አሜሪካ ለምትገነባው የድንበር ግንብ የተቀደሱ መካነ መቃብሮችን አፈረሰች

የፎቶው ባለመብት, Laiken Jordahl/Center for Biological Diversity
አሜሪካና ሜክሲኮን የሚለያየውን ድንበር ለመገንባት ቀደምት አሜሪካውያን የተቀደሱ ብለው የሚጠሯቸውን መካነ መቃብሮች እንዲፈርሱ መደረጋቸውን የአሜሪካ ህግ አውጭው አካል እንዲሁም የአካባቢው የቀደምት አሜሪካውያን ህዝብ መሪ አስታውቀዋል።
ይህ እየተፈፀመ ያለው በአሪዞና ሲሆን ባለስልጣናቱ የመካነ መቃብሩን ስፍራ አጥረው በድማሚት በማፈንዳት እያፈረሱት እንደሆነ አስታውቀዋል።
ኦርጋን ፖይፕ የሚል መጠሪያ ያለው ብሄራዊ መካነ መቃብር በዩኔስኮ ሊጠበቁ ይገባቸዋል ተብለው ዕውቅና ከተሰጣቸው ጥንታዊ ስፍራዎች አንዱ ነው።
መካነ መቃብሩ እንዲህ መፈራረሱ ብዙዎች የተቃወሙት ሲሆን የዲሞክራቱ ምክር ቤት አባል ራውል ግሪጃልቫ "ቅዱስ ቦታ ነው ያፈረሱት" ብለዋል።
መንግሥት ከማፍረሱ በፊት የአካባባቢው ይዞታ ያላቸውን የቀደምት አሜሪካውያን ቶሆኖ ኦኦድሃም ማህበረሰብ ለማወያየት አልቻለም ተብሏል።
የአካባቢ ተቆርቋሪዎች በበኩላቸው ከመካነ መቃብሩ መፍረስ በተጨማሪ ከስፍራው በታች ያለ ውሃን የማድረቅ ፤ እንዲሁም በስፍራው የሚኖሩ የዱር አራዊቶችን ራቅ ወዳለ ቦታም ሊያሰድዳቸው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
የድንበሩ ግንብ የሚሰራው በብረት ሲሆን ዘጠኝ ሜትር ከፍታና 70 ኪሎሜትር ርቀትን የሚሸፍን ሲሆን በአካባቢው የሚገኝ ብሄራዊ ፖርክም መሰረቱ ይሆናል ተብሏል።

ጥቂት ስለ ኦርጋን ፓይፕ?
የተባበሩት መንግሥታት ኦርጋን ፓይፕን በተፈጥሮም ሆነ በታሪካዊነቱ መጠበቅ ያለበት ስፍራ እንዲሆን የወሰነው በጎርጎሳውያኑ 1976 ሲሆን ስፍራው ባለው የበለፀገ የተፈጥሮ ሃብትም ዘላቂ ልማትን ማምጣት የሚችል እንዲሁም ለሌሎች ምሳሌ ስፍራ ነው ይለዋል።
በአሜሪካ ምክር ቤት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሊቀመንበር የሆኑት የምክር ቤቱ አባል ራውል ግሪጃልቫ አሜሪካና ሜክሲኮን የሚያዋስናቸውን 644 ኪሎሜትር ግዛት ይወክላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Laiken Jordahl/Center for Biological Diversity
ባለፈው ወር መካነ መቃብሩን በጎበኙበት ወቅት የቀደምት አሜሪካውያንን የኦኦድሃም ማህበረሰብ፣ ጥንታዊ ታጋዮቻቸው የተቀበሩበት ስፍራ መሆኑንም በአካባቢው መሪዎች ተነግሯቸዋል።
"በሰላም ያረፉ ሰዎችን ክብራቸውን ገፎ በድማሚት አፈንድቷቸዋል፤ እሱን ነው ያየነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለአሜሪካ ሚዲያዎች ቃለመጠይቅ በሰጡበትም ወቅት የትራምፕ አስተዳደር ቅዱስ ቦታዎችን እያፈረሰ እንደሆነና የአካባቢውን ጥበቃና ደህንነት በጠበቀ መልኩ ድንበሩ እንዲገነባ የሚቆጣጠረው አካልም እየደረሰ ያለውን የባህል መፍረስ ከቁብም አላስገባም ብለዋል።
በአንድ አካባቢ አስር ሺ አመታትን ያስቆጠሩ ጥንታዊ ቅርሶችን የያዘው ቦታም በዚሁ ፍንዳታ ፈርሷል።
የአሪዞና ሪፐብሊክ የቀደምት አሜሪካውያን መሪ ኔድ ኖሪስ ምንም እንኳን መሬቱ በአሜሪካ መንግሥት ቁጥጥር ስር ቢሆንም "ይህ መሬት ከጥንት ጀምሮ የሰፈርንበት ቦታ ነው" ብለዋል
አክለውም "ያፈረሱት መካነ መቃብር ቦታ የጥንት ቅድመ አያቶቻችን የተቀበሩበት ቦታ ነው። የህዝባችን መነሻ ናቸው፤ ሰዎች ነበሩ፤ ክብርም ያስፈልጋቸዋል። የቀረውን ቦታም መጠበቅ የኛ ግዴታ ነው"ብለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር በ2015 ቃል ለገባው የአሜሪካ ሜክሲኮ ድንበር ለመገንባት 22 አርኪዎሎጂያዊ ቦታዎችን የማፍረስ እቅድ እንደያዘ ዋሽንግን ፖስት ከብሔራዊ ፓርክ ያገኘው መረጃ ያሳያል።
የድንበሩን ግንብ እየገነባ ያለው ቡድን ከዚህም በተጨማሪ ሳጉዋሮ ካክቲ የሚባል ጥንታዊ የኦኦድሃም ማህበረሰብ ስፍራን አፍርሰዋል። ይህ ቦታ ቀደምት አሜሪካውያን የቅድመ አያቶቻቸው መንፈስ የሚኖሩበት ስፍራ ነው ብለውም ያምናሉ።
"እነዚህን ቅዱስ ቦታዎች እንዳልነበር አድርገው ሲያፈራርሷቸው ማየት በጣም የሚያሳዝን ነው" ብለዋል።
መካነ መቃብሮቹን ማፍረስ ህጋዊ ነው?
የትራምፕ አስተዳደር የድንበሩን ግንብ በከፊል መገንባት የጀመረ ሲሆን በህዝብ ይዞታዎች ላይ እየተገነቡ ያሉት።
የድንበሩን ግንብ ለመገንባትም ዋይት ሃውስ በርካታ ህግጋትን ማስተካከል እንዲሁም ይዞታዎች በአስተዳደሩ ስር እንዲሆኑ አድርጓል።
ራውል ግሪጃልቫ በበኩላቸው በጎርጎሳውያኑ 2005 የነበረ ህግን ለመመለስ እየተጋሉ ሲሆን ይህንንም ለማድረግ ሰሞኑን ምክር ቤቱ እቅድ ይዟል።













