ኢራን የዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላንን በስህተት መትታ መጣሏን አመነች

ታትሟል

ኢራን የዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላንን በስህተት መትታ መጣሏን አመነች።

የኢራን ጦር ባወጣው መግለጫ የዩክሬኑ የመንገደኞች አውሮፕላን "ሆነ ተብሎ አለመመታቱን" ገልጿል።

በኢራን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የተነበበው የጦሩ መግለጫ፤ አውሮፕላኑ በኢራን አብዮታዊ ጥበቃ አቅራቢያ በሚገኙ የደህንነት ሥፍራዎች እየበረረ ስለነበረ ''በሰዎች ስህተት" ተመትቶ ስለመጣሉ ተነግሯል።

በመግለጫው የመንገደኞች አውሮፕላኑ ተመቶ ለመውደቁ ኃላፊነት የሚወስዱት ተጠያቂ ይሆናሉ ተብሏል።

ከዚህ ቀደም የአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩክሬን እና ኢራቅ መንግሥታት አውሮፕላኑ በስህተት በሩሲያ ሰራሽ ሚሳኤል ተመትቶ ስለመውደቁ መረጃው አለን ማለታቸው ይታወሳል።

ምዕራባውያኑ መንግሥታት ይህን ይበሉ እንጂ፤ ትናንት የኢራን ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ኃላፊ አሊ አቤደዛዱህ "አውሮፕላኑ በምዕራብ አቅጣጫ ከአየር ማረፊያ ተነስቶ መብረር ከጀመረ በኋላ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ወደ ቀኝ ዞሮ ተመልሶ ለማረፍ እየመጣ ሳለ ነው የተከሰከሰው" በማለት ማስተባበያ ሰጥተው ነበር።

ኃላፊው ጨምረውም የዓይን እማኞች አውሮፕላኑ አየር ላይ ሳለ በእሳት ተያይዞ ማየታቸውን ገልጸዋል።

ከቴህራን እንደተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በተከሰከሰው አውሮፕላን ላይ ተሳፍረው የነበሩት 178 ሰዎች በሙሉ አልቀዋል።

ምዕራባውያኑ ምን ብለው ነበር?

የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ፤ ትናንት አውሮፕላኑ ከምድር ወደ ሰማይ ተወንጫፊ በሆነ ሚሳኤል ተመትቶ ስለመጣሉ ብዙ የደህንነት መረጃዎች ደርሰውኛል ብለው ነበር።

"ካናዳውያን ጥያቄዎች አሏቸው። ለጥያቄዎቻቸውም ምላሽ ማግኘት ይገባቸዋል" በማለት በአደጋው ዙሪያ ዝርዝር ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በአውሮፕላኑ ላይ ተሳፍረው ከነበሩት 178 ሰዎች መካከል 63 ካናዳውያን ሲሆን፤ ከዩክሬኗ ኪዬቨ ወደ ቶሮንቶ ካናዳ የሚያቀኑ ነበሩ።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ትናንት በስቲያ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ''ከዚህ አውሮፕላን ጋር በተገናኘ ጥርጣሬ አለኝ። የሆነ አካል ስህተት ሳይሰራ አይቀርም'' ከማለት ውጪ ዝርዝር ነገር መናገርን አልፈቀዱም።

የዩናይት ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰንም፤ ሃገራቸው ከካናዳ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ አገራት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የዩክሬን የደህንነት ኃላፊ ለአውሮፕላኑ መከስከስ ሦስት ምክንያቶችን አስቀምጠው ነበር። እነዚህም፦

  • አውሮፕላኑ አየር ላይ ሳለ እንደ ድሮን ካሉ ሌላ በራሪ አካል ጋር ተጋጭቷል።
  • የሞተር ብልሽት ወይም በቴክኒክ ችግር ምክንያት አውሮፕላኑ አየር ላይ ሳለ ጋይቷ ወይም ደግሞ
  • በሽብር ጥቃት ከአውሮፕላኑ ውስጥ ፍንዳታ አጋጥሟል የሚሉ መላ ምቶችን አስቀምጠው ነበር።

የአሜሪካ እና ኢራን ፍጥጫ

ለበርካታ ንጹሃን ዜጎች ሞት ምክንያት የሆነው ይህ ሁሉ እሰጣ ገባ የጀመረው አሜሪካ በፕሬዝደንት ትራምፕ ትዕዛዝ ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒን ከገደለች በኋላ ነው።

ዶናልድ ትራምፕ፤ ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒን 'አሸባሪ' ይበሉት እንጂ በኢራናውያን ዘንድ እንደ 'ጀግና' ነበር የሚቆጠረው።

የጦር ጀነራሉ፤ ከፕሬዝደንቱ በላይ እና ከኃይማኖት መሪው በታች የሚገኙ ሁለተኛው የኢራን ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰብ ነበሩ።

ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒ፤ የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ኩድስ ኃይል አዛዥ ነበሩ።

ኢራን ለጀነራሉ ግድያ በአሜሪካ ላይ የአጸፋ ምላሽ ለመውሰድ ብዙ ከዛተች በኋላ፤ በኢራቅ የሚገኙ የአሜሪካ የጦር መንደሮች ላይ የሚሳኤል ድብደባ አድርጋ ነበር።