በዲሞክራቲክ ኮንጎ ማካላ እስር ቤት በርካታ እስረኞች በረሃብ ሞቱ

እስረኞች በማካላ እስር ቤት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, እስር ቤቱ ሲገነባ ይይዛል ተብሎ ከታቀደው በአምስት እጥፍ የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው እስረኞችን ይዟል።
ታትሟል

በዲሞክራቲክ ኮንጎ በሚገኝ ትልቁ እስር ቤት ውስጥ ባለፈው ሳምንት ቢያንስ 17 ሰዎች በረሃብ እና መድሃኒት እጥረት መሞታቸውን አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት አስታወቀ።

የግብረ ሰናይ ድርጅቱ ሠራተኞች የሞት አደጋው በምግብ እና መድሃኒት እጥረት እንዲሁም በንፅህና ጉድለት የተፈጠረ እንደሆነ ተናግረዋል።

በአገሪቷ ዋና መዲና የሚገኘው ማካላ እስር ቤት ባለፉት ሁለት ወራት ምንም አይነት የምግብ አቅርቦት እንዳልተደረገለት የመንግሥት ባለሥልጣናት ገልፀዋል።

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የእስርቤቱ ባለሥልጣንም "በጣም አሳዛኝ ነው፤ በእያንዳንዱ ቀን ሰዎች እየሞቱ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እስር ቤቱ በጣም የተጨናናቀ ሲሆን ሲገነባ ታቅዶ ከነበረው የእስረኞች ቁጥር በአምስት እጥፍ የሚበልጥ እስረኞችን ይዟል።

በእስር ቤቱ ያለው ሁኔታ በጣም የከፋ ሲሆን፤ ቢያንስ 100 የሚሆኑ እስረኞች በጠና ታመው በሞት አፋፍ ላይ እንደሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆነ ቡድን አስታውቋል።

በእስር ቤቱ የሚገኙ ከ8 ሺህ በላይ የሚሆኑ እስረኖች ምግብ ለማግኘት በቤተሰባቸው ላይ ጥገኛ ለመሆን ተገደዋል።

በአስር ቤቱ ውስጥ ከሚገኙት ታሳሪዎች መካከል 6 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ፍርድ የተሰጣቸው ሲሆን፤ ሌሎቹ ጉዳያቸው በአገሪቷ የሕግ ሥርዓት ተይዞ ለዓመታት በእስር ለማሳለፍ የተገደዱ ናቸው።

የአገሪቷ የፍትህ ምክትል ሚኒስትር ሴሌስቲን ቱንዳ ያ ካሴንደ "እውነት ነው፤ ለምግብ አቅራቢዎቹ የክፍያ መዘግየት ነበር፤ በዚህም ምክንያት የምግብ አቅርቦቱ ተቋርጧል" ሲሉ ለኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል አስረድተዋል።

ሚንስትሩ ለአገሪቷ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ምላሽም አሁን ያለውን ሁኔታ ለማሻሻል የሚረዳ የተወሰነ ድጋፍ እንዳገኙ ገልፀዋል።

ይሁን እንጅ ኃላፊው ሌሎች የገንዘብ ድጋፎችም እንደሚቀጥሉ ቢናገሩም፤ በኪንሻሳ የሚገኘው የቢቢሲ የዜና ወኪል እንዳለው ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች የተባለው እውነት ስለመሆኑ ተጠራጥረዋል።

በማካላ እስር ቤት የሞቱት 17 እስረኞች መሞታቸውን ያስታወቀው ድርጅት 'ቢል ክሊንተን ፋውንዴሽን ፎር ፒስ' የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው።

ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ሁኔታ በአገሪቷ በሚገኝ ሌላ እስር ቤት 40 እስረኞች ሕይወታቸው አልፏል።