በሜክሲኮ የነፃነት ታጋዩ ዛፓታ እርቃን ስዕል ተቃውሞ አስነሳ

በሜክሲኮ የተነሳው ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በሜክሲኮ የነፃነት ታጋዩና፣ የአብዮቱ ጀግና ኤሚሊያኖ ዛፓታ የእርቃን ስዕል ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቷል።

ተቃዋሚዎቹ በሜክሲኮ ከተማ ለዕይታ በቀረበበት ሙዝየም በመሄድ "አቃጥሉት፣ አቃጥሉት" የሚሉ መልእክቶችንም አስተላልፈዋል።

ተቃውሞ ያስነሳው የእርቃን ስዕል ላይ ዛፓታ ትልቅ ሂል ያለው ጫማ ተጫምቶ፣ ሮዝ ቀለም ያለው ኮፍያ፣ በፈረስ ላይ ተቀምጦ እግሩ ወደኋላ ተቀልብሶ መቀመጫውን ፈንደድ አድርጎ ይታያል።

የዛፓታ የልጅ ልጅ ጆርጅ ዛፓታ ጎንዛሌዝ ስዕሉ እንዲወርድ ይፈልጋል።

"ይህ እንዲሆን አንፈቅድም" በማለትም ለአሶሺዬትድ ፕሬስ ተናግሯል።

"ለኛ ለቤተሰቦቹ አብዮተኛውን ጄኔራል እንደ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ (ጌይ) ማሳየት ማዋረድ ነው" ያለው ዛፓታ ጎንዛሌዝ የአያቱ ስዕልን ለማስወረድ እስከ መጨረሻው እንደሚሄዱ አስጠንቅቋል።

በሜክሲኮ አብዮት ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠውና የአብዮቱ መሪ ኤሚሊያኖ ዛፓታ የተገደለው እንደ ጎርጎሳውያኑ በ1919 በ39 አመቱ ነው። በብዙ ሜክሲኮያውያንም ዘንድ እንደ ጀግና የሚቆጠር ነው።

የዛፓታ ስዕል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከተቃዋሚዎቹም መካከል አርሶ አደሮችም ይገኙበታል። ዛፓታ ራሱ ደሃ አርሶ አደር ሲሆን በጉልተኛ ስርአት አመፅ በማስነሳትና የመሬት ከበርቴውንም በመቃወም ይታወቃል።

ከሙዝየሙ ውጭም ለሰአታት በመጮህ ተቃውሟቸውን ገልፀዋል። አንዳንዶቹም ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በስድብ የገለፁ ሲሆን ይህ ሁኔታ ግን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ግንኙነትን በሚደግፉት ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞታል። ለሁለት ጎራም እንዲከፈሉ አድርጓቸዋል።

በትዊተርም ላይ በአስርሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስዕሉን በመደገፍ እንዲሁም በመቃወም መልዕክታቸውን ያሰፈሩ ሲሆን፤ ዛፓታ የሚለውን ስምም ብዙዎች አጋርተውታል።

ተቃዋሚዎቹ ስዕሉ እስኪወርድ ድረስም የሙዝየሙን በር ዘግተው እንደሚቆዩ አስፈራርተዋል። ፋቢያን ቻይሬዝ በተባለው አርቲስት የተሰራው ይህ ስዕል 'አብዮቱ' (ዘ ሪቮሉሽን) የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፤ አውደ ርዕዩም የዛፓታን መቶኛ የሙት አመት አስመልክቶ የተዘጋጀ ነው።

የሜክሲኮ ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በአውደ ርዕዩ ላይ ከሰባ በላይ አርቲስቶች የተሳተፉበት ሲሆን፤ 141 ስራዎችም ቀርበዋል። ምንም እንኳን ተቃውሞ ያስነሳው ይህ ስራ ከአምስት አመታት በፊት ለዕይታ ቢቀርብም ከፍተኛ አትኩሮት ያገኘው፤ የሜክሲኮ የባህል ሚኒስትር ዐውደ ርዕዩን ለማስተዋወቅ በሚል በትዊተርና በፌስቡክ ገፁ ማጋራቱን ተከትሎ ነው።

አርቲስቱ ፋቢያን ቻይሬዝ እንደገለፀው ስዕሉን ለመስራት ያነሳሳውም በብዙዎች ዘንድ የዛፓታ "የወንድነት ፅንሰ ሃሳብ በገነነ መንገድ" መወከሉ ጋር ተያይዞ ነው።

"ማህበረሰቡ የወንድና የሴት አካል እንዲህ መሆን አለበት ብሎ ያወጣውን ህግጋት የማይከተሉ ስናገኝ ምቾትን ይነሳል። በዚህ ስዕል ላይ ብዙዎችን ያበሳጫቸው ምንድን ነው? ተቃዋሚዎች የተናደዱት ዛፓታ ሴትነትን ተላብሷል ወይ በሴት ተወክሏል በሚል ነው" ብሏል።

የአውደ ርዕይ አሰናጅ ሉይ ቫርጋስ በበኩሉ ስዕሉ የአንድ አርቲስት ጥበባዊ መገለጫ ነው፤ ይህም ጉዳይ በሜክሲኮ ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ጉዳይ ውዝግብ አስነስቷል።

ምንም እንኳን ተቃዋሚዎቹ ስዕሉ እስኪወርድ ድረስ በተቃውሟቸው እንደሚቀጥሉ ቢያስፈራሩም የሙዝየሙ ኃላፊዎች ስዕሉን እንደማያወርዱትና ለወራትም ለህዝብ ክፍት እንደሆነ አሳውቀዋል።