አሜሪካዊቷ ተዋናይት ቫዮላ ዴቪስ ሚሼል ኦባማን ወክላ ልትተውን ነው

አሜሪካዊቷ ተወናይት ቫዮላ ዴቪስ 'ቀዳማዊ እመቤቶቹ' የተሰኘ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ የቀድሞዋን የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማን ወክላ ልትተውን መሆኑን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የኦስካር ተሸላሚዋ ተዋናይት የቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማን ገፀ ባህሪ ተላብሳ በታሪክ የነበሩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሚስቶችን በሚመለከተው 'ሾው ታይም' ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ልትተውን መሆኑ ተገልጿል።
የድራማው የመጀመሪያ ክፍሎች ሚሼል ኦባማ፣ ኢሌኖር ሩዝቬልት እና ቤቲ ፎርድ ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው።
በደራሲ አሮን ኮሌይ የተፃፈው ይህ ድራማ፤ የፕሬዚደንት ሚስቶች በግለሰብም ሆነ በፖለቲካ ሕይወታቸው ያላቸውን ሃሳብና የነበራቸውን አስተዋፅኦ እንዲያሳይ ሆኖ የተዘጋጀ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ቀዳማዊት እመቤቷ እና የሥራ ባልደረቦቿ በሚኖሩበት በዋይት ሃውስ ምስራቅ ክንፍ፤ ምን ያህል የፖለቲካ ውሳኔዎች እንዳለፉም ተዳሶበታል።
ሚሼል ኦባማ ከተዋናይት ቫዮላ ጋር በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ የመገናኘት እድል የነበራቸው ሲሆን ከሁለት ዓመታት በፊት ቫዮላ በፌስቡክ ገጿ ላይ ለሚሼል ያላትን ስሜት "አንፀባርቂ፤ የሚመጣው ትውልድም አስተዋፅኦሽን ይየው" ስትል በጋራ የተነሱትን ፎቶግራፍ ጨምራ አጋርታለች።
ተዋናይት ቫዮላ ከሁለት ዓመታት በፊት ለእይታ በበቃው 'ፌንስስ' በምርጥ ረዳት ተዋናይት ዘርፍ የኦስካር ተሸላሚ ነበረች። ከዚያም አስቀድሞ 'ዘ ኸልፕ'፣ 'ዊዶውስ'፣ እና 'ሱሳይድ ስኳድ' በሚሉት ፊልሞች ላይ ኮከብ ተዋናይት ሆና ሰርታለች።














