ኮሮናቫይረስ፡ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ለረሃብ ከተጋለጡ 5 አገራት አንዷ ናት ተባለ

ታትሟል

ዓለም በኮሮናቫይረስ መጨነቋ ሌሎች ጉዳዮች ትኩረት እንዲያጡ አድርጓል።

በዚህም ሳቢያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዓለማችን "የረሃብ ወረርሽኝ" ያጋጥማታል ሲል አስጠንቋቋል። ድርጅቱ በዚህ ዓመት የምግብ እጥረት የሚያጋጥማቸው ሰዎች በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችል አስታውቋል።

በፈረንጆቹ 2019 ላይ በመላው ዓለም አስቸኳይ የምግብ እርዳት ያስፈልጋቸው የነበሩ ሰዎች ቁጥር 135 ሚሊዮን ነበር። በያዝነው የፈረንጆቹ 2020 ግን በቫይረሱ ስርጭት ምክንያት ሰዎች ከቤት እንዳይወጡ ከመደረጉ ጋር ተደራርቦ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 265 ሚሊዮን ይሆናል ብሏል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በፈረንጆቹ 2020 በከፍተኛ ደረጃ በረሃብ የሚጠቁት 5 የዓለማችን አገራትን ለይቷል። እነዚህም የመን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታን፣ ቬንዙዌላ እና ኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ አምስት አገራት ናቸው።

የመን

ሲካሄድባት የቆየው የእርስ በእርሱ ጦርነት ከመጀመሩም በፊት የመን የአረቡ ዓለም ደሃዋ አገር ነበረች። የሳኡዲ አረቢያ መራሹ ኃይልና የየመን ሀውቲ አማጺያን ከ2015 ጀምሮ የሚያደርጉት ጦርነት የአገሪቱን ችግር ከድጥ ወደ ማጡ አድርጎታል።

በየመን የምግብ እርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር 15.9 ሚሊዮን ይገመታል ይላል ድርጅቱ።

ዲሞክራቲክ ሪብሊክ ኮንጎ

ከ25 ዓመታት በላይ በአገሪቱ የዘለቀው ጦርነት የአገሪቱ ዜጎች ችግር ውስጥ እንዲገቡ አደርጓል።

ከጠቅላላው ሕዝብ 15 በመቶ የሚሆኑት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ይሻሉ ተብሏል።

የምግብ እርዳታ ከሚሹት 5 ሚሊዮኑ ደግሞ በአገሪቱ ባለው ጦርነት ከቀያቸው ተሰደው የሚገኙት ናቸው።

ቬንዙዌላ

እንደ የመን እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ በቬንዙዌላ ለተከሰተው የምግብ እጥት ጦርነት ዋነኛ ምክንያት አይደለም። የቬንዙዌላ ፈተና የምጣኔ ሃብት ቀውስ ነው።

ምንም እንኳ ቬንዜዋላ የዓላማችን ትልቁ የነዳጃ ዘይት ክምችት ቢኖራትም፤ ከፍተኛ የሆነው የዋጋ ግሽበት 1/3 የሚሆነው ሕዝቧ የምግብ እጥረት እንዲያጋጥመው አድርጓል።

4.8 ሚሊዮን ቬንዙዌላውያን ከፍተኛ የምግብ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል።

አፍጋኒስታን

አሜሪካ አፍጋኒስታንን እአአ 2001 ላይ ከወረረች ጀምሮ አገሪቱ በጦርነት ስትታመስ ቆይታለች።

ከግማሽ የሚልቁት አፍጋናውያን ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ። ከ11 ሚሊዮን በላይ የአገሪቱ ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተነግሯል።

ኢትዮጵያ

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥር 112.1 ሚሊዮን ነው ይላል። እንደ ድርጅቱ አሃዝ ከሆነ ከጠቅላላው ሕዝብ 8 ሚሊዮን የሚሆኑት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭቶች እና የምግብ ዋጋ መናር የአስቸኳይ ምግብ ፈላጊዎች ቁጥርን ከፍ አንዲል ስለማድረጉ ድርጅቱ አስታውቋል።