በተወለደች በሳምንት ውስጥ በኢቦላ የተጠቃችው ጨቅላ ህይወቷ ተረፈ

ታትሟል

ኢትዮጵያ

• የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ በአፍሪካና አውሮፓ ህብረት ፎረም ላይ ለመሳተፍ ወደ ኦስትሪያ አቀኑ።

በነገው እለት በሚካሄደው ፎረም ፕሬዚዳንቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የዲጂታል ቴክኖሎጅ የተመለከተ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

• በጉራጌ ዞን ማረቆና መስቃን አካባቢ ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ አመራሮችንና ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው።

የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እንዳስታወቀው የማረቆ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በለጠ ደራሮንና የመስቃን ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሚፍታህ ሸምሱን ጨምሮ ሌሎች ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ዲሞክራቲክ ኮንጎ

• በዲሞክራቲክ ኮንጎ በተወለደች በሳምንት ውስጥ በኢቦላ የተጠቃች ልጅ ህይወቷ መትረፉ ተገለጸ።

ለተከታታይ አምስት ሳምንታት ያልተቋረጠ ህክምና የተከታተለቸው ህጻን፤ ነጻ ተብላ ወደ ቤቷ ተወስዳለች።

ግብጽ

• በግብፅ ቄሶች ያረፉበትና ላለፉት 4400 ዓመታት ተነክቶ የማያውቅ መካነ መቃብር በአርኪዮሎጂስቶች ተገኘ።

መካነ መቃብሩ በቀለማት ያሸበረቁ ሥዕላዊ መግለጫዎች፣ የፈርኦን ሐውልቶችና ሌሎች ምስሎች የተሞላ ነው ተብሏል።

ካምቦዲያ

• ካምቦዲያ ከአፍሪካዊቷ ሃገር ሞዛምቢክ የመጣ ከ3.2 ቶን በላይ የሚመዝን የዝሆን ጥርስ መያዟን አስታወቀች።

1026 የሚሆኑትን የዝሆን ጥርሶቹ ወደብ ላይ መያዝ የተቻለው ከአሜሪካ ኤምባሲ በደረሳቸው ጥቆማ ነው።

ህንድ

• ህንዳውያን አንዲት ተማሪ በደቦ የተደፈረችበት ስድስተኛ ዓመት ለማስታወስ በወጡበት ሌላ የሶስት ዓመት ህጻን መደፈሯ ተሰምቷል።

ጥቃት አድራሹ የ40 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን፤ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ ተጀምሯል።

ሳዑዲ አረቢያ

• ሳዑዲ በየመን እያደረገች ላለችው ጦርነት አሜሪካ የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ እንድታቆም ሴኔቱ መወሰኑን አወገዘች።

የሳዑዲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሴኔቱን ውሳኔ እውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተና ጣልቃ ገብነት የታየበት ብለውታል።

እስራኤል

• የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ወንድ ልጅ ስለ ፍልስጤማውያን ባስተላለፈው መልዕክት ምክንያት ከፌስቡክ ለ24 ሰአት ታገደ።

ባለፈው ሳምንት በፍልስጤማውያን የተገደሉ እስራኤላውያን ወታደሮች ደም ማስመለስ አለብን ብሎ ጽፎም ነበር።

ሃንጋሪ

• ሃንጋሪ ውስጥ አዲሱን የሰራተኞች ህግ ለመቃወም ወደ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሄዱ የፓርላማ አባላት ተጎትተው እንዲወጡ መደረጉ አነጋጋሪ ሆኗል።

ድርጊቱን የተቃወሙ ሌሎች የፓርላማው አባላት ደግሞ በቴሌቪዥን ጣቢያው አካባቢ በመሰባሰብ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

ብራዚል

• ብራዚል ውስጥ 300 ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት በመፈጸም የተጠረጠረ ሃይማኖታዊ መሪ እጁን ለፖሊስ ሰጠ።

ሰውዬው ሃይማኖታዊ ፈውስስ እሰጣለው በማለት ጥቃት እንዳደረሰባቸው ተጎጂ ሴቶቹ ለፖሊስ ተናግረዋል።