታሊባንን ጨምሮ በሌሎችም ቡድኖች ላይ እርምጃ መውሰዱ እንዲቀጥል ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ፕሬዘዳንቱ፤ ታጣቂዎቹ የሰላም ጥሪን ገሸሽ አድገው ጥቃት ማድረሱን ቀጥለዋል ብለዋል።
የትኛውም ቡድን ሆስፒታሉ ላይ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነቱን አልወሰደም። ታሊባን በጋንድዝ ግዛት የደረሰውን ጥቃት ያደረስኩት እኔ ነኝ ሲል፤ አይኤስ ደግሞ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነቱን ወስዷል።
የአሜሪካ ልዑክ ዛልሚ ኻሊልዛድ ለሆስፒታሉ ጥቃት አይኤስን ተጠያቂ አድርገዋል። ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት እያደናቀፉ ነው ብለዋል። ይህ ክስ ግን ማክሰኞ ዕለት የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ለተነጠቁ እምብዛም ትርጉም የለውም።
ጨቅላ የልጅ ልጃቸው ተጎድቶ መሬት ላይ ላገኙት አያት ንግግሩ ዋጋ አይኖረውም። ስድስት ዓመት በሠራችበት ሆስፒታል ለተገደለችው አዋላጅም እርባና ቢስ ነው።
ልጆቹ ካቡል ወደሚገኘው አታቱርክ ሆስፒታል ተዛውረዋል። ልጄ ተርፎ ይሆን ብለው በሆስፒታሉ በር ላይ የልጃቸው ስም እስኪጠራ ይጠባበቁ የነበሩ ቤተሰቦች ልብ ይሰብሩ ነበር።
አንዳንድ ሴቶች ልጆችን በማደጎ እንውሰድ ብለዋል። ነገር ግን ይህ ያስቆጣቸው አያቶች ነበሩ።
ጨቅላዋ አሚና እስካሁን ቀዶ ህክምና ተደርጎላታል። ከዚ በኋላ ሁለት ይቀራታል።
ሐኪሞች በጥይት የተመታውን እግሯን እንደሚያድኑት ተስፋ ያደርጋሉ። ቤተሰቦቿ ግን አካል ጉዳተኛ ትሆናለች ብለው ይሰጋሉ።












