በሕንድ ከእነ ነፍሷ የተቀበረችው ጨቅላ በህይወት ተገኘች

የፎቶው ባለመብት, Anoop Kumar Mishra
በሰሜናዊ ሕንድ ከነነብሷ በመቃብር ስፍራ ተቀብራ የነበረች ጨቅላ በህይወት መገኘቷን የሕንድ ፖሊስ አስታወቀ።
አበሂናንዳን ሲንጋህ የተባሉ የፖሊስ ኃላፊ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ ጨቅላዋ የተገኘችው አንድ የአከባቢው ነዋሪዎች እንደተወለደች የሞተች ጨቅላን ለመቅበር እየቆፈሩ ሳሉ ነው።
በአነስተኛ ሸክላ ውስጥ ተደርጋ ተቀብራ በህይወት የተገኘችው ጨቅላ ወደ ሆስፒታል ከተወሰደች በኋላ እያገገመች ነው ተብሏል።
ፖሊስ እንዳለው ከሆነ ጨቅላዋ 90 ሴንቲ ሜትር ጥልቀት ባለው ጉድጓድ ሸክላ ውስጥ ተደርጋ ነው የተቀበረችው።
"የጨቅላዋን ወላጆች እየፈለግን ነው። ይህ ወንጀል በወላጆች እውቅና ወይም በወላጆቿ እንደተፈጸመ ጥርጣሬ አለን" ሲሉ የፖሊስ ኃላፊው ተናግረዋል።
የፖሊስ ኃላፊው ጨምረው እንደተወለደች የሞተችውን ልጅ ለመቅበር ሲቆፍሩ የነበሩት የአከባቢው ሰዎች ድንገት ጨቅላዋ ተቀብራበት የነበረውን ሸክላ በመቆፈሪያው ከተመታ በኋላ ጉዳዩ ትኩረታቸውን ስቦ ህጻኗ መገኘቷን ተናግረዋል።
"ፖሊስ የጨቅላዋን ጤንነት በቅርበት እየተከታተለ ነው። እያገገመች ነው።" ሲሉ አበሂናንዳን ሲንጋህ ተናግረዋል።
በሕንድ በተለይ ደግሞ አነስተኛ ገቢ ባላቸው ማህበረሰብ ውስጥ ሴት ልጆች እንደ ዕዳ ይቆጠራሉ። በዚህም ጥቂት የማይባሉ ወንድ ልጅ ለመውለድ ፍላጎት ያላቸው እናቶች ያረገዙት ሴት ልጅ መሆኗን ሲያውቁ ውርጃ ይፈጽማሉ።
በሕንድ ከወሊድ በኋላ ሴት ጨቅላ ህጻናትን መግደል አዲስ ዜና አይደለም።















