የቻይናዋ ሸንዠን ከተማ የውሻና የድመት ሥጋ መብላትን አገደች

ታትሟል

12 ሚሊዮን ዜጎች የሚኖሩባት ሸንዠን ከተማ ይህንን በማገድ የመጀመርያዋ የቻይና ከተማ ሆናለች።

ይህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የዱር እንሰሳትን ሥጋ ተከትሎ የመጣ ስለመሆኑ በመጠርጠሩ ነው። ቻይና የዱር እንሰሳት ሥጋ ንግድም ሆነ መመገብ ላይ ክልከላ ጥላለች።

ሸንዠን ከተማ ከዚህ አንድ እርምጃ ወደፊት በመሄድ ይህ ክልከላ የውሻና የድመት ሥጋንም እንዲጨምር አድርጋለች። ይህ ሕግ ተፈጻሚ የሚሆነው ግን ከአንድ ወር በኋላ በግንቦት 1 ላይ ነው።

በትንሹ 30 ሚሊዮን ውሾች በእሲያ ለምግብነት ይቀርባሉ። ይህ መረጃ የሂዩማን ሶሳይቲ ኢንተርናሽናል ነው። ቁጥሩ ከዚህም ሊጨምር ይችላል።

ያም ሆኖ በቻይና የውሻ ሥጋ መብላት ብዙዎቹ እንደሚያስቡት የሚዘወተር ተግባር አይደለም። አብዛኛዎቹ ቻይናዊያን እንዲያውም ሐሳቡም የላቸውም ብቻም ሳይሆን የሚመኙትም ነገር አይደለም።

ሮይተርስ ከሸንዠን ከተማ እንደዘገበው በክልከላው መግለጫ ውስጥ "ውሾችና ድመቶች ለሰዎች የቀረቡና ወዳጅ እንሰሳት" እንደሆኑና የእነርሱን ሥጋ አለመብላት የስልጣኔ ምልክት እንደሆነም ተጠቅሷል።

የእንሰሳት መብት ተሟጋቾች ውሳኔውን "ይበል የሚያሰኝ" ብለውታል።

"ይህ ውሳኔ ወሳኝ እርምጃ አድርገን ነው የምንወስደው፤ 10 ሚሊዮን ውሾችና 4 ሚሊዮን ድመቶች በጭካኔ በየዓመቱ በቻይና ምድር ይታረዱብን ነበር፤ …" ብለዋል የኤች ኤስ አይ ፖሊሲ ስፔሻሊስት ዳይሬክተር ዶክተር ፒተር ሊ።

ሆኖም ቻይና ዜጎቿ የድብ ሀሞትን መጠቀም መብታቸው እንደሆነ አሳውቃለች። የድብ ሀሞት በቻይና የባሕል ሕክምና ወሳኝ ግብአት ነው።

ቻይናዊያን በተለይ ወረርሽኙን ተከትሎ ለኮሮና በሽተኞች የድብ ሀሞትን በመስጠት ለማከም ይሞክራሉ።

የድብ ሀሞት ለጉበት ሕመም ፈውስ እንደሆነ ቢነገርም ለኮሮናቫይረስ ይሆናል የሚለው ግን ገና አልተጠናም።

የኮሮናቫይረስ መነሻ ነው ተብሎ የሚታሰበው የዉሃን ከተማ እንሰሳት ተዋጽኦ መሸጫ እንደሆነ ከተገመተ በኋላ በርካታ ተመሳሳይ የእንሰሳት ሥጋ ገበያዎች በመላው ቻይና እንዲዘጉ ተደርጓል።

በበሽታው ከተያዙት ቀደምቶቹ ቻይናዊያን በዉሃን ከተማ የዱር እንሰሳት ገበያ ውስጥ ይሰሩ የነበሩና ንክኪ የነበራቸው መሆናቸው ምናልባት በሽታው ወደ ሰው የተላለፈው ከዚያ ገበያ ነው የሚለውን መላምት አጠናክሮታል።