ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ የኔዘርላንድስ መንግሥት 'ነጠላ ሰዎች የወሲብ አጋር ፈልጉ' የሚል መመሪያ አወጣ
የደች መንግሥት ለብቸኞች አዲስ መመሪያ አውጥቷል። መመሪያው አጋር የሌላቸው ነጠላ ሰዎች በዚህ ወረርሽኝ ወቅት አንድ የወሲብ አጋር እንዲፈልጉ ያሳስባል።
ብሔራዊ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ነው ነጠላ ሰዎች በአንድ የወሲብ አጋር ተወስነው ደስታቸውን እንዲያጣጥሙ የሚል ምክር የለገሰው።
ከአጋሮቹ አንዱ ሰው የኮሮናቫይረስ ምልክት ከታየበት ግን ወሲብ ማድረግ አይመከርም ብሏል ተቋሙ።
ተቺዎች የኔዘርላንድስ መንግሥት በዚህ ከባድ ወቅት ምነው አጋር አልባ ሰዎችን ችላ አለ ማለታቸውን ተከትሎ ነው ተቋሙ በአዲስ ምክረ-ሐሳብ ከች ያለው።
ኔዘርላንድስ ውስጥ ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ ግዴታ የሆነው ወርሃ መጋቢት አጋማሽ ላይ ነበር። ሕጉ እንደ ጎረቤት አገራት ጠበቅ ያለ አይደለም። ሰዎች ማኅበራዊ ርቀታቸውን ከጠበቁ ሰብሰብ ብለው ጊዜያቸውን ማሳለፍ ይችላሉ።
ተቋሙ ከትናንት በስትያ ባወጣው መመሪያ ነጠላ ሰዎች ምንም ቢሆን አካላዊ ግንኙት ይሻሉ ብሏል። ወሲብ ሲፈጽሙም ጥንቃቄ እንዳይለያቸውና በተቻለ መጠን ኮሮናቫይረስ የማይዛመትበት መንገድ ይምረጡ ሲልም ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር ለግሷል።
'ለምሳሌ ወሲባዊ ግንኙት ማድረግ ከፈቀዳችሁት ሰው ጋር ምክክር አድርጉ። ሁለታችሁም ከቫይረሱ ነፃ መሆናችሁን አረጋግጡ' ይላል መመሪያው።
አልፎም ነጠላ ሰዎች በአንድ ቢወሰኑ እንደሚመረጥ፤ እዚህም እዚያም ማለቱ ለቫይረሱ መስፋፋት እንደሚዳርግ የተቋሙ መመሪያ ያትታል።
በተጨማሪም ለበርካታ ጊዜያት በጥንድት የቆዩ ሰዎች አንደኛው አጋር የኮሮናቫይረስ እንዳለበት ከጠረጠሩ ወሲብ እንዳይፈፅሙ ተቋሙ መክሯል።
በአሁኑ ጊዜ ኔዘርላንድስ የእንቅስቃሴ እገዳዋን በአምስት ከፍላ በማላላት ላይ ትገኛለች። የመጀመሪያው ክፍል ቤተ-መፃሕፍት፣ የውበት ሳሎኖች፣ ማሳጅ ቤቶች እንዲሁም 'ቴራፒ' የሚሰጡ ክሊኒኮችን መክፈት ነው።
የደች ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩት በአገራቸው ቀስ በቀስ በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር መቀነሷን ካስታወቁ በኋላ ነው እንቅስቃሴዎች መላላት የጀመሩት።
ኔዘርላንድስ ውስጥ ባለፉት 24 ሰዓታት 200 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ሲነገር፤ 53 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል። በጠቅላላው አገሪቱ 43 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ይፋ አድርጋለች። የሟቾች ቁጥር ደግሞ 5 ሺህ 500 ነው።