በኢትዮጵያ የተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሆነ

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የማህበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን በቫይረሱም የተያዙም ሰዎች ከ57 ሺህ በልጧል። በትናንትናው ዕለት ለ24 ሺህ 544 ሰዎች በተደረገው ምርመራ 950 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። በዚህም መሰረት በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 57 ሺህ 466 ደርሷል። ከነዚህም ውስጥ 20 ሺህ 776 ያገገሙ ሲሆን 897ቱ ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል። አገሪቷ በአጠቃላይ ያከናወነችው ላብራቶሪም ከአንድ ሚሊዮን በልጧል። የቫይረሱን ስርጭት አካሄድ የሚከታተሉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የወረርሽኙ ስርጭት ከመረጋጋት ይልቅ እየጨመረ በመሆኑ፣ አሁንም ጥንቃቄ መልዕክቶቹ በአግባቡ ተግባራዊ መሆን አለባቸው። አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ አፍና አፍንጫን መሸፈን እንዲሁም እጅን በሚገባ በሳሙናና በውሃ መታጠብ ከጥንቃቄ መልዕክቶቹ መካከል ይገኙበታል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የሶሪያ ሃኪሞች በኮቪድ-19 ቁስ እጥረት ህይወታቸው እያለፈ ነው ተባለ

    ሂዩማን ራይትስ ዎች የተሰኘው የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት በሶሪያ መንግሥት ይዞታ ስር በሚገኙ አከባቢዎች የሚያገለግሉ የጤና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ አቅርቦት እጥረት ለበሽታው እየተጋለጡ መሆኑን አስታወቀ።

    ሂዩማን ራይትስ ዎች ጨምሮ እንዳለው በበሽታው ምክንያት ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የጤና ባለሙያዎች ህይወታቸው አልፏል።

    ድርጅቱ ያነጋገራቸው የጤና ባለሙያዎች እንዳሉት ከሆነ የሆስፒታል አልጋዎች በኮቪድ-19 በተያዙ ታማሚዎች ተጨናንቀዋል።

    የሶሪያ መንግሥት በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2800፣ በበሽታው የሞቱ ሰዎች አሃዝ ደግሞ 116 ነው ይላል።

    ሂዩማን ራይትስ ዎች ግን በሶሪያ በቫይረሱ የተያዙ እና የሞቱ ሰዎች ቁጥር መንግሥት ከሚለው በብዙ እጥፍ እንደሚበልጥ ይናገራል።

    ድርጅቱ ባለፉት 4 ወራት ብቻ 33 ዶክተሮች የኮቪድ-19 ምልክት ባለው ሕመም ህይወታቸው አልፏል ብሏል።

  2. የኬንያ አየር መንገድ በዓለም ላይ ላሉ የጤና ሰራተኞች በግማሽ ቅናሽ አደረገ

    በዓለም ላይ ያሉ የጤና ሰራተኞች ወደ የትኛውም አገር በኬንያ አየር መንገድ የሚጓዙ ከሆኑ መክፈል የሚጠበቅባቸው ግማሹን መሆኑን አየር መንገዱ አስታውቋል።

    ቅናሹ በኢኮኖሚም ሆነ በቢዝነስ ደረጃ ለሚጓዙ የጤና ሰራተኞች ሲሆን ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ የሰውን ልጅ ህይወት ለማትረፍ ቀን ተሌት በማለት እየተጋፈጡ ላሉት የጤና ባለሙያዎች ምስጋና ለመቸር በማሰብ ቅናሽ እንዳደረገ አየር መንገዱ አስታውቋል።

    አየር መንገዱ በወረርሽኙ ምክንያት በባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 133 ሚሊዮን ዶላር እንደከሰረም ከሰሞኑ ተገልጿል።

    ከወረርሽኙ በተጨማሪ በቀጠናው በገጠመው ፉክክርና ሌሎች ችግሮች መንግሥት የተወሰኑትን አውሮፕላኖችም ከስራ ውጭ ለማድረግ ተገዷል።

    ከገጠመው ቀውስና እዳ እንዲወጣም በማለት የኬንያ ፓርላማ አባላት አየር መንገዱ በመንግሥት ባለቤትነት ስር እንዲሆን ውሳኔ ያስተላለፉት በባለፈው ወር ነበር።

  3. አሜሪካ በዓለም ጤና ድርጅት በሚመራው የክትባት ፍለጋ አትሳተፍም

    የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ በዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት በሚመራው የኮሮረናቫይረስ ክትባት የማግኘትና ከተገኘ በኋላ የማከፋፈል ስራ ላይ እንደማትሳተፍ ጠቁሟል።

    ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ እንደዘገበው የዋይት ሃውስ ባለስልጣናት 172 አገራት በሚሳተፉበትና የዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ድርጅት በበላይነት በሚያስተባብረው ስራ ላይ መሳተፍ አይፈልጉም።

    '' አሜሪካ ቫይረሱን ለማሸነፍ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ከዓለም አቀፍ ወዳጆቿ ጋር በትብበብር ትሰራለች፤ ነገር ግን በዓለም ጤና ድርጅት እና ቻይና በሚዘወር እንቅስቃሴ ላይ አትሳተፍም'' ብለዋል የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ጁድ ድሪ።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ቢሆኑ ከቫይረሱ ስርጭትና እርምጃዎች ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የዓለም ጤና ድርጅትን ሲተቹ ተደምጠዋል።

  4. ዚምባብዌ በሁለት ሳምንት ውስጥ ትምህርት ቤቶችን ልትከፍት ነው

    የዚምባብዌ መንግሥት በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ትምህርት ቤቶች እንደሚከፈቱና በዓመቱ መጨረሻ ላይ ደግሞ ተማሪዎች ለብሄራዊ ፈተና እንደሚቀመጡ አስታወቀ።

    'ካምብሪጅ' ለሚባለው ፈተና የሚቀመጡ ተማሪዎች በፈረንጆቹ መስከረም 14 ወደ ትምህርት ቤት ይመለሳሉ ተብሏል።

    ለዚምባብዌ ትምሀርት ቤት ፈተናዎች የሚቀመጡ ተማሪዎች ደግሞ መስከረም 18 ትምህርታቸው የሚጀምሩ ሲሆን ፈተናውን ደግሞ ታህሳስ ወር ላይ እንደሚወስዱ ተጠቁሟል።

    መንግሥት ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ከትምህርት ኃለፊዎችና የጤና ባለስልጣናት ጋር ምክክር ካደረገ በኋላ መሆኑም ተገልጿል።

    የዚምባብዌ መረጃ ሚኒስትሯ ሞኒካ ሙትስቫንግዋ እንዳሉት ሁለቱ ሳምንታት በትምህርት ቤቶች የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚረዱ እርምጃዎችን ለመውሰድ በቂ ናቸው።

    ዚምባብዌ እስካሁን 6 ሺህ 559 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን አግኝታለች።

  5. ኮቪድ-19 ያሰናከለው ምርጫና ያልተረጋጋው የኢትዮጵያ የፖለቲካ

  6. በኮሮናቫይረስ የተያዘችው ስደተኛ ሄሊኮፕተር ውስጥ ልጇን ተገላገለች

  7. ናንሲ ፔሎሲ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ ታዩ

    በዴሞክራቶች ቤት ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውና ዶናልድ ትራምፕ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ባለማድረጋቸው ሲተቹ የሚሰሙት ናንሲ ፔሎሲ የሴቶች ውበት ሳሎን ውስጥ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ ታይተዋል።

    ፎክስ ኒውስ ባገኘው ምስል መሰረት የሕዝብ እንደራሴ አፈጉባኤዋ የከተማዋን የኮሮረናቫይረስ መከላከያ ሕግ በመጣስ ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ።

    የሳን ፍራንሲስኮ ወረርሽኝ ትዕዛዝ እንደሚለው ደንበኞችም ሆነ አገልግሎት ሰጪዎች በውበት ሳሎኖች ውስጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታቸው ነው።

    ናንሲ ፔሎሲም በውበት ሳሎኑ ውስጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛቸውን ከፊታቸው ላይ በማውረድ አንገታቸው ላይ አድርገውት ታይተዋል።

    ከክስተቱ በኋላም የከተማዋን ሕግ መጣሳቸውን እንዳለስተዋሉ ገልጸዋል።

  8. እንደምን አደራችሁ

    እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ አማርኛ ቤተሰቦች

    ቢቢሲ አማርኛ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተገናኙ የአገር ውስጥ እና ዓለማቀፍ ዜናዎችን ወደናንተ የሚያደርስበት የቀጥታ ዘገባው አሁን ተጀመረ።

    በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ከ900 ሺህ በላይ ናሙናዎች ላይ የኮቪድ-19 ምርመራ የተደረገ ሲሆን በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 53 ሺህ 304 ደርሷል።

    አብራችሁን ቆዩ።