ኡጋንዳዊያኖቹ የምስራቅ አፍሪካን የተሰጥኦ ውድድር አሸነፉ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

ኡጋንዳዊያኖቹ እህትና ወንድም ኢስተርና እና ኢዝኬል ሙተሳሲራ፤ በአህጉሪቱ የሚገኙ አራት አገራት በተሳተፉበት የምስራቅ አፍሪካ የተሰጥኦ ውድድር አሸናፊ ሆነዋል።

እሁድ ምሽት በተካሄደውና እና ስድስት ተወዳዳሪዎች በቀረቡበት የመጨረሻ ውድድር በማሸነፋቸው የ50 ሺህ ዶላር የገንዘብ ሽልማት አሸናፊ መሆን ችለዋል።

ለመጨረሻ ዙር ውድድር ያለፉት ከኡጋንዳ 'ኮሜዲክ ዳንስ ግሩፕ'፣ 'ዳንስ አሊያንስ ኔትወርክ' ፣ 'ጀሆቫህ ሻሎም አካፔላ'፤ ከኬንያ 'ጃኔላ ታማራ' እና 'ስፔል ካስት'፤ 'ኢንትዮብራና ካልቸራል ትሩፕ' ከሩዋንዳ ይገኙበታል።

ኢስተር እና አዝኬል የዊትኒ ሂውስተንን እና የማሪያ ኬሪን 'ዌን ዩ ብሊቭ' ሙዚቃ ያቀረቡ ሲሆን በዳኞች እና 'ኢኤ ጂቲ ፋይናል' በሚል ሀሽ ታግ በትዊተር ገጽ ሲካሄድ በነበረው ድምፅ ማሸነፍ ችለዋል።

የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙስቬኒ ተወዳዳሪዎቹ ካሸነፉ በኋላ "ስለ ዜናው ከልጅ ልጆቼ ሰማሁ፤ ጥሩ ሙዚቃ ነበር ያስደመጣችሁን። እንኳን ደስ አላችሁ!" ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ ደስታቸውን ገልፀዋል።

የተሰጥኦ ውድድሩ የእንግሊዛዊው ሳይመን ኮዌል የሆነው 'ጋት ታለንት' አካል ሲሆን ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያና አዘጋጇ ኬንያ ተሳትፈውበታል።

ባሳለፍነው ነሃሴ ወር የብሩንዲ መንግሥት በአገሪቷ ዝነኛ የሆነውን ከበሮ (ድራም) ብሩንዲያውያን ስደተኞች በዝግጅቱ ላይ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ተጫውተዋል በሚል ከከሰሰ በኋላ ውድድሩ በብዙዎች ዘንድ የመከራከሪያ ርዕስ ሆኖ ነበር።

በተሰጥኦ ውድድሩ ላይ ከበሮውን የተጫወተው የብሩንዲ ስደተኛ በጎረቤት አገር ሩዋንዳ ነዋሪ ነው።

የብሩንዲ ሕግ ያለ መንግሥት ፈቃድ የአገሪቷን ከበሮ መጫወት ይከለክላል።

የብሩንዲ ንጉሳዊያን ከበሮ በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 2014 በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም [ዩኔስኮ] ተመዝግቧል።