ታይፎን ሃግቢስ፡ ጃፓን 110 ሺህ የነፍስ አድን ሠራተኞችን አሰማራች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባሳለፍነው ቅዳሜ ጃፓን 'ታይፎን ሃግቢስ" በተባለ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ ከተመታች በኋላ ከ110 ሺህ በላይ የነፍስ አድን ሠራተኞችን ለፍለጋ እና ለነፍስ አድን ሥራ ላይ አሰማርታለች።
'ታይፎኑ' በአስርት ዓመታት ውስት ካጋጠመው በጣም ከባዱ እንደሆነ ተነግሯል። በአደጋውም 37 ሰዎች ሲሞቱ 20 የሚሆኑት የደረሱበት አልታወቀም።
ክስተቱ ሦስት የራግቢ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች እንዲሰረዙ ምክንያት ሆኗል። ነገር ግን በጃፓንና በስኮትላንድ የነበረው ውድድር ቀደም ብሎ ተካሂዷል።
በውድድሩ ጃፓን 28 ለ21 የረታች ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሩብ ፍፃሜ አልፋለች።
ከውድድሩ በኋላም የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ጃሚ ጆሴፍ በአደጋው ለተጎዱ ወገኖች ሃዘናቸውን ገልፀዋል።
"በታይፎን ጉዳት ላጋጠማችሁ በሙሉ፤ ይህ ጨዋታ የሁላችሁም ነው። ጭንቀቱ በጣም ከባድ ነበር፤ በመሆኑም ዛሬ የተካሄደው ከጨዋታም በላይ ነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምንም እንኳን አሁን ነፋስ የቀላቀለው ዝናብ የቀነሰና ከመሬት ሸሽቶ የሄደ ቢሆንም በርካታ ጥፋቶችን ግን ጥሎ አልፏል።
በሺህዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች፣ የእሳት አደጋ ሠራተኞች፣ የድንበር ጠባቂዎች እና ወታደሮች በመሬት መንሸራተት እና በጎርፉ ሳቢያ ለተጎዱ ሰዎች ለመድረስ እየሠሩ ይገኛሉ።
በጃፓን ስምንት የሚሆኑ ግዛቶች በጎርፉ የተጎዱ ሲሆን በመካከለኛው ግዛት ናጋኖ፤ የነፍስ አድን ሠራተኞች ቡድን በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ለመታደግ ወገባቸው ድረስ የሚያጠልቅ ውሃ ውስጥ ገብተው እየፈለጉ ነው።
በናጋኖ የባቡር ማቆሚያ ቦታም በጎርፍ ተሞልቶ የነበረ ሲሆን፤ 10 ፈጣን ባቡሮች በጎርፉ ተውጠዋል። እያንዳንዱ ባቡር 30 ሚሊየን ዶላር ያወጣል ተብሎ ይገመታል።
የጃፓን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፤ የነፍስ አድን ሠራተኞቹ በጎርፉ ምክንያት የተወሰዱ እና ግምት ውስጥ ያልገቡ ቤቶች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ ብሏል።
እሁድ ዕለት የኤሌክትሪክ ኃይል ከተቋረጠባቸው 262 ሺህ መኖሪያ ቤቶች አሁን ላይ ቁጥሩ ወደ 92 ሺህ መኖሪያ ቤቶች ዝቅ ቢልም፤ 120 ሺህ የሚሆኑት የውሃ አቅርቦት የላቸውም።
በአደጋው ከ7 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው የነበረ ሲሆን፤ በመጠለያ ውስጥ የነበሩት ግን 50 ሺህ ብቻ ነበሩ ተብሏል።
የጃፓን ዋና መዲና ቶክዮ በአንፃራዊ መልኩ ከአደጋው የተረፈች ቢሆንም ሌሎች ከተሞች ግን በጎርፉ ተመትተዋል።
በሃኮኔ ከተማ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ አንድ ሜትር ጥልቀት ያለው ጎርፍ ያጋጠመ ሲሆን በጃፓን በ48 ሰዓታት ውስጥ ከተመዘገበው ከፍተኛው ነው ተብሏል።
በናጋኖ፤ ከችኩማ ወንዝ ሞልቶ የፈሰሰው ጎርፍ መኖሪያ ቦታዎች በጎርፍ እንዲጥለቀለቅ አድርጎታል።
ጃፓን በታይፎን የተመታችው ባለፈው ወር ብቻ ሲሆን 30 ሺህ የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶች ወድመዋል፤ ቤቶቹ እስካሁንም ድረስ አልተጠገኑም።














