ገዳይ የሆነው እስያዊ ፈንገስ በአውስትራሊያ ተገኘ

ታትሟል

በዓለማችን ገዳይ ከሆኑት አንዱ የሆነው የፈንገስ ዝርያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውስትራሊያ በቅሎ መገኘቱን ተመራማሪዎች አረጋገጡ።

ፈንገስ በሥሩ እንጉዳይን ጨምሮ 144 ሺህ በላይ ዝርያዎች እንዳሉት ይነገራል።

ይህ በአውስትራሊያ የተገኘው ፈንገስ 'ፖይዝን ፋየር ኮራል' ይሰኛል። ቀይ መልክ ያለው ይህ መርዛማ የፈንገስ ዝርያ ከዚህ ቀደም በጃፓንና ኮሪያ ይበቅል እንደነበር ይነገራል።

ዝርያው በእስያ ከዚያም በትሮፒካል ኪዊንስ ላንድ ግዛት መታየቱ ተከትሎ ወደ ሌሎች ቦታዎችም ሊዛመት እንደሚችል አጥኝዎቹ ተናግረው ነበር። ፈንገሱ ለምግብነት ከዋለ የአካልና የአዕምሮ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ነው።

በጃፓንና በደቡብ ኮሪያ ከተመዘገቡ ሞቶች የተገኘ ምርመራ እንዳመላከተው ሰዎች ይህ መርዛማ ፈንገስ፤ ለባህላዊ መድሃኒትነት ይጠቀሙበት ከነበረው ፈንገስ ጋር ስለሚምታታባቸው ባለማወቅ ሻይ ለማፍላት ይጠቀሙበት ነበር።

ፈንገሱ እንኳንስ ተጠጥቶና ከአካል ጋር ከተነካካ የሰውነት መቆጣትና የቆዳ ችግሮች ሊያስከትል እንደሚችል የጀምስ ኩክ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ።

"በአጥኝዎች ከሚታወቁት ከመቶዎቹ ዝርያዎች ወይም በጣም መርዛማ ከሆኑት እንጉዳዮች መካከል መርዙ በቆዳ ውስጥ ሰርፆ ሊገባ የሚችለው ይህ ብቻ ነው" ብለዋል ዶ/ር ማት ባሬት።

ተመራማሪው ይህ ፈንገስ መኖሩን ማረጋገጥ የቻሉት በካርንስ ከተማ አቅራቢያ ጫካ ውስጥ አንድ የአካባቢው ፎቶ አንሽ ምስሉን በፎቶ ካስቀረው በኋላ ነበር።

ይሁን እንጂ ፈንገሱ በቻይና፣ ታይላንድ እና ፓፑዋ ኒው ጊኒ መታየቱን ዶ/ር ባሬት ተናግረዋል። ተመራማሪው እንደሚሉት ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት ነፋስ ብናኙን ሳያዛምተው እንዳልቀረ ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልፀዋል።

"በትሮፒካል አውስትራሊያ እንጉዳይን የሚሰበስቡ ባለሙያዎች የሉንም፤ በመሆኑም እስካሁን ድረስ ይህ ዝርያ ሳይገኝ ሊቆይ ችሏል" ሲሉ ተመራማሪው ለቢቢሲ አስረድተዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት ፈንገሱ ባለፉት ስድስት ወራት በአውስትራሊያ ውስጥ ካልተለዩ፤ ነገር ግን ከተገኙ ከ20 በላይ ዝርያዎች አንዱ ነው።