አውሮፓ ውስጥ በፖሊስ የሚፈለጉ ሴት ወንጀለኞች ይፋ ተደረጉ

የፎቶው ባለመብት, EUROPOL
የአውሮፓ ሕብረት የወንጀል መከላከል ተቋም ዩሮ ፖል በከባድና በተደራጁ የወንጀል ድርጊቶች የሚፈለጉ ወይም የተፈረደባቸው ናቸው ያለቸውን ሴት ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ዘመቻ መጀመሩን ይፋ አደረገ።
የአውሮፓ አገራት የፖሊስ ተቋም የሆነው ዩሮፖል አህጉሪቱ ውስጥ በወንጀል ድርጊቶች "እጅግ ተፈላጊ" የተባሉትን ሴቶች ፎቶግራፎችን ለዚሁ ተግባር በከፈተው የኢንተርኔት ገጽ ላይ አስፍሯል።
በድረ ገጹ ላይ የተፈላጊዎቹ ፎቶ በጭምብል የተሸፈነ ሲሆን ገጽታቸውን ለማየት የሚፈልግ ሰው በጭምብል የተሸፈነውን ምስል ሲጫን የተፈላጊዎቹ ማንነት ይገለጣል።
አውሮፓ ውስጥ በወንጀል ከሚፈለጉት ሴቶች መካከል ዘጠኝ ሩሲያዊያን ወጣት ሴቶችን በህገ ወጥ መንገድ ወደ ስፔን በመውሰድ በኃይል የወሲብ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ አድርጋለች ተብላ የምትፈለገው ኤሌና ፑዚሬቪች አንዷ ናት።
ሌላዋ ደግሞ አንጀሊና ሳችዮካ ከአምስት ዓመት በፊት ላቲቪያ ዋና ከተማ ሪጋ ውስጥ አንዲትን ወጣት ደብድባ በመግደል የምትፈልግ ናት።
የዩሮፖል ቃል አቀባይ ክሌር ጆርጅ እንዳለችው በዚህ ዘመቻ የጠፉትን ወንጀለኞች ፈልጎ ለማግኘት ያለውን ዕድል ከፍ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል።
"ምንም እንኳን በአብዛኛው ስለሚፈለጉ ወንድ ወንጀለኞች ቢነገርም፤ ሴቶችም በድርጊቱ እጃቸው አለበት። እኛ ማሳየት የፈለግነው ሴቶችም እንደ ወንዶች ሁሉ አደገኛ ወንጀል የመፈጸም ዕድል እንዳላቸው ነው" ብላለች ክሌር።
ቃል አቀባይዋ ክሌር አክላም ዩሮፖል የአውሮፓ አገራት በጣም የሚፈልጓቸውን ሴት ወንጀለኞችን ዝርዝር እንዲያቀርቡ የተጠየቁ ቢሆንም ዩናይትድ ኪንግደም፣ ቆጵሮስና ሉክሰምበርግ ግን ወንድ ተፈላጊዎችን ነበር የላኩት።

የፎቶው ባለመብት, EUROPOL
ዩሮ ፖል ይህንን ማድረግ የፈለገው ሴቶችም እንደ ወንዶች ሁሉ ከባድ ወንጀል ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ለማሳወቅ እንደሆነ ገልጿል።
ምንም እንኳን በዓለም ዙሪያ ሴቶች በከባድ ወንጀሎች ውስጥ ተሳታፊ ቢሆኑም አብዛኞቹ ወንጀሎች የሚፈጸሙት ግን በወንዶች እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በከባድ ወንጀሎች ላይ የሚሳተፉ ሴቶችን በተመለከተ በብሪታኒያ መንግሥት እንዲሰራ ተደርጎ ይፋ የተደረገውና በቅርቡ ይፋ የተደረገው አንድ ጥናት እንዳመለከተው በተደራጁ የወንጀል ቡድኖች ውስጥ ያለውን የመሪነት ስፍራን ጨምሮ በወንጀል ድርጊቶች ውስጥ አብዛኛውን ሚና የሚጫወቱት ወንዶች ናቸው።
"ወንጀል ጾታ የለውም" በሚል ስያሜ የተከፈተው ይህ ድረ ገጽ እየተፈለጉ ያሉ 21 ወንጀለኞችን ያቀረበ ሲሆን ከእነዚህ መካከልም 18 ሴቶች ሲሆኑ ሦስቱ ደግሞ ወንዶች ናቸው። ድረ ገጹን ለመመልከት የሚከፍቱ ሰዎች በጭምብል የተሸፈነውን የተፈላጊዎችን ምስል እስኪገልጡ ድረስ ሆን ተብሎ ጾታቸውን እንዳያውቁ ሆን ተብሎ ተደርጓል።
በኬንት ዩኒቨርስቲ የሥነ ጾታና የወንጀል ጥናት ባለሙያ የሆኑት ዶክትር ማሪያን ዱጋን ለቢቢሲ እንደተናገሩት የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች ከባድ ወንጀሎችን ሲፈጽሙ ለጾታ የተሰጡ ፍረጃዎችን ይጠቀሙበታል።
ለምሳሌም በዩሮ ፖል ዘመቻ ውስጥ ከተጠቀሱት ሴቶች መካከል አብዛኛዎቹ ከወሲብ ተግባራትና ከዕፅ ዝውውር ጋር የተያያዙ ናቸው።
"ለነዚህ የወንጀል ድርጊቶች ደግሞ የሴቶች ሚና አስፈላጊነትን የወንጀል ቡድን መሪዎች ጠንቅቀው ይረዱታል" በማለት ሴቶቹ እነዚህ ከባድ ወንጀሎች ብቻቸውን እንደማይፈጽሙት አመልክተዋል።














