ቦይንግ የ737 ማክስ አውሮፕላኖች ትዕዛዝ ተሰረዘበት

ታትሟል

የሳዑዲ አረቢያው ርካሹ አየር መንገድ ፍላይኤዲል ከቦይንግ ሊገዛቸው ያቀዳቸውን 30 ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች መሰረዙ ተሰማ።

አየር መንገዱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው 346 ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡበትን፤ በኢንዶኔዥያና በኢትዮጵያ የተከሰከሱትን የ737 ማክስ አውሮፕላኖች አደጋ ተከትሎ ነው።

ቦይንግ ማክስ 737 አወሮፕላኖቹ እንዳይበሩ እገዳ ከተጣለበት በኋላ የአውሮፕላን መቆጣጠሪያ መሳሪያ ለማስተካከል እየሰራ እንደሆነ በተደጋጋሚ አስታውቋል።

ቦይንግ ፍላይኤዲል ከውሳኔው የደረሰው ቦይንግ ማክስ 737 የተስተዋለባቸው ችግር ተቀርፎ እስኪጠናቀቁ መጠበቅ በለመቻሉ ነው ብሏል።

አየር መንገዱ ሊገዛ ያቀዳቸው 20 ተጨማሪ 737 ማክስ አውሮፕላኖች በትንሹ 5.9 ቢሊን ዶላር የሚያወጡ የነበረ ሲሆን ለግዥውም ቅናሽ ተደርጎለት እንደነበረ ተገልጿል።

ባለቤትነቱ የመንግሥት የሆነው ፍላይኤዲል አየር መንገድ አሁን ፊቱን ወደ ኤርባስ ኤ 320 አዙሯል።

737 ማክስ አውሮፕላን በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ሁለት አደጋዎችን አስተናግዷል፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢቲ 302 አውሮፕላን ሁለተኛው ነው።

ከዚሁ አውሮፕላን ጋር ተመሳሳይ የሆነው የኢንዶኔዥያው ላየን ኤር በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2018 በጃካርታ ባህር ላይ መከስከሱም የሚታወስ ነው።

የአደጋ መርማሪዎች ምርመራቸውን በአውሮፕላኑ የመቆጣጠሪያ ስርዓት ላይ ትኩረት ያደረጉ ሲሆን ቦይንግ መቆጣጠሪያ መሳሪያውን ሶፍት ዌር ለማሻሻል ጥረት እያደረኩ ነው ብሏል።

737 ማክስ አውሮፕላኖች መቼ ለበረራ ዝግጁ እንደሚሆን ግን የተቀመጠ የጊዜ ገደብ የለም።

ባሳለፍነው ሳምንት ቦይንግ በሁለቱ አደጋዎች ለተጎዱ ቤተሰቦች የ100 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አድርጌያለሁ ሲል አስታውቋል።

ድጋፉ በሁለቱም አደጋዎች ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች እንደሚሆን ቢያስታውቅም የተጎጂ ቤተሰቦች እና ጠበቃዎች ግን ድጋፉን ተቃውመውታል።