ሟች የኬንያ የፊልም ቦርድ አባል ተደርገው ተሾሙ

ሮበርት ኮቻሌ

የፎቶው ባለመብት, Twitter

ታትሟል

ከአንድ ዓመት በፊት የሞቱት ግለሰብ በስህተት የኬኒያ የፊልም ደረጃ ምደባ ቦርድ አባል ተደርገው መመደባቸውን ባለስልጣናት ገለፁ።

ሮበርት ኮቻሌ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የዛሬ ዓመት ሲሆን የኬኒያ የፊልም ደረጃ መዳቢዎች ሆነው ከተመደቡ ሦስት የቦርድ አባላት መካከል አንዱ ሆነው ነው የተሾሙት።

የኬንያ ፊልም ደረጃ መዳቢ ሲኒማዎችንና በቴሌቪዥንና ሬዲዮ አየር ላይ የሚውሉ ፕሮግራሞችን ይዘት የሚቆጣጠር አካል ነው።

ኬንያዊያን በማህበራዊ የመገናኛ ብዙኀን መድረኮች ላይ ወጥተው በመንግሥታቸው ላይ ትችታቸውን ያዘነቡ ሲሆን የኬኒያ መንግሥት ሀገራዊ ጉዳይን እንዴት ባለ ዝርክርክነት እንደሚይዝ ማሳያ ነው ሲሉ ቁጣቸውን ገልፀዋል።

የቦርዱ ሊቀመንበር የሆኑት እዝቄል ሙቱአ ግን "እዚህ ግባ ማይባል ነገር ከበቂ በላይ ታገዝፋላችሁ" ሲሉ ተቺዎቹን ኮንነዋል።

ስህተቱ ሊፈጠር የቻለው የፊልም ደረጃ መዳቢው ከአንዱ የሚንስትር መሥሪያ ቤት ወደ ሌላ ሲዛወር በተፈጠረ መምታታት ሊሆን እንደሚችል አክለው ገልፀዋል።

ኬንያዊያን ግን የቦርድ ሊቀመንበሩ ማስተባበያ አልተዋጠላቸውም።

አንዳንዶች ጉዳዩን የሳቅ መፍጠሪያ፣ የጨዋታ ማድመቂያ ያደረጉት ሲሆን 'ሟች ከመሾማቸው በፊት ፈቃዳቸው ተጠይቆ ይሆን' በማለት ተሳልቀዋል።