ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉና ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ ተወሰነ

በኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር አምስት መድረሱን ተከትሎ በመላ አገሪቱ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉና ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ መወሰኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስታወቁ። ቢቢሲ አማርኛ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ የሚወጡ ትኩስ ዘገባዎችን በቀጥታ ያቀርባል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የዛሬው የቀጥታ ዘገባችን በዚህ ይቋጫል

    የዛሬው የቀጥታ ዘገባችን በዚህ ይቋጫል።

    ወደ እናንተ ስናደርሳቸው የነበሩትን ዘገባዎች ከዚህ በታች መመልከት ይችላሉ።

    ነገ ጠዋት በሌላ የቀጥታ ዘገባ እንመለሳለን።

  2. መዓዛ መላኩ፤ መስማት ለተሳናቸው ዜጎች ስለኮሮናቫይረስ መረጃ የምታቀብለዋ በጎ ፍቃደኛ

    በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ ሕብረተሰቡን ለመርዳት በበጎ ፈቃደኝነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው።

    ከእነዚህም መካከል ሰለ ኮሮናቫይረሰ ጠቃሚ መረጃዎችን መስማት ለተሳናቸው ዜጎች በፌስቡክ አማካኝነት በምልክት ቋንቋ የምታሰራጨው መዓዛ መላኩ ትገኝበታለች።

    ልዩ ፍላጎት ያላቸው ዜጎች እንደዚህ ያሉ ወሳኝ እና ወቅታዊ መረጃዎችን የሚያገኙበት ዕድል በጣም ጠባብ እንደሆነ መዓዛ ትናገራለች።

    ለዚህም “ኃላፊነቴን መወጣት ስላለብኝ ይህን ተግባር ለመፈጸም ተነሳሳሁኝ” ስትል መዓዛ ለቢቢሲ ተናግራለች።

    መዓዛ በፌስቡክ ገጿ ቫይረሱን በተመለከተ ከመንግሥት እየተሰጡ ያሉ መግለጫዎችን መስማት ለተሳናቸው ዜጎች በምልክት ቋንቋ እያስተላለፈች ትገኛለች።

    በአገሪቱ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ከቫይረሱ ጋር በተገናኘ መስማት ለተሳናቸው ዜጎች አጥጋቢ መረጃ መስጠት እስኪጀምሩ ድረስ ፌስቡክን በመጠቀም መልዕክት የማድረስ ጥረቴን እቀጥላለሁ ብላለች።

    መዓዛ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምልክት ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪዋን፤ ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ ከኦስሎ ዩኒቨርሲቲ በልዩ ፍላጎት ትምህርት አጠናቃለች።

  3. ኮሮናቫይረስ፡ አጫጭር ዓለም አቀፍ መረጃዎች

    • ዛሬ ላይ ከቻይና በላይ በተቀረው የዓለማችን ክፍል በኮሮናቫይረስ የተጠቁ ብዙ ሰዎች ይገኛሉ

    • ሆላንድ፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ እና ሰዊዘርላንድን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ አገራት በኮሮናቫይረስ የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መሆኑን ሪፖርት እያደረጉ ነው።

    • ጀርመን ከፈረንሳይ፣ ኦስትሪያ እና ስዊዘርላንድ ጋር የሚያገናኘትን ድንበር ዘግታለች።

    • ኒው ዮርክ እና ሎስ አንጀለስን ጨምሮ በርካታ የአሜሪካ ከተሞች ምግብ ቤቶች እና መጠጥ ቤቶች እንዲዘጉ ውሳኔ አስተላልፈዋል።

    • በኢራን በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 853 ደርሷል። 14991 ሰዎች በኮሮና መያዛቸውን ተከትሎ ኢራን ከቻይና እና ጣሊያን በመቀጠል በዓለማችን ብዙ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙባት ሦስተኛ አገር ሆናለች።

    • ኤርትራ ዜጎቿ እንቅስቃሴያቸውን እንዲገድቡ ጥሪ አቅርባለቸ። የኤርትራ ዜጋም ሆነ ነዋሪ፤ አስቸኳይ ካልሆነ በቀር በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ከሚደረጉ ጉዞዎች እንዲቆጠቡ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር አሳስቧል።

    • ታንዛኒያናና ሶማሊያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች በአገራቸው መገኘታቸውን ይፋ አድርገዋል።

    የኮሮናቫይረስ በተመለከተ እና መንግሥታት የቫይረሱን ስርጭትን ለመግታት እየወሰዱ ስላሉት እርምጃ ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት ዘውትር የቢቢሲ ገጽን መጎብኘት አይዘንጉ።

  4. የተወካዮች ምክር ቤት ነገ ሊያካሂድ የነበረውን ስብሰባ ሰረዘ

    የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ ያካሂድ የነበረውን መደበኛ ስብሰባ መሰረዙን ለአባላቱ አሳውቋል።

    ምክር ቤቱ በፌስቡክ ገጹ ለምክር ቤት አባላቱ የስብሰባውን መሰረዘ ባሳወቀበት ጽሑፍ ላይ ለስበሰባው መሰረዝ ምክንያቱ ምን እንደሆነ አልጠቀሰም።

    ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ዛሬ ረፋድ ላይ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሰብሰባዎች እንዳይካሄዱ መወሰኑን ማሳወቃቸው ይታወቃል።

  5. አምቡላንስ ሰብሮ ያመለጠው ከኮሮና ነጻ መሆኑ ተነገረ

    በኮሮናቫይረስ ተጠርጥሮ አምቡላን ሰብሮ ያመለጠው ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ ተነገረ።

    ከሳዑዲ ዓረቢያ ተመልሶ የኮሮናቫይረስ ምልክት ማሳየቱን ተከትሎ ወደ ለይቶ ማቆያ በሚወሰድበት ጊዜ አምቡላንስ ሰብሮ አምልጦ በደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ በቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወሳል።

    የኢትዮጵያ ሕብረሰተብ ጤና ኢንስቲትዩት ግለሰቡ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ በላቦራቶሪ ምርመራ ተረጋግጧል ብሏል።

    አምቡላንስ ሰብሮ ያመለጠው ወጣት በወቅቱ ያደረገውን ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ በመጫን ያንብቡ።

  6. በስፔን እና ሆላንድ በኮሮናቫይረስ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው

    በስፔን እና ሆላንድ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ይገኛል።

    በስፔን በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 300 ተቃርቧል።

    በሆላንድ ደግሞ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ 278 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 24 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሞተዋል።

    በስፔን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 8744 ያሸቀበ ሲሆን፤ 297 ሰዎች ሞተዋል።

    በስፔን ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ አዲስ 991 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፤ 9 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።

  7. ኤርትራ ዜጎቿ እንቅስቃሴያቸውን እንዲገድቡ ጥሪ አቀረበች

    ምንም እንኳ ኮሮናቫይረስ በኤርትራ ሪፖርት ባይደረግም፤ የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር የበሽታውን ስርጭት ቀድሞ ለመከላከል በማሰብ ዜጎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ገደብ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

    የኤርትራ ዜጋም ሆነ ነዋሪ፤ አስቸኳይ ካልሆነ በቀር በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ከሚደረጉ ጉዞዎች እንዲቆጠቡ ጤና ጥበቃ ሚንስቴሩ አሳስቧል።

    ከዚህ በተጨማሪም፤ ሰዎች ከሚሰበሰቡባቸው ስፍራዎች ዜጎች እራሳቸውን እንዲያርቁ ምክር አዘል ማሳሰቢያዎች ተላልፈዋል።

  8. ወረርሽኝ ምንድን ነው? እስካሁን በዓለም የተከሰቱት ወረርሽኞችስ ምን ዓይነት ነበሩ?

    ዓለማችን በተለያዩ ጊዜያት መጠናቸውና ዓይነታቸው የተለያዩ ወረርሽኞችን አስተናግዳለች። ለመሆኑ ወረርሽኝ ምንድን ነው?

    የሜሪያም ዌብስተር መዝገበ ቃላት "ወረርሽኝ ማለት አንድ በሽታ በሰፊ ቦታ ላይ ሲከሰትና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ሲይዝ ነው" በማለት ይተረጉመዋል።

    በተለያዩ ጊዜያት በዓለም ዙሪያ የተከሰቱት ወረርሽኞች በርካታ ቁጥር ያለው ሰው ያጠቁ ሲሆን በፈረንጆቹ በ1918 አካባቢ የተከሰተው ስፓኒሽ ፍሉ ግን በገዳይነቱ ተወዳዳሪ የለውም። በወቅቱ በዚሁ ወረርሽኝ ሳቢያ 50 ሚሊዮን ሕዝብ መሞቱ ይነገራል።

  9. የአንበሳ እና ሸገር አውቶብሶች ለታሳፋሪዎች እጅ ማጽጃ ያቀርባሉ

    የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት አንበሳ እና ሸገር አውቶብሶች ለተሳፋሪዎቻቸው የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘር እንደሚያቀርቡ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) አስታወቁ።

    ተሳፋሪዎች ወደ አውቶብሶቹ ሲገቡ እጃቸውን በሳኒታይዘር እንዲያጸዱ ይሆናል። እንዲሁም የአውቶብሶቹ አሽከርካሪዎች የእጅ ጓንት ያደርጋሉ ብለዋል ምክትል ከንቲባው።

  10. ታንዛኒያና ሶማሊያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ማገኘታቸውን ይፋ አደረጉ

    ታንዛኒያና ሶማሊያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች በአገራቸው መገኘቱን ይፋ አድረጉ።

    የሶማሊያ ጤና ጥበቃ ሚንስትር ፎወሲያ አቡካር በኮሮናቫይረስ መያዙ የተረጋገጠው ግለሰብ ከውጪ አገር የተመለሰ የሶማሊያ ዜጋ ነው ብለዋል።

    የሶማሊያ ባለስልጣናት ከመጋቢት 9 ጀምሮ ወደ ግዛታቸው የሚደረጉ በረራዎችን ለሁለት ሳምንታት ማገዳቸውን አሳውቀዋል።

    የታንዛኒያ ጤና ሚንስቴር በበኩሉ ዛሬ ቫይረሱ የተገኘባት ሴት የ46 ዓመት ጎልማሳ መሆኗን አሳውቋል።

    ጤና ጥበቃ ሚንስቴሩ ጨምሮም ግለሰቧ ከቤልጄየም ተነስታ በሰዊድንና በዴንማርክ በኩል አድርጋ ወደ ታንዛኒያ መግባቷን ይፋ አድርጓል።

    የታንዛኒያ የጤና ጥበቃ ሚንስትር ኡሚ ሙዋሊሙ እንዳሉት፤ ግለሰቧ በታንዛኒያ አየር ማረፊያ እንደደረሰች መልካም ጤንነት ስላልተሳማት ለጤና ባለሙያዎች ሪፖርት አድርጋለች።

    ከግለሰቧ ጋር ንክኪ ነበራቸው የተባሉ ሰዎችን ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ሚንስትሯ ጨምረው አስታውቀዋል።

  11. በኢትዮጵያ መንግሥት በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ተግባራዊ የሚደረጉ እርምጃዎች

    የኮሮናቫይረስ [ኮቪድ-19] ስርጭትን ለመከላከል የተቋቋመው ኮሚቴ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ባደረገው ውይይት የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባትና በኢኮኖሚውላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ በመመዘን እንደ አስፈላጊነቱ ሊሻሻሉ የሚችሉያላቸውን የሚከተሉትን እርምጃዎች ለሁለት ሳምንታት ተግባራዊ እንዲደረጉ ወስኗል፡

    1.ስፖርታዊ ክንዋኔዎች፣ ስብሰባዎችና የውይይት መድረኮችን ወደ ሌላ ጊዜ ማስተላለፍ።

    2.የተወሰነ ሕዝብ የሚሰበሰብባቸውን ክንውኖች የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን ሳያማክሩ ያለማድረግ

    3.ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውጪ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችንሁሉ መዝጋት

    4.በሀይማኖት ተቋማትና የአምልኮ ስፍራዎች ሕዝብ የሚሰበሰብባቸውን ሁኔታዎች መቀነስ

    5.ብሔራዊ የንጽህና አጠባበቅና መከላከያ መንገዶችን የሚያስገነዝብ ንቅናቄ ማስጀመር

    6.የአፍ መሸፈኛ ጭምብል፣ ሳሙናዎች፣ ፈሳሽ የመድሃኒት አልኮልና ሌሎችእንዲሰራጩ ማድረግ

    7.በትራንስፖርት መገልገያዎች ላይ መጨናነቅ ለመቀነስ የመንግሥት አውቶብሶች ለሕዝቡ በነፃ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ።

    8.የመንግሥት ሠራተኞችን የሚያጓጉዙ አውቶብሶችሥራቸውን ካከናወኑ በኋላ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ።

    9.የንግድሚኒስቴር ቁሳቁሶችና መገልገያዎች ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት መቆጣጠርና አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪን በሚያደርጉ ላይ እርምጃ መውሰድ።

    10.በአረጋውያን እንክብካቤ ማዕከላት ውስጥ የመከላከያ እርምጃዎች ይወሰዳሉጤና ሚኒስቴር ክትትል ያደርጋል።

  12. የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንዲዘጋጅ ጠየቀ

    የኢትዮጵያዊያን የአኗኗር ዘዬ ለኮሮናቫይረስ በቀላሉ መሰራጨት ምቹ በመሆኑ ምዕመናን ይህን ልማድ ለጊዜው በመግታት የጤና ተቋማት የሚሰጡትን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ።

    ጉባኤው ምዕመናን የቫይረሱ ምልክቶችን በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ላይ ሲመለከቱ መረጃውን በአፋጣኝ ለሚመለከታቸው የጤና ተቋማት እንዲያሳውቁም ጠይቋል።

    ምዕመናን በየቤተ እምነታቸው ተገኝተው የአምልኮ ሥነ ሥርዓቶችን ሲካፈሉም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፤ ይህንንም ሲያደርጉ የሌሎችን ስሜትና ሥነ ልቦና በማይጎዳ መልኩ እንዲሆን አሳስቧል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው።

    በሌላ በኩል የንግድ ማኅበረሰቡም የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚያስፈልጉም ሆነ በሌሎች የፍጆታ እቃዎች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ ጭማሪ ከማድረግ እንዲታቀቡም ጠይቋል።

    የመንግሥት ኃላፊዎች አስፈላጊውን ጥረትና ዝግጅት እንዲያደርጉ፤ መገናኛ ብዙሃንም ትክክለኛ መረጃን በወቅቱ በማድረስ ወገናቸውን የመርዳት ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስቧል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ።

  13. የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ልንፈጽማቸው የሚገቡ ነገሮች

    የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) በሽታ

    እራስዎንና ሌሎችን እንዴት መጠበቅ ይችላሉ?

    እነዚህን መልካም ልምዶች ይከተሉ

    • እጅዎ በሚታይ ሁኔታ ሲቆሽሽ ዘወትር በሳሙናና በውሃ በደንብ አድርገው ይታጠቡ።
    • በእጅዎ ላይ የሚታይ ቆሻሻ ከሌለ ከአልኮል በተዘጋጁ የእጅ ማጽጃ እጅዎን ያጽዱ ወይም በሳሙናና በውሃ ይታጠቡ።
    • በሚያስነጥሱ ወይም በሚያስሉ ጊዜ ተጠቅመው በሚጣሉ ስስ ወረቀቶች አፍና አፍንጫዎን ይሸፍኑ።የተጠቀሙበትንም ወረቀት ወዲያው ያስወግዱ።
    • በሽታው ከተከሰተባቸው አገራት የመጡ ከሆነና ትኩሳት፣ሳል፣የመተንፈስ ችግር ካጋጠመዎ በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ የጤና ተቋም ይሂዱ።
    • ሲያስሉና ሲያስነጥሱ በስስ ወረቀት ወይም በክርንዎ አፍና አፍንጫዎን ይሸፍኑ።

    ማድረግ የሌለብዎነገሮች

    • በህይወት ካሉ የግብርናና የዱር እንስሳት ጋር ወይም እነሱ ከነኳቸው ነገሮች ጋር መከላከያ ሳያደርጉ የቅርብ ንክኪን ያስወግዱ።
    • በበሽታ የሞቱ እንስሳትን ሥጋ ከመመገብ ይቆጠቡ።
    • የበሽታው ወረርሽኝ ከተከሰተባቸው አገራት ከመጡ ወይም የጉንፋን ምልክቶች ከሚታይባቸው ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪን ያስወግዱ።
    • ጥሬ ሥጋን፣ እንቁላልንና ወተትን ጨምሮ ያልበሰሉ የእንስሳ ተዋጽኦዎችን ከመመገብና ከመጠጣት ይቆጠቡ።
  14. ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ለአንድ ቀን ሠራተኞቹ ከቤታቸው እንዲሰሩ አደረገ

    በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሠራተኞች በዛሬው ዕለት [ሰኞ መጋቢት 07] ከቤት እንዲሰሩ ቦርዱ ወስኗል።

    ቦርዱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ለቦርዱ የቴክኒካ ድጋፍ ከሚሰጡ የውጭ አገር ባለሙያዎች መካከል አንድ ግለሰብ የበሽታው ምልክቶች ናቸው የሚባሉት ስለታዩበት ሲሆን ምርመራ ተደርጎ ውጤቱ እስኪረጋገጥ ድረስ ቅድመ ጥንቃቄ ሲባል የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ገልጿል።

    ይህ ግለሰብከአንድ ወር በፊት ወደ አገር ውስጥ የገባ ሲሆን ቦርዱም ምልክቶቹ ከታዩበት ጊዜ አንስቶ ምርመራ እንዲደረግለት ጠይቆ ምርመራው እንዲካሄድ እየጠበቀ ይገኛል።

    በዚህም መሰረት የግለሰቡ ምርመራ ተከናውኖ የሚገኘው ውጤት እስኪታወቅ ለዛሬ የቦርዱ ሠራተኞች ከቤታቸው ሆነው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ መደረጉን አመልክቷል።

  15. ሰበር, ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፤ ስብሰባዎችም እንዳይካሄዱ መወሰኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አስታወቁ

    ከዛሬ ጀምሮ ትምህርት ቤቶች፣ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና ትልልቅ ስብሰባዎች ለቀጣዮቹ 15 ቀናት እንደሚዘጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስታወቁ።

    እገዳው ከዛሬ ጀምሮ በመላ አገሪቱ ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ዛሬ በጽ/ቤታቸው በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

    የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ግን እንደ አስፈላጊነቱ በያሉበት ዩኒቨርሲቲ ክትትል የሚደረግላቸው ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ ታይቶ አነስተኛ ስብሰባዎችም በጤና ሚኒስቴር እውቅና ሊካሄዱ እንደሚችሉም አመልክተዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በዚህ ወቅት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ እንደ አልኮልና ሳሙና ያሉ በስፋት የሚሰራጩም ይሆናል።

  16. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ህብረተሰቡ ጤና ሚኒስቴር የሚሰጠውን መመሪያ እንዲከተል አሳሰቡ

    ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን መከላከል ይቻል ዘንድ ህብረተሰቡ በጤና ሚኒስቴር የሚሰጡ መመሪያዎችን እንዲተገብር ማሳሰባቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት መረጃ ዘግቧል።

    ዘገባው እንደሚያሳየው ፓትሪያርኩ በቀሪው የዐቢይ ፆም ጊዜ በሁሉም የኢትዮጵያ

    ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አድባራት እና ገዳማት የምህላ ጸሎት እንዲደረግም አውጀዋል።

  17. በርካታ አፍሪካ አገራት ወደ አገራቸው የሚደረግ ጉዞን እያገዱ ነው

    ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ አገራት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን እያገኙ መሆናቸውን ተከትሎ የጉዞ እገዳዎችን እየጣሉ ነው።

    ቀደም ሲል ኬንያ ከየትኛውም ኮሮናቫይረስ ከተገኘበት አገር ወደ ኬንያ የሚደረግን ጉዞ ማገዷ ሲሰማ የኬንያን ፈለግ በመከተል ደቡብ አፍሪካም ተመሳሳይ እገዳ ጥላለች።

    የደቡብ አፍሪካ እገዳ ቻይና፣ኢራን፣ ጣልያን፣ ስፔን፣ እንግሊዝና አሜሪካን ይጨምራል።

    ጋናም የኮሮናቫይረስ ከፍተኛ ስርጭት ካለባቸው አገራት ተጓዦች እንዳይመጡብኝ ብላለች። የኮሮናቫይረስ ኬዝ ያልተመዘገበባቸው ጅቡቲና ታንዛኒያም ጭምር ዓለም አቀፍ በረራዎችን አግደዋል።

    በኮሮናቫይረስ የተያዙ 28 ሰዎች የተገኙባት እንዲሁም ሞት የተመዘገበባት ሞሮኮም ዓለም አቀፍ በረራዎችን አግዳለች።

    አልጄሪያ ከነገ ጀምሮ ወደ ፈረንሳይ የሚደረግን በረራ እንደምታቆም ስታስታውቅ ሞዛምቢክ ባለስልጣናቷ ወደ ውጭ አገር ጉዞ እንዳያደርጉ ከልክላለች።

    በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ በ26 የአፍሪካ አገራት እንደተገኘ ተረጋግጧል።

  18. የኢንትርኔት አገልግሎት መቋረጥና የኮሮናቫይረስ በሽታ መረጃ

    በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ለወራት ተቋርጦ የቆየው የቴሌኮም አገልግሎት ከኮሮናቫይረስ ክስተት ጋር በተያያዘ እንዲከፈት እየቀረበ ባለው ጥያቄ ዙሪያ እስካሁን የተለየ ነገር እንደሌለ የኢትዮቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለቢቢሲ ገለጹ።

    ይህንን በተመለከተ የወረርሽኙ አሳሳቢነት ከታወቀና በኢትዮጵያ ውስጥም የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው ከተሰማ በሗላ በተለይ ምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ አካባቢዎች የስልክና የኢንተርኔት አገልገሎቶች መቋረጣቸው ስለበሽታው ያለውን የመረጃ ተዳራሽነት ያስተጓጉላል በሚል ጥያቄዎች እየተንሱ ነው።

    ተጨማሪ ሦስት የኮሮናቫይረስ ተጠቂዎች መገኘታቸውና በርካታ በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎች መኖራቸውን በጤና ሚኒስቴር መገለፁን ተከትሎ የኢንተርኔና የስልክ አገልግሎቶችን የመመለስ ሐሳብ ካለ በሚል ቢቢሲ ለኢትዮቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

    ትናንት አመሻሽ ላይ ለሥራ ጉዳይ ከከተማ ርቅው ቆይተው እየተመለሱ መሆናቸውን የጠቀሱት ሥራ አስፈጻሚዋ ተቋርጦ ስላለው የቴሌኮም አገልግሎት አዲስ መረጃ አንደሌላቸው ለቢቢሲ ተናገረዋል።

  19. በአውሮፓ በአንድ ቀን ብቻ ከፍተኛ የተባለውን የሞት ቁጥር ተመዘገበ

    ሦስት የአውሮፓ ኅብረት አገራት እስከ ዛሬ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በቀን ከተመዘገበባቸው የሞት መጠን አንጻር ትናንት ከፍተኛ የተባለውን የሞት አስመዝግበዋል።

    ጣሊያን በትናንትናው ዕለት 368 ዜጎቿን ስታጣ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር ወደ 1 ሺህ 809 አሻቅቧል።

    ስፔን 97 ዜጎቿ የሞቱባት ሲሆን አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 288 ደርሷል። በፈረንሳይም በትናንትናው ዕለት 29 ሰዎች ሲሞቱ በአጠቃላይ 120 ዜጎቿን በኮሮናቫይረስ ተነጥቃለች።

    የዩናይትድ ኪንግደምም ትናንት ብቻ 14 ሰዎች የሞቱባት ሲሆን በአጠቃላይ ደግሞ የሟቾች ቁጥር ወደ 35 አድጓል።

    በአውሮፓ መንግሥታት መመሪያዎችን በማጠናከርና የድንበር ቁጥጥሮችን በመጨመር ላይ ናቸው።

    ኦስትሪያ ከአምስት ሰው በላይ መሰባሰብ የተከለከለ መሆኑን አውጃለች። በብዙ የኅብረቱ አገራትም ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።

  20. ኬንያ የውጪ ዜጎች ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ በማገድ ትምህርት ቤቶችን እንዲዘጉ ወሰነች

    ኬንያ ባለፈው አርብ ካስመዘገብችው አንድ በበሽታው የተያዘ ሰው በተጨማሪ ሁለት ሰዎች መገኘታቸውን ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በቴሌቪዥን ቀርበው አሳወቁ።

    በተጨማሪም ኬንያ የኮሮናቫይረስ ከተመዘገበባቸው አገራት የሚመጡ ስዎች ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ እገዳ የጣለች ሲሆን ኬንያዊያንና የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው ብቻ መግባት የተፈቀደላቸው ሲሆን ለ14 ቀናት እራሳችውን አግልለው መቆየት ይጠበቅባቸዋል።

    በተጨማሪም በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ የትምህርት ተቋማት ትምህርት እንዲያቆሙ የሚደረግ ሲሆን የተለያዩ ተቋማትም የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ፕሬዝዳንቱ አዘዋል።