ሞቷል ተብሎ የነበረው የአል ሸባብ መሪ በህይወት እንዳለ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በካንሰር ህመም መሞቱ የተነገረው የሶማሊያው ታጣቂ እስላማዊ ቡድን አል ሸባብ መሪ አህመድ ዲሪዬ በህይወት እንዳለ ተነገረ።
ግለሰቡ መሞቱ ከተነገረ ከዓመት በኋላ የተለቀቀው የድምጽ መልዕክት ዲሪዬ በህይወት እንዳለ አመላካች መሆኑ ተገልጿል።
በአል ሸባብ ቡድን የመገናኛ ብዙኀን ክንፍ በኩል ይፋ በተደረገው የ20 ደቂቃ የድምጽ ቅጂ ላይ በተደረገ ትንተና ድምጹ ከነሐሴ 16/2011 እስከ መስከረም 6/2012 ባለው ጊዜ ውስጥ የተቀረጸ መሆኑ ተነግሯል።
ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለው የአል ሸባብ ቡድን መሪ የነበረው አህመድ አብዲ ጎዳኔ ከአምስት ዓመት በፊት በአሜሪካ በተፈጸመ የአየር ጥቃት መገደሉን ተከትሎ የመሪነት ቦታውን የተረከበው አህመድ ዲሪዬ ባስተላለፈው የድምጽ መልዕክት በተለያዩ ርዕሶች ላይ ሲናገር ተደምጧል።
ጠንከር ያለ ድምጸት ያለው የዚህ የድምጽ መልዕክት ዋነኛ ዓላማ ግለሰቡ በህይወት እንዳለ ታልሞ የተደረገ ንግግሩ መሆኑ ተገልጿል።
የእስላማዊው ቡድን መሪው አህመድ ዲሪዬ እድሜው በአርባዎቹ ክልል ውስጥ እንደሚሆን የሚገመት ሲሆን፤ ባስተላላፈው በዚህ የድምጽ መልዕክት ላይ አል ሸባብ በሞቃዲሾ ከንቲባ ላይ ስለፈጸመው ግድያ፣ በቅርቡ ስለተካሄደውና አወዛጋቢ ስለነበረው የደቡብ ጁባላንድ ምርጫም አንስቷል።
በተጨማሪም የቡድኑ መሪ በቅርቡ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደሚሰማ ስለሚጠበቀውና በሶማሊያና በኬንያ መካከል ስላለው የባሕር ጠረፍ ውዝግብም በማንሳት፤ አል ሻባብ ጉዳዩን በተመለከተ የሚሰጥን የውጭ ፍርድ ቤት ውሳኔን እንደማይቀበል ገልጿል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ታጣቂው ቡድን በአፍሪካ ኅብረትና በሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች ከዋና ዋና የሐገሪቱ ከተሞች ተገፍቶ የወጣ ቢሆንም ዋና ከተማዋን ጨምሮ በሌሎችም ስፍራዎች ከፍተኛ ጥቃቶችን ከማድረስ ግን አልተገታም።
በብዛት በአሜሪካ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖች የሚደገፈው የሶማሊያ ሠራዊት በታጣቂው ቡድን ስር በሚገኙት የደቡባዊና ማዕከላዊ የሐገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ የሚባል ወታደራዊ ዘመቻን በቅርቡ ማካሄድ ጀምሯል።
















