ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በባንግላዴሽ ለሴተኛ አዳሪዋ ኢስላማዊ ጸሎተ ፍትሐት መደረጉ እያነጋገረ ነው
የመብት ተሟጋቾች በባንግላዴሽ አንድ ያልተለመደ ነገር አሳክተዋል።
በታሪክ የመጀመርያ ነው የተባለውን ኢስላማዊ ጸሎተ ፍትሐት (ሰላተል ጀናዛ) እንዲሰገድ አስደርገዋል። በአመዛኙ የሙስሊም ቀኖና መሠረት ይህ በሴተኛ አዳሪዎች ሬሳ ላይ ጸሎት ማድረግ እምብዛምም የተለመደ አይደለም።
ሐሚዳ በጉም ትባላለች። በባንግላዴሽ ትልቁ የሴተኛ አዳሪዎች አገናኝ ማዕከል (ብረትል) ውስጥ ስትሰራ ኖራለች። የአልጋ ቁራኛ ከሆነች በኋላ ባለፈው ሳምንት ነበር በ65 ዓመቷ ሕይወቷ ያለፈው።
ስትሞት ታዲያ የት ትቀበር ይሆን የሚለው የሁልጊዜም ጥያቄ ነበር። ሐሚዳ ግን መቀበሪያ ቦታ ብቻም ሳይሆን ጸሎተ ፍትሐትም ተደርጎላታል። በመብት ተሟጋቾች ከፍተኛ ጥረት።
በጸሎት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባልተለመደ መልኩ በቁጥር ብዙ የሚባሉ ሰዎች ነገሩን ለመታደም ተገኝተዋል ነው የተባለው።
ሴተኛ አዳሪነት በባንግላዴሽ ሕጋዊ ቢሆንም የእስልምና እምነት መንፈሳዊ መሪዎች ግን ሴተኛ አዳሪዎቹ የእምነቱ ተከታይ ቢሆኑም እንኳ ጸሎተ ፍትሐት አያደርጉላቸውም። በእስላም መቃብርም እንዲቀበሩ አይፈቅዱላቸውም።
በዚህም ምክንያት ሴተኛ አዳሪዎች ሲሞቱ በብዛት ውል በሌለው ሥፍራ እንዲሁ ቆፈር ቆፈር እየተደረገ እንዲቀበሩ ይደረጋል። አንዳንድ ጊዜም ሬሳቸው ወደ ወንዝ ይጣላል።
ምንም ዓይነት መደበኛ ጸሎትም አይደረግላቸውም። በኢስላም አስተምህሮ መሠረት አንድ አማኝ ሲሞት ሬሳው በተገኘበት ስግደት ይደረጋል። ይህም ሶላተል ጀናዛ ይባላል።
ሐሚዳ ሴተኛ አዳሪ ስለነበረች ይጠብቃት የነበረውም ፈታኝ ሁኔታ ነበር።
ነገር ግን የሴተኛ አዳሪዎች ኅብረት የአካባቢው ፖሊስ የእምነቱና መሪዎች እንዲያነጋግርላቸው ጫና በማሳደራቸው ነገሩ ሌላ መልክ እንዲይዝ ሆነ።
"ኢማሙ መጀመርያ አካባቢ በሐሚዳ ሬሳ ላይ ጸሎት እንዲደረግ እምብዛምም አልፈቀዱም ነበር። እያመነቱ ነው የተቀበሉን" ብሏል በድርድሩ ላይ የተገኘው የፖሊሶች አለቃ አሺቁራህማን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ።
"ኢማሙን አንድ ጥያቄ ጠየቅናቸው፤ 'ኢስላም በሴተኛ አዳሪ ሬሳ ላይ የፍትሐት ጸሎት (ሶላተል ጀናዛ) ላይ አትገኙ ብሎ ያዛልን?' ስንላቸው ምላሽ አልነበራቸውም"
ከዚህ በኋላ ነበር ለሐሚዳ ጸሎቱ እንዲደረግላት የሆነው፤ ባሳለፍነው ሐሙስ።
ራሕማን የተባሉ ነዋሪ እንደገለጹት ሬሳ ላይ በሚደረግ የጸሎት ሥነ ሥርዓት (ሶላተል ጀናዛ) በትንሹ 200 ሰዎች ተገኝተዋል። ከጸሎቱ በኋላም 400 የሚሆኑ ሰዎች ለቅሶ ደርሰዋል።
"ይህ በባንግላዴሽ በፍጹም የተለመደ ተግባር አይደለም። ሰዎች ጸሎቱ ላይ ለመገኘት እስከ ምሽት ነው የጠበቁት። ሴተኛ አዳሪዎችም ዓይናቸው በእንባ ተሞልቶ ነበር" ብሏል ራህማን።
ለሐሚዳ በመቃብሯ ተገኝቶ ጸሎት ካደረሱላት ሰዎች መሀል አንዱ ወንድ ልጇ ነው። ሙኩል ሰይክ ይባላል።
የ35 ዓመቷ ልጇ ላክሲሚም ነበረች። ልጇ ላክሲሚ ልክ እንደ እናቷ ሁሉ በሴተኛ አዳሪ የወሲብ ንግድ አሳላጭ ማዕከል ውስጥ ነው የምትሰራው።
"በፍጹም እናቴ እንደ ሰው ክብር አግኝታ ትቀበራለች አላልኩም ነበር" ብላለች ላክሲሚ።
"ተስፋ አደርጋለሁ ሁላችንም ሴተኛ አዳሪዎች ተመሳሳይ ጸሎተ ፍትሐት እንደምናገኝ" ስትል እናቷ የገጠማት ዕድል ወደርሷም እንዲመጣ እንደምትመኝ ተናግራለች።
የሴተኛ አዳሪዎች ማኅበር ሊቀመንበር የሆነችው ጁሙር እንደተናገረችው ደግሞ ከዚህ ቀደም አባሎቻቸው ሲሞቱ የሟች ቤተሰቦች የመቀበሪያ መሬት ለማግኘት እንኳ ፍዳቸውን ይበሉ ነበር።
በጠዋት ማልደን ሟቾችን ለመቅበር ስንሞክር ሰዎች በዱላ እየደበደቡ ያሳድዱናል ብላለች ለጋዜጠኞች።
ሐሚዳና ልጇ የሚሰሩበት የወሲብ አገልግሎት አሳላጭ ኤጀንሲ (brothel) ከባንግላዲሽ ዋና ከተማ ዳካ 250 ኪ ሜትር በስተምዕራብ ነው የሚገኘው።
የተመሠረተውም በዚያች አገር ታላቋ ብሪታኒያ በቀኝ ገዢነት በነበረችበት ወቅት ነበር።