በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት የ2012 ምርጫ መራዘሙ ተገለፀ

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ አገራት የተለያየ እርምጃ እየወሰዱ ነው። የአየርም ሆነ የብስ ድንበሮቻቸው የዘጉ፣ ከተሞቻቸውን ከእንቅስቃሴ ያቀቡ እንዲሁም ሰዓት እላፊ የጣሉ አገራት በርካቶች ናቸው። ሁሉም ቢሆኑ በአንድ ድምጽ ስለ ወረርሽኙ መከላከያ ሲናገሩ የሚደመጠው አካላዊ ርቀትንና፣ የግል ንጽህናን መጠበቅ እንዲሁም የበሽታው ምልክት የሚታይባቸው ሰዎች ራሳቸውን ለይተው እንዲያቆዩ ነው። ዓለም በአሁኑ ሰዓት 33 ሺህ ያህል ዜጎቿን በኮቪድ-19 ምክንያት አጥታለች። ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ከዓለም ዙሪያ የምናሰባስባቸውን ዘገባዎች በቀጥታ እናቀርብላችኋለን።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ሰበር, በድሬዳዋ አንድ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ተገኘ

    የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ ኮቪድ-19 እንደተገኘበት እና ይህም በአጠቃላይ በአገሪቱ ቫይረሱ የተገኘባቸውን ሰዎች ቁጥር ወደ 26 ከፍ እንዳደረገው አስታውቋል።

    ቫይረሱ እንዳለበት የተረጋገጠው ግለሰብ የ42 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን ከአውስትራሊያ አዲስ አበባ ከዚያም ወደ ድሬዳዋ የሄደ መሆኑ ተገልጿል።

    በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ያሉ ሃያ ሁለት (22) ታማሚዎች ሲኖሩ ሁለት ታማሚዎች በጽኑ ህሙማን ህክምና ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

  2. የኪነጥበብ ባለሙያዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በሕክምና ባለሙያዎች የሚነገሩ መልዕክቶችን በጥበብ አዋዝተው ወደ ሕብረተሰቡ ያደርሳሉ።

    ከዚህ በፊትም የጃኖ ባንድ አባላት፣ ኮሜዲያን ቶማስ፣ ተዋናይት ማህደር አሰፋ፣ ድምጻዊ ልጅ ሚካዔል እና ሌሎች በርካቶች መልዕክታቸውን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ለአድናቂዎቻቸው አድርሰዋል።

    አሁንም በጤና ጥበቃ የፌስቡክ ገጽ ላይ ይህንን መልዕክት አግኝተናል። ትወዱታላችሁ ብለን እናምናለን።

    ከምንም በላይ ራሳችንን ከኮሮናወረርሽኝ ለመከላከል እጃችንን መታጠብ፣ በምናስነጥስበትና በምናስልበት ወቅት አፍንጫችንን መሸፈን እንዲሁም አካላዊ ርቀታችንን መጠበቅ አንርሳ!

    ጤና እንክረም!

  3. ሰበር, የ2012 ምርጫ በተያዘለት ጊዜ እንደማይካሄድ ተገለፀ, የ2012 ምርጫ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በተያዘለት ጊዜ እንደማይካሄድ ተገለፀ

    ሰበር ዜና

    በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ለነሐሴ ሊካሄድ ታስቦ የነበረውን ምርጫ ለማካሄድ እንደማይችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳወቀ::

    የምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫውን ማካሄድ የማይቻለው መሆኑን በመረዳት ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ በመሰረዝ በሰሌዳው መሰረት መከናወን ያለባቸው ተግባራት ለጊዜው እንዲቆሙ መወሰኑን በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

    ምርጫ ቦርድ አውጥቶት በነበረው የጊዜ ሰሌዳ ምርጫው ለነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ተቆርጦ የነበረ ቢሆንም የመራጮች ምዝገባ፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላ፣ ስልጠናና ስምሪት የመሳሰሉት ተግባራት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ለማቋረጥ መገደዱን አስታውቋል።

    እነዚህ ተግባራት በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ቀድመው መከናወን ቢጠበቅባቸውም በዓለምም ሆነ በኢትዮጵያ ባጠላው የቫይረሱ ስጋት መከናወን ሳይችሉ ቀርተዋል ብሏል።

    ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳለው በተያዘው የጊዜ ሰሌዳው መሰረት ሥራዎችን ለማከናወን ጥረት እያደረገ በሚገኝበት ወቅት ባለፉት ሳምንታት በአገራችንና በዓለም ላይ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንቅስቃሴዎች እንዲቋረጡ ማስገደዱን አመልክቷል።

    የተለያዩ አገራትም ምርጫዎቻቸውን እንዲሁም ሌሎች ትልልቅ ዝግጅቶቻቸውን ለመሰረዝ መገደዳቸውን በመጥቀስ ኢትዮጵያም ይህንኑ ለመከተል መገደዷን ገልጿል።

    የኮሮናቫይረስ ስጋት በቀጣዩ ሚያዝያ ወር ሊጀምር የታቀደው የመራጮች ምዝገባና ሌሎችም ዝግጅቶች ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንዲሁም ጫና ማሳደሩን የጠቀሰው የቦርዱ መግለጫ ለዚህም ማሳያ የሆኑትን ምክንያቶች ያለቸውን ጠቅሷል።

    የኮሮናቫይረሱ መከሰትን ተከትሎ መንግሥት አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ የመንግሥት ሰራተኞቸ ከቤት ሆነው እንዲሰሩ መደረጋቸውና ክልሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ጨምሮ የትራንስፖርት እንዲሁም የመሰብሰብ ገደቦች መጣላቸውን ከምክንያቶቹ ውስጥ አካቷል።

    ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ለቦርዱ ድጋፍ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ሰራተኞቻቸው ከቤት እንዲሰሩ መደረጋቸው ምርጫ ቦርድ ሊያከናውናቸው ካሰባቸው ተግባራት ላይ ጫና ማሳደራቸውን መግለጫው አትቷል።

    ምርጫ ቦርዱ ምርጫው መቼ ሊካሄድ እንደታሰበ ቁርጥ ያለ ቀን ባያስቀምጥም የወረርሽኙ ስጋት ተወግዶ ሁኔታዎች ሲመቻቹ ግምገማ በማካሄድ አዲስ የጊዜ ሰሌዳ እንደሚያወጣም አስታውቋል።

    የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በውሳኔው ላይ ያደረገውንም የዳሰሳ ጥናትና ሰነድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑንም ገልጿል።

  4. የአማራ ክልል ከ7 ሺህ በላይ እስረኞችን በይቅርታ ሊለቅ ነው

    በአማራ ብሔራዊ ክልል መንግስት የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ መስሪያ ቤት ዓርማ

    የፎቶው ባለመብት, ANRS Attorney General

    የአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚል ከሰባት ሺ በላይ እስረኞች በይቅርታ እንዲፈቱ መወሰኑን የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዓለምሸት ምህረቴ ገለፁ።

    በይቅርታ እንዲፈቱ የተወሰነላቸው ግለሰቦች ከሰው ግድያ ውጪ በሆኑ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው የነበሩ ናቸው።

    በዚህም መሰረት በይቅርታው የተካተቱት የሚያጠቡ እናቶች፣ በአመክሮ የመፈቻ ጊዜያቸው የተቃረበና ቀላል ወንጀል የፈፀሙ ታራሚዎች ይገኙበታል።

    ከዚህም በተጨማሪ የሌሎች አገራት ዜጎች ሆነው ከሰው መግደል ውጪ በሆኑ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው በመታረም ላይ የሚገኙ ግለሰቦችም ይቅርታ እንሚደረግላቸው ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

  5. የአማራ ክልል ባህርዳርን ጨምሮ አራት ከተሞች እንዲዘጉ ወሰነ

    የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ያደረገ ወጣት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአማራ ክልል ነዋሪ የሆኑ ሁለት ግለሰቦች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ ክልሉ አራት ከተሞች እንቅስቃሴያቸው እንዲገደብ ተወስኗል።

    በዚህም መሰረት ከመጋቢት 23፣ 2012 ዓ.ም ከ6፡00 ሰዓት ጀምሮ በባህርዳር፣ በአዲስ ቅዳም፣ እንጅባራ፣ ቲሊሊ ከተሞች ለ14 ቀናት ያህል የህዝብም ሆነ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ የክልሉ የኮሮና ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ኮማንድ ፖሰት መወሰኑን የአማራ ኮሙዩኒኬሽን በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

    መግለጫው አክሎም ሁኔታዎች የሚባባሱ ከሆነም የጊዜ ገደቡም እንደሚራዘም ገልጿል።

    በነዚህ ከተሞች ውስጥ መንቀሳቀስ የሚችሉት ግለሰቦችና ተሽከርካሪዎች የድንገተኛ የጤና አገልግሎት ሰጭ እና ወረርሽኙን ለመከላከል የተሰማሩ የግብረ ኃይልና የቴከኒክ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የተፈቀደላቸው በጎ ፈቃደኞችም መሆናቸውም ተገልጿል።

    የክልሎ ኮማንድ ፖስት እንቅስቃሴያቸው በታገደባቸው አራቱ ከተሞች እርዳታ ለሚሹ ወገኖች የምግብ እርዳታ በሚያሰባስበው ግብረ ኃይልና የበጎ ፈቃደኛ አባላት አማካኝነት በኩል የሚችሉትን ያህል እርዳታ እንዲለግሱም ለነዋሪዎች ጥሪ አቅርቧል።

    ለህዝቡ መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ የደረቅና የፈሳሽ የጭነት ተሽከርካሪዎች እለታዊ ተግባራቸው እንደሚቀጥል እንዲሁም ከፀጥታ፣ ከውሃ እና መብራት ጋር በተያያዘ የሚንቀሳቀሱ አካላት መደበኛ ተግባራቸውን ለማከናወን ኮማንድ ፖስቱ ፈቃድ እንደሚሰጥ አስታውቋል። ሆኖም እንቅስቃሴያቸው በተገደበባቸው አራቱ ከተሞች አልፈው የሚሄዱ ተሽከርካሪዎች ማራገፍም ሆነ መጫን ክልክል መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ ገልጿል።

    በሌሎች የክልሉ ከተሞች እንዲሁ ተመሳሳይ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል የጠቆመው መግለጫው፤ ይህንነን ውሳኔ ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም አካል ሆነ ግለሰብ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድበት ኮማንድ ፖስቱ አፅንኦት ሰጥቷል።

    በቫይረሱ የተያዙት ግለሰቦች በአማራ ክልል በባሕርዳር ነዋሪ የሆኑ የ37 ዓመት ሴትና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የአዲስ ቅዳም ነዋሪ የሆኑ የ32 ዓመት ወንድ መሆናቸውም ተገልጿል።

  6. በኬንያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለማስከበር የተጣለ ሰዓት እላፊን ለማስከበር በተተኮሰ ጥይት አንድ ታዳጊ ሞተ

    በኬንያ ከመሸ በኋላ መንቀሳቀስ የሚከለክለውን የሰዐዓት እላፊ ለማስከበር የፖሊስ አባላት ተንቀሳቅሰዋል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኬንያ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት የተጣለውን ሰዓት እላፊ ባላከበሩ ሰዎች ላይ በተተኮሰ ተባራሪ ጥይት የ13 ዓመት ታዳጊ መሞቱ ተሰማ።

    በኬንያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት በሚል መንግሥት ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ ንጋቱ 11 ሰዓት ድረስ የሚዘልቅ የሰዓት እላፊ የጣለው ባለፈው ሳምንት ሲሆን ይህንንም ለማስከበር የፀጥታ አካላት ታዝዘዋል።

    ይሁን እንጂ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ እና ሌሎች ከተሞች ግን ዜጎች ይህንን የሰዓት እላፊ በተደጋጋሚ ሲጥሱ ታይተዋል።

    ፖሊስ የሰዓት እላፊውን ባላከበሩ ዜጎች ላይ አስለቃሽ ጋዝና ጥይት በተደጋጋሚ ሲተኩሰ የታየ ሲሆን አሻፈረኝ ያሉም በፖሊስ ዱላ ተደብድበዋል።

    ሰኞ ዕለት ማታ ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት የሞተው የ13 ዓመቱ ታዳጊ በቤቱ በረንዳ ላይ እየተጫወተ ነበር ተብሏል።

    ፖሊስ ወደ ቤታቸው አልገባ ባሉ ነዋሪዎች ላይ ጥይት በመተኮሱ ሆዱ ላይ በጥይት የተመታው ታዳጊ፣ ሆስፒታል ተወስዶ ሕክምና እየተደረገለት መሞቱ ተሰምቷል።

    የኬንያ ፖሊስ አዛዥ ግድያው እንዲጣራ ያዘዙ ሲሆን በአካበቢው የሰዓት እላፊውን ለማስከበር በተሰማሩ የፖሊስ አባላት ላይ ምርመራ ተጀምሯል ብለዋል።

  7. የታንዛኒያ የሕዝብ እንደራሴዎች የምክር ቤት ስብሰባውን በቪዲዮ ሊካፈሉ ነው

    በዳሬሰላም ሆስፒታል የሚመጡ ታካሚዎች እጃቸውን በሳኒታይዘር እንዲያጸዱ ይደረጋል

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የታንዛኒያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮሮናን ወረርሽኝ አስመልክቶ አዳዲስ መመሪያዎችን ለሕዝብ እንደራሴ አባላቱ አስተዋውቋል።

    ምክር ቤቱ ባወጣው መመሪያ ከ150 አባላት በላይ በአንድ ስብሰባ ላይ መሳተፍ እንደማይቻል ተገልጿል።

    በምክር ቤቱ የማይገኙ ስብሰባውን በኢንተርኔት በቀጥታ በታብሌታቸውና በቪዲዮ ኮንፍረንስ መከታተል ይችላሉ ተብሏል።

    የምክር ቤቱ አፈጉባዔ የሆኑት ጆብ ንዱጊ ለቢቢሲ እንደገለፁት ምክር ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ በሚል ነው።

    አፈ ጉባኤው አክለውም አንዳንዴ በምክር ቤቱ እስከ 700 ሰዎች እንደሚገኙ አስታውሰው በዚህ ወቅት አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ የኮሮናቫይረስን መከላከል እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል።

    ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሕዝብ እንደራሴዎች በምክር ቤቱ ውሳኔ ተደስተዋል።

    የታንዛኒያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 394 አባላት አሉት።

  8. በቫይረሱ የተያዙ ግለሰቦች ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሰዎችን ለመለየት ክትትል እየተደረገ ነው-አማራ ክልል

    ባህር ዳር

    የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በትናንትናው ዕለት ባደረገው 66 ተጨማሪ ምርመራ ሁለቱ በኮሮና ቫይረስ የተያዙት ግለሰቦች በአማራ ክልል ነዋሪ መሆናቸውን አስታውቋል።

    ይህንንም ተከትሎ ከታማሚዎቹ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዲሁም ንክኪ ይኖራቸዋል ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎችን የመለየትና የክትትል ሂደት እየተከናወነ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ ገልፀዋል።

    በቫይረሱ የተያዙት ግለሰቦች በአማራ ክልል ባሕር ዳር ነዋሪ የሆኑ የ37 ዓመት ሴትና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የአዲስ ቅዳም ነዋሪ የሆኑ የ32 ዓመት ወንድ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውም ተገልጿል።

    ግለሰቦቹ መንግሥት ያዘዘው የአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ከመጀመሩ ዕለት አስቀድሞ ከዱባይ እና ከአሜሪካ የገቡ ሲሆን፤ የበሽታውን ምልክት ማሳየታቸውን ተከትሎ ምርመራ ተደርጎላቸዋል፤ በምርመራው መሰረትም መያዛቸው ተረጋግጧል ብሏል።

    የዚህን ዜና ዝርዝር ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ

  9. የአውሮፓ አገራት እንደምን አርፍደዋል?, በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተጠቁት የአውሮፓ አገራት እንደምን አርፍደዋል?

    አዛውንቱ በአውሮፓ ጎዳናዎች

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ጣሊያን- በጣሊያንበኮሮና ቫይረስ ህይወታቸውን ያጡትን ሺዎችን በማሰብ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረግ፤ እነርሱን የማሰብ ሥነ ሥርዓትም ተከናውኗል፡፡ በጣሊያን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመጠኑ ለመቀነሱ የእንቅስቃሴ ገደቡ ውጤት ሳይሆን እንዳልቀረ ባለስልጣናቱ ተስፋ አድርገዋል።

    ሰኞ ዕለት የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው አጠቃላይ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 648 ሲሆን ከትናንት በስቲያ ግን ቁጥሩ 3 ሺህ 815 ነበር። ምንም እንኳን የሟቾች ቁጥር ከትናንት በስቲያ 756፤ ትናንት ደግሞ 812 በመሆን ቢጨምርም።

    በአገሪቷ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብም ለመጭዎቹ 11 ቀናት ያህል ይቀጥላል።

    ጀርመን-የጀርመኗ ምስራቃዊ ከተማ፤ የና- ከተማዋ ሰዎች በገበያ ቦታዎችና ሱቆች፣ እንዲሁም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሲጠቀሙ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) እንዲያደርጉ ወስናለች። ኦስትሪያም ሰዎች በሱፐር ማርኬቶች ማስክ እንዲያደርጉ አሳስባለች።

    ልክ እንደ ሌሎች የአውሮፓ አገራት ጀርመንም የማስክ እጥረት አጋጥሟታል፤ የህክምና ጉዳዮችንም ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች ነው። ምንም እንኳን የጤና ባለሙያዎች በቀላሉ የሚዘጋጁ ማስኮች የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ ነው ቢሉም፣ የና ግን ህዝቦቿ የራሳቸውን ማስክ እንዲሰፉ አሳስባለች።

    ሮበርት ኮች ኢንስትቲዩት እንዳስታወቀው በጀርመን በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 600 ደርሷል፤ የሟቾቹ አማካይ እድሜም 80 ነው።

    የሟቾች ቁጥር 650 ነው ተብሎ የተገመተ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል 31 የሚሆኑት እድሜያቸው ከ60 በታች እንደሆነ ተጠቅሷል።

    በአገሪቷ ባቫሪያ እና ሰሜናዊ ርሂን ዌስትፓሊያ ክፉኛ በቫይረሱ የተጠቁ ግዛቶች ናቸው።

    ስፔን- የስፔን ጤና ሚኒስቴር በ24 ሰዓታት ውስጥ የሟቾች ቁጥር 849 መሆኑን አስታውቋል፤ ይህም በአገሪቷ ከተመዘገበው ከፍተኛው ነው። እሁድ ዕለት የነበረው ከፍተኛው ቁጥር 838 ነበር። በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ከቻይና በልጦ 94 ሺህ 417 ደርሷል።

    በዚህም የተነሳ ጽኑ ህሙማንን ክፉኛ በቫይረሱ ከተጠቁት ማድሪድና እና ካታሎኒያ ግዛቶች ወደ ሌሎች የስፔን ክፍል ለመውሰድ እቅድ እንዳለ ተገልጿል።

    ኔዘርላንድስ- በኔዘርላንድስ የእንቅስቃሴ ገደቡን ተከትሎ ዘራፊዎች አጋጣሚውን እየተጠቀሙበት ነው ተብሏል። በስነጥበብ ወዳጆች ዘንድ ስመጥር የሆነውን ሰዓሊ የቫን ጎህ የሥዕል ሥራ ላረን ከሚገኘው ጋለሪ ተሰርቋል፡፡ የሥዕል ሥራው 6 ሚሊየን ዩሮ ያወጣል ተብሎ ይገመታል።

  10. ንቀው ሊተዋቸው የሚገቡ የተሳሳቱ አመለካከቶች

    የላም ሽንት እንደ መድሃኒት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደ አገሩ ባህልና ልማድ በኮሮናቫይረስ ላለመያዝ ወይም ለመከላከል ይረዳሉ በሚል የተለያዩ ሃሳቦች በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲንሸራሸሩ ይስተዋላል።

    ኢትዮጵያም ውስጥ ቢሆን አረቄ፣ ሎሚ መጠጣት፤ ነጭ ሽንኩርት፣ ዝንጅብልና ፌጦን እንደ መከላከያ እንዲሁም የኮሮና መድሃኒት ነው እየተባለም ሲነገር ተሰምቷል። ቢቢሲ በተለያየ ማህበረሰቦች ዘንድ የሚነገሩ አፈ ታሪኮችን (የተሳሳቱ እምነቶችን) በመቃረም ሰብስቧል። እስቲ ጥቂቶቹን እነሆ !

    ትንፋሽን መያዝ- ትንፋሻችሁን ለ10 ሰከንድ ሳትጨነቁ መያዝ ከቻላችሁ ሳምባችሁ ላይ የህብረ ህዋስ (ቲሹ) መጎዳት አልያም የሳምባ ችግር እንደሌለባችን ማረጋገጫ ነው ይባላል። ይህ ግን ስህተት ነው። 10 ሰከንድ ያለምንም ችግር ትንፋሽን መያዝ መቻል የሳንባ ጤንነታችን መፈተሻ አይደለም። የሳንባ እክል የኮቪድ-19 ምልክት አይደለም።

    በመሆኑም የኮሮናቫይረስ ዋነኛ ምልክት ከፍተኛ ትኩሳትና የማያቋርጥ ደረቅ ሳል መሆኑን አትዘንጉ!

    በቤት ውስጥ የሚዘጋጁ የእጅ ማጽጃ (ሳኒታይዘር)- በኢንተርኔት በመታገዝ በቤት ውስጥ የምናዘጋጃቸው የእጅ ማጽጃዎች፣ በቤት ውስጥ የሚዘጋጁ ጸረ ተዋህስያን እና ለጽዳት የምንጠቀምባቸው ምርቶች ምን አልባት ለቆዳችን ተስማሚ ላይሆኑ ይችላሉ።ለምሳሌ ብዙዎች ቮድካ የተባለው መጠጥ ፍቱን ነው ይላሉ። ይሁን እንጅ ውጤታማ ለመሆን በቂ የአልኮል መጠን የለውም።

    ቫይረሱ ወለል ላይ ለወር ያህል መቆየት ይችላል- ይህ የመሆን እድሉ በጣም ዝቅተኛ ነው። ሳርስ እና መርስ የተባሉ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች ላይ የተሰራ ጥናት እንደሚያመላክተው ቫይረሱ እንደ ብረት፣ ፕላስቲክና ብርጭቆ ያሉ ጠንካራ ቁሶች ላይ ከሁለት ሰዓት በጣም ቢበዛ እስከ 9 ቀናት ሊቆዩ ይችላሉ።

    በመሆኑም የቫይረሱ የመተላለፍ እድል ከ72 ሰዓታት በኋላ ይቀንሳል።

    የላም ሽንት- በህንድ የሚኖሩ አንዳንድ የሂንዱ እምነት ተከታዮች የላም ሽንት መድሃኒትነት አለው ብለው ያምናሉ። ስለሆነም ኮሮናቫይረስን ጨምሮ ሌሎች በሽታዎችን ይፈውሳል ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጅ የላም ሽንት ኮቪድ -19 ጨምሮ ሌሎች በሽታዎችን እንደሚያድን የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም።

    በመሆኑም የሚያዋጣው ባለሙያዎች በመከሩት መንገድ እጅን መታጠብ እንዲሁም አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ብቻ ነው!!

  11. በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር ከ800ሺህ ተሻገረ

    የአሜሪካ ጦር በኒው ዮርክ ያዘጋጀው ጊዜያዊ ሆስፒታል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ጦር በኒው ዮርክ ያዘጋጀው ጊዜያዊ ሆስፒታል

    በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር ከ800ሺህ በላይ ሆኗል።

    እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሁናዊ አሃዝ መሠረት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 800,049 ደርሷል።

    ይህ ቁጥር በቫይረሱ የተያዙ፣ የሞቱ እና ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ድምር ነው።

    አሜሪካ 164ሺህ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በመያዝ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

    ከአሜሪካ በመቀጠል ጣሊያን፣ ስፔን፣ ቻይና፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ እንደየ ቅደም ተከተላቸው በርካታ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ይዘዋል።

  12. የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የጁመዓና ጀመዓ ሶላቶችን ከለከለ

    ሙስሊም

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የጁመዓና ጀመዓ ሶላቶችን ከለከለ።

    የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማ ምክር ቤት ዛሬ በሰጠው ፈትዋ (ሃይማኖታዊ ብያኔ) የጁመዓ ሶላትን ጨምሮ ሌሎች ውሳኔዎችን አሳልፏል።

    ከእነዚህም መካከል፡

    • የጁመዓ እና ጀመዓ (የጋራ) ሶላት ከዛሬ ጀምሮ እንዲቆም
    • በገጠርም ሆነ በከተማ በስብሰባ መልክ የሚካሄዱ ሃማኖታዊ ትምህርቶች(ቁርዓን መቅራት) እንዲሁም የዚክር ስብስብ እንዲቆም
    • በበሽታው የተያዙና በእድሜ የገፉ የእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ፤ ሁሉም የሙስሊም ማህበረሰብ በየትኛውም የሶላት ወቅት በቤታቸው እንዲሰግዱ
    • በአምስቱም የሶላት ወቅቶች የሚደረጉት አዛኖች አማኞች ወደ መስጅድ እንድመጡ ጥሪ የሚያደርጉ ሳይሆን በየቤታቸው እንዲሰግዱ የሚደረግ መሆኑን አማኞች እንዲገነዘቡ
    • በእጅ መጨባበጥ የበሽታውን ስርጭት ስለሚያስፋፋው በእጅ በመጨባበጥ ሰላምታ መለዋወጥም ተክልክሏል።
    • የጤና ተቋማትና መንግሥት የሚያወጣቸውን መመሪያዎች መከተል ሃይማኖታዊ ግዴታ መሆኑን ምክርቤቱ አሳስቧል።

    የጠቅላይ ምክር ቤቱ ቤት መጋቢት 12/2012 ዓ.ም የተለያዩ ለጥንቃቄ የሚረዱ ውሳኔዎችን ያስተላለፈ ቢሆንም አሁንም የበሽታው አደገኝነትና ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ ሌላ ተጨማሪ ፈትዋ (ውሳኔ) ማስተላለፍ ማስፈለጉን አስታውቋል።

  13. ግብጽ በፒራሚዷ ላይ ዜጎቿ እራሳቸውን ከኮሮናቫይረስ እንዲጠብቁ መልዕክት አስተላለፈች

    የግብጽ ታላቁ ጊዛ ፒራሚድ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ግብጽ፣ ሰኞ ዕለት ምሽት የኮሮናቫይረስን መከላከል በሚመለከት በታላቁ ፒራሚድ ላይ የአንድነትና የሕብረት መልዕክት አስተላለፈች።

    "ደህንነታችንን ለምትጠብቁ ምስጋና ይድረሳችሁ" የሚለው መልዕክት ተፅፎ የተነበበው "ከቤት አትውጡ" እና "ጤንነታችሁን ጠብቁ" ከሚሉ ሌሎች መልዕክቶች ጋር ነበር።

    100 ሚሊየን ሕዝብ ያላት ግብጽ፤ እስካሁን ድረስ 656 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ሲታወቅ፣ 41 ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ መሞታቸው ተገልጿል።

    የግብጽ የቱሪዝምና የቅርስ ሚኒስትር የሆኑት ካሊድ አል-አናኒ በዚህ ወረርሽኝ የግብጽ ቱሪዝም ክፉኛ መጎዳቱን ገልፀው "ቅድሚያ ግን ለጤና እንሰጣለን" ማለታቸው ተዘግቧል።

  14. በስፔን በ24 ሰዓት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሞት ተመዘገበ

    የስፔን የጤና ባለሙያዎች በሃዘን ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የስፔን የጤና ባለሙያዎች በሃዘን ላይ

    በስፔን በሃያ አራት ሰዓታት ውስጥ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት 849 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

    ይህ ቫይረሱ በአገሪቷ መገኘቱ ከተረጋገጠ በኋላ በ24 ሰዓታት ውስጥ ያጋጠማት ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር ነው።

    እንደ አገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ከሆነ እስካሁን 8 ሺህ 189 ሰዎች በቫይረሱ ሞተዋል።

    ስፔን አውሮፓ ውስጥ ከጣሊያን ቀጥሎ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ፍዳዋን እያየች ያለች አገር ናት።

  15. ሰበር, በኢትዮጵያ ተጨማሪ ሦስት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች በመገኘታቸው ቁጥሩ 25 ደረሰ

    ማስክ ያደረገች ኢትዮጵያዊት ወጣት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ስትጓዝ። መጋቢት 17 አዲስ አበባ ኢትዮጵያ።

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ማስክ ያደረገች ኢትዮጵያዊት ወጣት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ስትጓዝ። መጋቢት 17 አዲስ አበባ ኢትዮጵያ።

    በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሦስት ተጨማሪ ሰዎች መገኘታቸውን ተከትሎ በጠቅላላው በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች 25 መድረሳቸውን የጤና ሚንስትሯ አስታወቁ።

    ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል ሁለቱ የ30 እና የ36 ዓመት ግለሰቦች ሲሆኑ መጋቢት 15 በተመሳሳይ በረራ ከዱባይ ወደ አዲስ አበባ የገቡ መሆናቸውን እንዲሁም በአሰገዳጅ የለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ ናቸው ተብሏል።

    ሁለት ግለሰቦች የኮቪድ-19 ምልክቶችን ማሳየታቸውን ተከትሎ በተደረገላቸው ምርመራ በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አሳውቀዋል።

    ሦስተኛ ታማሚ የ60 ዓመት አዛውንት መሆናቸው እና መጋቢት 6 ከፈረንሳይ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ተመልክቷል።

    ግለሰቧ የበሽታውን ምልክት ማሳየታቸውን ተከትሎ በለይቶ ማቆያ ከቆዩ በኋላ በተደረገላቸው ምርመራ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል ተብሏል።

    የጤና ሚንስትሯ ጨምረው እንዳስታወቁት ባለፉት 24 ሰዓታት ለ66 ሰዎች የኮቪድ-19 ምርመራ ተካሂዶ በአጠቃላይ ምርመራ የተካሄደላቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 1013 ደርሷል።

    በአሁኑ ሰዓት በኮቪድ መያዛቸው ተረጋግጦ በኢትዮጵያ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው የሚገኙት 21 ሰዎች ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል ሁለቱ በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኙ ተነግሯል።

    ሁለት በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው ጃፓናውያን ወደ አገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል።

  16. የአገር መከላከያ በሄሊኮፕተር መረጃ የያዙ በራሪ ወረቀቶችን ሊበትን ነው

    አገር መካለከያ

    የፎቶው ባለመብት, FDRE Defense Force

    የአገር መከላከያ ሠራዊት ስለ ኮሮናቫይረስ መረጃ የያዙ በራሪ ወረቀቶችን በሄሊኮፕተር ሊበትን መሆኑን አስታወቀ።

    የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ የአገር መከላከያ ሠራዊት በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ በኮሮናቫይረስ ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ያካሂዳል።

    ከእነዚህም መካከል አንዱ በሄሊኮፕተር በመታገዝ ስለ ኮቪድ-19 መረጃ የያዙ በራሪ መረቀቶችን መበተን ነው ተብሏል።

  17. የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ከኮቪድ-19 ነጻ መሆናቸው ተረጋገጠ

    ኔታኒያሁ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆናቸው በምርመራ መረጋገጡ ተነገረ።

    ቀደም ሲል የጠቅላይ ሚንስትር ኔታኒያሁ አማካሪያ በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ለይቶ ማቆያ መግባታቸው ይታወሳል።

    የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት እንዳለው ኔታኒያሁ ወደ ለይቶ ማቆያ የገቡት ከሌሎች የቅርብ አማካሪዎቻቸው ጋር እንደሆነ አስታውቆ ነበር።

    አሁን ግን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር የምርመራ ውጤታቸው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን እንዳመላከተ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።

  18. ሰበር, በምዕራብ ኦሮሚያ ተቋርጦ የነበረው የቴሌኮም አገልግሎት እንዲከፈት ተወሰነ

    Shimelis Abdisa

    የፎቶው ባለመብት, Office of PM

    የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በምዕራብ ኦሮሚያ ተቋርጦ የነበረው የስልክና የኢንትርኔት አገልግሎት ከዛሬ ጀምሮ እንዲከፈት መወሰኑን አስታወቀ።

    የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት በምዕራብ ኦሮሚያ በተለይም በአራቱ የወለጋ ዞኖች ተቋርጦ የነበረው የሞባይል ኢንተርኔት እና የሰልክ አገልግሎት ከዛሬ ጀምሮ እንዲከፈት መወሰኑን ጠቁመዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ለወራት ከግንኙነት መስመሮች ተቆራርጠው በቆዩት አካባቢዎች ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው።

    በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሸኔ የተባለው ቡድን በአካባቢዎቹ የነበረውን የአስተዳደር መዋቅርና የቴሌኮም አገልግሎት መስጫ አውታሮችን በማፍረሱ ምክንያት ለወራት ችግሩ መቀጠሉን ጨምረው ገልጸዋል።

    አቶ ሽመልስ እንዳሉት የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎቱን መልሶ ለማስጀመር እንደምክንያት የጠቀሱት በዞኖቹ ያለው የጸጥታ ችግር በመወገዱ መሆኑን አመልክተዋል።

    ፕሬዝደንት ሽመልስ በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ የወለጋ ዞኖች ሲያደርጉት የነበረውን የሥራ ጉብኝት ያጠናቀቁት ትናንት ነበር።

    ከኮሮናቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ውስጥ የቴሌኮም አገልግሎት የተቋረጠባቸው አካባቢዎች ስለወረርሽኙ መረጃ ያገኙ ዘንደ የቴሌኮም አገልግሎቶች እንዲከፈቱ የተለያዩ ወገኖች መንግሥትን ሲጠይቁ እንደነበረ ይታወሳል።

  19. ህንድ ውስጥ ከሌላ አካባቢ የመጡ ሰዎች ላይ ጸረ-ተህዋሲያን መረጨቱ ቁጣን ቀሰቀሰ

    የህንድ መንግሥት ሠራተኞች ቁጥራቸው በርከት ባሉ በሌላው የአገሪቱ ክፍል ለሥራ ሄደው በተመለሱ ዜጎች ላይ ኮሮናቫይስን የሚገድል ጸረ-ተህዋሲያን መርጨታቸው ከፍተኛ ቁጣን ቀሰቀሰ።

    የአገሪቱ መንግሥት የአካባቢው ባልስልጣናት የወሰዱትን እርምጃን በተመለከተ ምርመራ ጅምሬያለሁ ብሏል።

    የኬሚካል ርጭት የተደረገባቸው ሰዎች ህንድ ያስተላለፈችውን ሙሉ ለሙሉ የእንቅስቃሴ መገደብ ትዕዛዝን ተከትሎ ከሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ወደ ቀያቸው የተመለሱ ናቸው ተብሏል።

    የአካባቢው ባለስልጣናትም ተመላሽ ቫይረሱን ይዘው ሊመለሱ ይችላሉ በማለት ጸረ-ተህዋሲያን እንዲረጭባቸው የተደረገ ሲሆን፤ ድርጊቱም በርካቶችን አስቆጥቷል።

    የህንድ ዜጎች ከውጪ አገራት ወደ ህንድ ሲገቡ በተመሳሳይ መልኩ የኬሚካል ርጭት ተካሂዶባቸዋል ወይ? ሲሉም የጠየቁ አልጠፉም።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

  20. ሶማሊያ ዜጎች ከቤታቸው ሆነው እንዲጸልዩ አሳሰበች

    ሶማሊያዊ ታዳጊ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የሶማሊያ መንግሥት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሁሉም ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች (መድረሳዎች) እንዲዘጉ ውሳኔ አስተላለፈ።

    ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ዜጎች ወደ መስጅድ መሄዳቸውን ትተው በቤታቸው ሆነው እንድጸልዩ ጭምር መንግሥት አስጠንቅቋል።

    ምንም እንኳን በሶማሊያ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 3 ብቻ ቢሆንም፤ ስጋቱ ቫይረሱ ከተሰራጨ ለመቆጣጠር አዳጋች ይሆናል የሚል ነው።

    በሶማሊያ የጤና ተቋማት ላለፉት 30 ዓመታት በተካሄዱት ጦርነቶች የወደሙ ሲሆን፤ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችም የሚኖሩት በጣም በተጨናነቁ መጠለያዎች (ካምፖች) ውስጥ ነው።

    በአገሪቷን አብዛኛውን ደቡባዊና ማዕከላዊ ክፍል የተቆጣጠረው አስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ አል-ሻባብ “በኮቪድ -19 በሽታ የሚያዙት ብቸኛ ሰዎች ለመንግሥት አሊያም ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚሰሩ፤ ‘ኢ አማኒ’ የሆኑ ናቸው” ብሏል።