ካስተር ሰሜኒያ የደቡብ አፍሪካን የእግር ኳስ ቡድን ተቀላቀለች

ካስተር ስሜንያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካስተር ስሜንያ ለመጀመሪያ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው ከ7 ዓመታት በፊት በተካሄደው የለንደን ኦሎምፒክ ነበር
ታትሟል

የሁለት ጊዜ የ800 ሜትር የኦሎምፒክ አሸናፊዋ ደቡብ አፍሪካዊቷ ሯጭ ካስተር ሰሜኒያ የደቡብ አፍሪካን የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ተቀላቀለች።

የ28 ዓመቷ አትሌት ሰሜኒያ ከፍተኛ 'ቴስቶስትሮን' የተሰኘው ሆርሞን ያላቸው ሴት ሯጮችን በተመለከተ የወጣውን ሕግ ተከትሎ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽን በውድድር ላይ እንዳትሳተፍ ተደርጓል።

ሕጉን በመቃወም ያቀረበችውን አቤቱታ የስፖርት የግልግል ዳኝነት ተቋም (ካስ) ውድቅ ካደረገባት በኋላ ወደ ስዊዘርላንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አምርታ እየተከራከረች ትገኛለች።

በ800 ሜትር ለአገሯ ደቡብ አፍሪካ ሦስት ጊዜ ወርቅ ያመጣችው ሰሜኒያ፤ በወርሃ መስከረም ዶሃ ላይ በሚካሄደው ውድድር ላይ እንደማትሳተፍም ታውቋል። ምክንያቱ ደግሞ "ለሴት አትሌቶች ከሚፈቀደው በላይ የቴስቴስትሮን ሆርሞን በውስጧ አለ" በመባሉ ነው።

በመሆኑም አሁን ላይ ከሩጫው ዓለም ወደ እግር ኳሱ ዘርፍ ጎራ ማለቷ ተሰምቷል።

ሰሜኒያ፤ ተቀማጭነቱን ደቡብ አፍሪካ ጓተንግ ያደረገውን JVW የተሰኘ የሴቶች እግር ኳስ ቡድንን በመቀላቀል ሥልጠና እየወሰደች ነው።

በቡድኑ ድረ ገፅ ላይም፤ "በአዲሱ ጉዞዬ እቀጥላለሁ፤ ቡድኑ ያሳየኝን ፍቅርና ያደረገልኝን ድጋፍ አደንቃለሁ" የሚለው አስተያቷ ሰፍሮ ይገኛል።

'JVW FC' የተሰኘው የእግር ኳስ ቡድን ከስድስት ዓመታት በፊት በደቡብ አፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን አምበል ጃናይን ቫን ውይክ የተቋቋመ ሲሆን፤ ዓላማው ሴት እግር ኳሰኞችን መመልመል፣ ማጎልበት እና ብቃት ያላቸውን ተጨዋቾች ማፍራት ነው።

ቡድኑ በጓተንግ ግዛት ታዋቂ ከሆኑ እግር ኳስ ቡድኖች አንዱ ነው።

የቡድኑ መስራች ጃናይን ቫን ውይክ፤ "ሰሜኒያ በሩጫው ፈፅሞ ተስፋ አልቆረጠችም" ብለዋል። አሁን ላይ እረፍት ላይ መሆኗንም በመግለፅ፤ በዚህ የእረፍት ጊዜዋ የተለየ ነገር ማድረግ ስለፈለገች ቡድኑን እንደተቀላቀለች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እንደ ቡድኑ መሪ ከሆነ ሰሜኒያ እስካሁን ሁለት የሥልጠና ዙሮች ላይ ተካፍላለች፤ ነገር ግን የሩጫ ዓለምና የእግር ኳስ ሜዳ ስለሚለያዩ ተጨማሪ ሥልጠናዎች ያስፈልጋታል።

"የእሷ ወደ እግር ኳሱ መምጣት ለቡድኑ በጣም ጠቃሚ ነው፤ በደቡብ አፍሪካ ለእግር ኳስ የሚሰጠው ክብር ከፍ እንዲል ያደርገዋል" ሲሉም ሰሜኒያ እግር ኳስ ስትጫወት ለቡድኑ አባላትና ለሌሎች ወጣት ሴቶች ተነሳሽነትን መፍጠር ትችላለች በማለት በእሷ ላይ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።

ሰሜኒያ የእግር ኳስ ቡድን የተቀላቀለች ብቸኛዋ ሯጭ አይደለችም፤ ከሁለት ዓመታት በፊት የዓለማችን የአጭር ርቀት ሯጭ ዩዜን ቦልት ኮንትራቱን ሳይፈራረም ቢቀርም በኖርዌያዊያን ቡድን ሥልጠና ወስዶ ነበር።

የሰሜኒያ የቀድሞ አሰልጣኝ ማሪያ ሙቶላም ወደ እግር ኳሱ ዓለም ተቀላቅለዋል።