በኮሮናቫይረስ ጥርጣሬ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ እራሳቸውን ለይተው ተቀመጡ
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶክትር ቶላ በሪሶ በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት እራሳቸውን ለይተው በአንድ ክፍል ለብቻቸው መቀመጣቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ተብሎ ይፋ ከተደረገውና ጃይካ የሚባለው በትምህርት ላይ ከሚሰራው የተራድኦ ድርጀት ባልደረባ ከሆነው ጃፓናዊ ጋር በሥራ ምክንያት በመገናኘታቸው እራሳቸውን ለተወሰኑ ቀናት ለይተው እንዲያቆዩ ያደረጋቸው ምክንያት እንደሆነ ኃላፊው ገልጸዋል።
ጃፓናዊው ከዶክትር ቶላ ጋር በተገናኘበት በዚያን ጊዜ "ገና ከውጪ አገር መምጣቱ ስለነበር ምንም አይነት የበሽታው ምልክት አይታይበትም ነበር" በማለት ከእርሱ ጋርም አንድ ኢትዮጵያዊ አብሮት እንደነበረ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ይህ ጃፓናዊ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ በአርሲ ዞን ሁለት ትምርት ቤቶችን ጎብኝቶ እንደነበረ የሚናገሩት ኃላፊው እሱ በሄደባቸው ቦታዎች አብረተውት የነበሩ ሰዎችም እራሳቸውን ለይተው ክትትል እተደረገላቸው መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።