የአሜሪካ፣ የቻይናና የሩሲያ ፉክክር በአፍሪካ ላይ

ጆን ቦልተን

የፎቶው ባለመብት, AFP/GETTY

ታትሟል

ቻይናና ሩሲያ አፍሪካ ውስጥ ግልጽ ያልሆነ እና ከሙስና ጋር የተያያዘ ዘዴን በመጠቀም ተጽዕኗቸውን ለማስፋት እየሰሩ ነው ስትል አሜሪካ ከሰሰች።

የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የሆኑት ጆን ቦልተን እንደተናገሩት ሁለቱ ሃገራት በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ከአሜሪካ አንጻር በኢኮኖሚ ረገድ የበላይነትን ለመያዝ "ሆን ብለው ሌት ተቀን" ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል።

አማካሪው ጨምረው እንደገለጹት የትራምፕ አስተዳደር ለአፍሪካ ያዘጋጀው አዲስ ዕቅድ በንግድና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ላይ ትኩረትን የሚያደርግ ይሆናል።

"በአዲሱ ዕቅዳችን መሰረት የምንወስነው እያንዳንዱ ውሳኔዎች፣ የምንከተላቸው ሁሉም ፖሊሲዎች እና ለእርዳታ የምናወጣው እያንዳንዱ ዶላር አሜሪካን በአህጉሪቱ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ጉዳዮች የሚያሳኩ ይሆናሉ" ሲሉ በዋሽንግተኑ ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን ውስጥ ባደረጉት ንግግር ገልፀዋል።

ጆንቦልተን ቻይናን "ጉቦ በመስጠት፣ ግልጽነት በሌላቸው ስምምነቶችና ብድርን ሃገራት ለፍላጎቷና ለጥያቄዎቿ ተገዢ እንዲሆኑ ማስገደጃ አድርጋለች" ሲሉ ከሰዋል።

ቻይና በጂቡቲ ላይ ያላትን ተጽእኖ ጠቅሰው፤ ይህም አሜሪካ ጂቡቲ ውስጥ ባላት ጦር ሰፈር ላይ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ያለውን የንግድ ግንኙነት ሚዛን ወደ ምሥራቅ በማዞሩ በኩል ቀጥተኛ ተጽእኖ አለው።

ሩሲያን በተመለከተም ለህግ፣ ለተጠያቂነትና ለግልጽ አስተዳደር ትኩረት በማይሰጥ ሁኔታ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በመፍጠር የተጽእኖ አቅሟን ከፍ ለማድረግ እየጣረች ነው ብለዋል።

"ሩሲያ በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ ለምታገኘው የድምጽ ድጋፍ ስትል የጦር መሳሪያ መሸጥንና የኃይል አቅርቦትን ቀጥላለች" በተጨማሪም "ከአህጉሪቱ የተፈጥሮ ሃብትን እራሷን በሚጠቅም ሁኔታ እየወሰደች ነው" ብለዋል።