ደቡብ አፍሪካ፡ ዘጠኝ 'ህገወጥ' ማዕድን አውጭዎች በድንጋይ ተወግረው ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በምዕራብ ጆሃንስበርግ ግዛት በህገወጥ ማዕድን ቁፋሮ ተሰማርተዋል የተባሉ ዘጠኝ አውጭዎች በድንጋይ ተወግረው መገደላቸው ተሰምቷል።
ፖሊስም ገዳዮቹን ለመያዝ ክትትል ጀምሯል።
ደቡብ አፍሪካን ከምታዋስናት ጎረቤት ሃገር ሌሴቶ የመጡት እነዚህ ማዕድን አውጭዎች አስከሬን ማቶሌቪሊ በሚባል ጎዳና ተጥሎ የተገኘ ሲሆን፤ ከሟቾች በተጨማሪ በህይወትና በሞት መካከል ሲያጣጥር የነበረ አንድ ግለሰብም ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።
'ዛማ ዛማ' (በዙሉ ቋንቋ እድላቸውን ሞካሪ የሚል ትርጉም ያለው) ስም የተሰጣቸው እነዚህ ማዕድን አውጭዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሲሆን በተለያየ የሀገሪቷ ክፍል ተሰማርተው ይሰራሉ።
እዚህ ሰዎች በደቡብ አፍሪካ ሊሰሩ አይገባም በሚሉ ተፎካካሪ ቡድኖች አማካኝነት ተደጋጋሚ ግጭቶች የሚከሰቱ ቢሆንም የአሁኑ ግን የከፋ ነው ተብሏል።
በዚህ ሳምንት አርብ የደረሰው ይህ ጥቃት ፖሊስ አካባቢውን ከከበበው ከሃያ አራት ሰዓት በኋላ የተከሰተም እንደሆነ ተዘግቧል።
ፖሊስ ከግድያው ጋር በተያያዘ 87 ሰዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለጥያቄ እንደሚፈልጋቸው ቢያሳውቅም ዝርዝር ጉዳይ ይፋ አልሆነም።
"ይህን ጭካኔ የተሞላበት አረመኔያዊ ተግባር እናወግዛለን፤ የአካባቢውን ደህንነት ለማረጋገጥም ሆነ ፍትህን ለማስፈን ያለማቋረጥ እንሰራለን" በማለት የጉዋተንግ ግዛት ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ኤልያስ ማዌላ በመግለጫቸው አትተዋል።
"የማረጋገጥላችሁ ጉዳይ ቢኖር ተጠርጣሪዎቹ እንደሚታሰሩና እስከዛ ድረስ ፖሊስ ምንም አይነት እንቅልፍ እንደማይተኛ ነው" ብለዋል።
ኮሚሽነሩ በጆኃንስበርግ የሚገኙ ሌሎች ፖሊሶችም ገዳዮቹን እንዲያድኑ በሚል በተጨማሪ ኃይልነት እንዲሰማሩ አድርገዋል።
በዓለም ላይ ካሉ ሃገራት ከፍተኛ ጥቃት ከሚደርስባቸው ሃገራት አንዷ በሆነችው ደቡብ አፍሪካ ባለፈው አመት አምሳ ስምንት ግድያዎች በአንድ ቀን ብቻ እንደተመዘገቡ የመንግሥት መረጃ ያሳያል።












