በኮሮናቫይረስ ስጋት ካናዳ እራሷን ከጃፓኑ የኦሊምፒክ ውድድር አገለለች

የካናዳ ስፖርተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በዚህ ዓመት ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበቀው የጃፓን ኦሊምፒክ ካናዳ እራሷን አገለለች።

የጨዋታው ዋነኛ ተሳታፊ ከሚባሉት መካከል የሆነችው ካናዳ እራሷን በማግለሏ በውድድሩ መካሄድ ላይ ተጨማሪ ጥርጣሬ ጥሏል።

ካናዳ ይህንን ውሳኔዋን ያሳወቀችው የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ለመጀመሪያ ጊዜ የኦሊምፒክ ውድድሩ ለሌላ ጊዜ ሊተላለፍ ይችላል በማለት ከተናገሩ በኋላ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውስትራሊያ የኦሊምፒክ ቡድን እንዳለው አሁን ባለው ሁኔታ ውድድሩ በተያዘለት ጊዜ እንደማይካሄድ "ግልጽ እየሆነ በመምጣቱ" ተሳታፊ አትሌቶች ለቀጣዩ ዓመት እንዲዘጋጁ ተነግሯቸዋል።

ጃፓን ለማስተናገድ ለዓመታት ስትዘጋጅለት የነበረው የ2020ው ኦሊምፒክ ውድድር ከአራት ወራት በኋላ በሐምሌ ወር ላይ ነበር የሚካሄደው።

የካናዳ የኦሊምፒክና ፓራኦሊምፒክ ኮሚቴ ውሳኔውን በተመለከተ እንዳለው፤ ከውድድሩ ለመውጣት "አስቸጋሪ" ካለው ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ከአትሌቶች፣ ከስፖርት ቡድኖችና ከካናዳ መንግሥት ባለስልጣናት ጋር መመካከሩን ገልጿል።

ኮሚቴው ጨምሮም ለዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ለዓለም አቀፉ የፓራኦሊምፒክ ኮሚቴና የዓለም የጤና ድርጅት የኦሊምፒክ ውድድሩ በአንድ ዓመት እንዲዘገይ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

"ውድድሩን ለሌላ ጊዜ በማሸጋገር ሂደት ውስጥ የሚያጋጥመውን ውስብስብ ሁኔታን ብንረዳውም፤ ምንም ነገር ከአትሌቶቻችንና ከዓለም ሕዝብ ጤናና ደኅንነት የሚበልጥ አይሆንም" ብሏል የካናዳ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ ላይ።

ኮሮና