ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሥራ ባልደረባው የተመረዘው ከዓመታት ጣር በኋላ ሕይወቱ አለፈ
በጀርመን በሥራ በባልደረባው ምግቡ የተመረዘበት ግለሰብ ለአራት ዓመታት በሞት አፋፍ ላይ ከቆየ በኋላ ሕይወቱ ማለፉን የአገሪቷ ሚዲያ ዘገበ።
የ26 ዓመቱ ግለሰብ ሳንዱዊቹ ውስጥ የተጨመረው ሊድ እና ሜርኩሪ ኬሚካል ከፍተኛ የሆነ የአዕምሮ ጉዳት አድርሶበት ነበር።
ሌሎች ሁለቱ ጓደኞቹም ለአደጋው ተጋላጭ የነበሩ ሲሆን፤ በኩላሊታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት አጋጥሟቸዋል።
ድርጊቱ የታወቀው በአውሮፓዊያኑ 2018 በሰሜን ምዕራብ ጀርመን ሆልቴ ስታክብሮክ በብረት መገጣጠሚያ ድርጅት አንድ ሠራተኛ በምሳው ላይ ነጭ ብናኝ በማግኘቱን ነበር።
ይህንን ተከትሎም በሥራ ቦታው የደህንነት ካሜራዎች ተገጥመዋል።
ታዲያ በእነዚህ ካሜራዎች አማካኝነት ነበር ድርጊቱን ፈፅሟል የተባለው ግለሰብ ክላውስ ኦ በሥራ ባልደረቦቹ ለምሳ በተዘጋጀ ሳንዱዊች ላይ የሆነ ነገር ሲያስቀምጥ የተቀረፀው።
በመሆኑም ክላውስ ኦ፤ በግድያ ሙከራ ጥፋተኛ ተብሎ እድሜ ልኩን በእስር እንዲያሳልፍ ባሳለፍነው ዓመት ውሳኔ ተላልፎበታል።
የአገሪቷ አቃቤ ሕግ ቬት ዋልተር፤ በግለሰቡ ድርጊት የተመረዘው ግለሰብ ሕይወት በማለፉ በጀርመን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አዲስ ምርመራ እንዲካሄድ ሊታዘዝ ይችላል ማለታቸውን ዘ ብላይንድ የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
የግለሰቡ መሞት ከምዕራብ ጀርመን ዋና ከተማ በርሊን በ350 ኪሎሜትር በምትርቀው ቤልፌልድ ከተማ ፍርድ ቤት ነበር የተረጋገጠው።
በምግቡ ላይ ሊድ አሴቴት የተባለ ኬሚካል እና ሜርኩሪ መጨመሩም በምርመራ ታውቋል። እነዚህ ኬሚካሎች ጣዕም አልባ ሲሆኑ ወደ ሰውነት ከገቡ በአካል ክፍሎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ያስከትላሉ።
በተጨማሪ ምርመራም በመራዡ ግለሰብ ቤት የታሸገ ሜርኩሪ፣ ሊድ እና ካድሚየም ኬሚካሎች ተገኝቷል።
ባሳለፍነው የአውሮፓዊያኑ 2019 በነበረው የፍርድ ሂደት ዳኛው "ግለሰቡ ለአጠቃላይ ለሕዝቡ አደገኛ በመሆኑ ፍርዱ ሊቀነስለት አይገባም" ሲሉ ውሳኔ አስተላልፈዋል።
ክላውስ ኦ "የተለያዩ ኬሚካሎች ጥንቸሎችን እንዴት ሊጎዳ እንደሚችል እንደ ተመራማሪ ሲሞክር ነበር" ሲሉ አንድ የሥነ ልቦና ባለሙያም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።