ትራምፕ ከማክሰኞ በፊት ሆርሙዝ የማይከፈት ከሆነ ኢራን "ሲኦል" እንደምትሆን አስነዋሪ ቃላትን በመጠቀም ዛቱ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን ከማክሰኞ በፊት የሆርሙዝ ወሽመጥን የማትከፍት ከሆነ አገሪቱን “ሲኦል” እንደሚያደርጉ አስነዋሪ ቃላትን በመጠቀም አስጠነቀቁ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በውጊያ ወቅት ተመትቶ የወደቀን የአሜሪካ ጦር አባል ፈልጎ ማዳን ሲባል ምን ማለት ነው?

    በቀላል ቋንቋ ይህ ተልዕኮ በውጊያ ወቅት ተመትቶ የወደቀን አብራሪ ወይንም በጠላት ጦር ተቆርጦ የቀረን ሠራዊት የመፈለግ፣ ድጋፍ የመስጠት እና የማትረፍ ዘመቻ ነው።

    ይህ ከተለመደው በሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ወይም በአደጋ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ፈልጎ የማግኘት ጥረት በተቃራኒው ጦርነት በሚካሄድባቸው እና በአወዛጋቢ ስፍራዎች የሚካሄድ ዘመቻ ነው።

    አንዳንድ ጊዜ አርብ ዕለት በኢራን ግዛት እንደሆነው ሁሉ ፍለጋው እና በሕይወት የማግኘቱ ሥራ የሚሰራው በጠላት ግዛት ውስጥ ዘልቆ በመግባት ይሆናል።

    የፍለጋ እና በሕይወት የማትረፍ ዘመቻው የሚካሄደው በሂሊኮፕተር ሲሆን አብሮም በበረራ ላይ ነዳጅ መሙላት የሚያስችል አውሮፕላን እንዲሁም በመንገድ ላይ ከጠላት ጥቃት ቢገጥም ጥቃት የሚፈጽም እና አካባቢውን የሚቃኝ አውሮፕላን ድጋፍ ለመስጠት ይከተላሉ።

    የቀድሞ አዛዥ እና የዚህ ልዩ ኃይል አባል የነበረ ግለሰብ ለሲቢኤስ እንደተናገረው በኢራን ውስጥ እንደተካሄደው የፍለጋ እና በሕይወት የማዳን ተግባር ቢያንስ በብላክ ሆክ ሂሊኮፕተር የሚታገዙ 24 አባላት ይሳተፉበታል።

    ይህ የፍለጋ ቡድን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ከአውሮፕላኑ ላይ ዘሎ የሚወርድ ሲሆን መሬት ካረፈ በኋላም ከጠፋው የአውሮፕላን አብራሪ ጋር ግንኙነት መፍጠር ቀዳሚ ተግባሩ ይሆናል።

    የጠፋው የአውሮፕላን አብራሪ ከተገኘ በኋላ አስፈላጊ ከሆነ የሕክምና ድጋፍ መስጠት፣ ከጠላት ዕይታ መሰወር እና አካባቢውን ለቅቀው የሚወጡበት ስፍራ ላይ መገኘት ይኖርባቸዋል ሲል ሲቢኤስ ዘግቧል።

    የቀድሞው አዛዥ ለሲቢኤስ "አስፈሪ እና አደገኛ ማለት ሁኔታውን ማቃለል ነው" ሲል ተናግሯል።

    አክሎም "በመላው ዓለም ይህንን ለማከናወን ነው የሰለጠኑት። ስዊስ አርሚ ናይቭስ ኦፍ ዘ ኤር ፎርስ (የአየር ኃይሉ የስዊዝ ቢላ) በመባል ነው የሚታወቁት" ብሏል።

    አርብ ዕለት ኢራን ውስጥ የተቀረጸ እና ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ ተንቀሳቃሽ ምስል የአሜሪካ ሂሊኮፕተር እና ቢያንስ አንድ ነዳጅ የሚሞላ አውሮፕላን በኢራን ኩህዜስታን አውራጃ ሰማይ ላይ ሲበሩ ታይተዋል።

    ተጨማሪ ለማንበብ ቀጣዩን መስፈንጠሪያ ይጫኑ

  2. የኢራን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ከ350 በላይ የአሜሪካ ጦር አባላት ጉዳት ደርሶባቸዋል- ፔንታጎን

    አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በመሆን ኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱበት ዕለት አንስቶ 365 የአሜሪካ ወታደሮች ጉዳት እንደደረሰባቸው ፔንታጎን አስታወቀ።

    አሜሪካ በዚህ ጦርነት ውስጥ 13 ወታደሮቿ ተገድለውባታል።

    ጉዳት የደረሰባቸው የአሜሪካ ወታደሮች ከእግረኛ፣ ባሕር ኃይል እንዲሁም ከአየር ኃይል አባላቱ የተውጣጡ መሆናቸውን የፔንታጎን መረጃ ያሳያል።

  3. ኢራን እና አሜሪካ በኢራን ግዛት ተመትቶ የወደቀውን የአየር ኃይል ባልደረባ ለማግኘት ጥድፊያ ላይ መሆናቸው ተዘገበ

    የአሜሪካ ተዋጊ ጄት በኢራን ግዛት ውስጥ ተመትቶ መውደቁ ከተሰማ በኋላ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ከበረራ አባላቱ መካከል አንዱ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ሳያርፍ እንዳልቀረ እየዘገቡ ነው።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ አብራሪው መገኘቱን እና አብሮት የነበረው የጦር መሣሪያ ስርዓት ተቆጣጣሪ ባልደረባው ግን እየተፈለገ መሆኑን ተናግረዋል።

    የኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ዜጎች “አብራሪውን በሕይወት ይዞ ለሚያስረክብ” ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት እንደሰጠው ሲያስተዋውቁ ተደምጠዋል።

    ሽልማቱ እስከ 66 ሺህ 100 የአሜሪካ ዶላር እንደሚደርስ የመገናኛ ብዙኃኑ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ይህ ገንዘብ በአገሪቱ ከሚታወቀው ወርሃዊ ደሞዝ አንጻር እጅግ በጣም ከፍተኛው ነው።

    ከዚህ መግለጫ በኋላ የታጠቁ ግለሰቦች በሁለት የአገሪቱ ደቡባዊ ግዛቶች የጦር ጄቱ ውስጥ የነበሩ አባላትን ፍለጋ ላይ መሰማራታቸውን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ተለቅቋል።

    አንድ ትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠ ቪዲዮ በደቡባዊ ኩህዜስታን አውራጃ በርካታ ሰዎች ጠመንጃ እና የአገሪቱን ባንዲራ ይዘው ፍለጋ ሲሰማሩ ያሳያል። በቪዲዮው ላይ አንዱ ግለሰብ “ፈጣሪ ይረዳናል እናገኘዋለን” ሲል ይደመጣል።

  4. የአሜሪካ ጄት ኢራን ውስጥ ተመትቶ መውደቁን አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘገበ

    የአሜሪካ ተዋጊ ጄት ኢራን ውስጥ የወደቀው ተመትቶ መሆኑን ከአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር የኢሜይል መልዕክት መመልከቱን የዜና ወኪሉ አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘገበ።

    የዜና ወኪሉ የተመለከተው የፔንታጎን ኢሜይል መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ “አውሮፕላን ተመትቶ ወድቋል” የሚል እንደሆነ ገልጿል። ኤሜይሉ ዝርዝር መረጃ አላከተተም ተብሏል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አርብ ዕለት የአሜሪካ ተዋጊ አውሮፕላን መትቶ መጣሉን ገልጿል።

    የኢራን ባለሥልጣናት እንደሚናገሩት ጄቱ ሲመታ አብራሪው ወጥቷል፤ የአገሪቱ ዜጎችም አብራሪውን እንዲፈልጉ ጠይቀዋል።

    እንደተመታ የተገለጸው “ኤፍ-15ኢ” ተዋጊ ጄት ሁለት አብራሪዎችን የሚይዝ ሲሆን፣ የአሜሪካ ኃይሎች አንዱን እንደታደጉት ተዘግቧል።

    የአሜሪካ መንግሥት እስካሁን ድረስ ስለ ክስተቱ ይፋዊ አስተያየት አልሰጠም። ዋይት ሐውስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስለ ወደቀው ጄት ገለጻ እንደተደረገላቸው ከመግለጽ ውጪ ተጨማሪ መረጃ አላቀረበም።

  5. የኢራኑ አፈ ጉባኤ አሜሪካ “ከአገዛዝ ለውጥ” ወደ “ፓይለቶቻችንን አፋልጉን” ተሸጋግራለች ሲሉ ተሳለቁ

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ እና አሜሪካ ለድርድር ከምትመርጣቸው የአገሪቱ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ የሆኑት ሞሐማድ ባግሄር ጋሊባፍ ኢራን ውስጥ ተመትቶ መውደቁ በተዘገበው የአሜሪካ ተዋጊ ጄት ላይ ተሳለቁ።

    አፈ ጉባኤው በኤክስ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አሜሪካኖች በኢራን ውስጥ የአገዛዝ ለውጥ ከማምጣት ወደ አብራሪዎቻቸውን ወደ መፈለግ መሸጋገራቸውን በምጸት ጽፈዋል።

    “በተከታታይ ኢራንን ለ37 ጊዜ ካሸነፉ በኋላ፣ ይህ ያለ ስትራቴጂ የጀመሩት ጦርነት አሁን ‘ከአገዛዝ ለውጥ’ ወደ ‘እባካችሁ ፓይለቶቻችንን አፋልጉን’ ወደሚል ደረጃ ወርዷል” ብለዋል ጋሊባፍ።

    ከቀናት በፊት ትራምፕ በኢራን ውስጥ የአገዛዝ ለውጥ መካሄዱን አፈ ጉባኤው የሚካተቱበት አዲሱ የኢራን መሪዎች ትውልድ ከቀደሙት “በጣሙን የተለሳለሱ ጽንፈኞች” እና “ምክንያታዊ” ናቸው ብለው ነበር።

    ሞሐማድ ባግሄር ጋሊባፍ በኤክስ ላይ ጨምረውም “የሚደንቅ ነው። ምን ዓይነት ለውጥ ነው። ፍጹም ብልሆች” ሲሉ በአሜሪካኖች ተሳልቀዋል።

    አንዳንድ ያልተረጋገጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ጋሊባፍን ቀጣይ አጋር እና ቀጣዩ የኢራን መሪ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ ያምናል።

  6. የወደቀውን የአሜሪካ ተዋጊ ጄት አንድ አብራሪ መታደግ መቻሉን ባለሥልጣናት ተናገሩ

    ኢራን ውስጥ የወደቀው የአሜሪካ ተዋጊ ጄት ውስጥ ከነበሩ ሁለት የአየር ኃይል አባላት መካከል አንዱን መታደግ እንደተቻለ የዋሽንግተን ባለሥልጣናት መናገራቸው ተዘገበ።

    በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ሁለት ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ እንዳመለከተው የወደቀው “ኤፍ-15ኢ” ተዋጊ ጄት ሁለት ሰዎችን ይዞ ነበር።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በአገሪቱ ማዕከላዊ ክፍል በሚገኝ አካባቢ የአሜሪካ ተዋጊ ጄትን መትቶ መጣሉን አስታውቋል።

    ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጣ እና ቢቢሲ ያረጋገጠው አንዲ ቪዲዮ አንድ የአሜሪካ አውሮፕላን በሁለት ሄሊኮፕተሮች ታጅቦ በደቡባዊ ኢራን የፍለጋ እና የመታደግ ዘመቻ ሲያካሂድ ይታያል።

    በደቡባዊ ኢራን የሚገኘው ኮህጊሉዬህ እና ቦየር አህመድ ግዛት አስተዳዳሪ፤ የተመታውን የአሜሪካ ጄት አብራሪ “በሕይወት መያዝ” ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

    “የጠላት ኃይልን መያዝ ወይም መግደል የተሳካላቸው ሰዎች በተለየ ሁኔታ በአስተዳደሩ ጽህፈት ቤት ይመሰገናሉ” ማለታቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

  7. ኢራን ውስጥ ስለወደቀው ተዋጊ ጄት መታወቅ ያለባቸው ጉዳዮች

    ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለጠፈ እና ኢራን ውስጥ የወደቀው የአሜሪካ ተዋጊ አውሮፕላን ስብርባሪ የሚያሳይ ምሥል የተከሰከሰው “ኤፍ-15ኢ ስትራይክ ኢግል” የጦር ጄት እንደሆነ ያመለክታል።

    የዚህ ጄት ዝርያዎች ከአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበረ ቢሆንም “ኤፍ-15ኢ” ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀው በ1988 ነው። የአንዱ ጄት ዋጋ 100 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነው።

    እንዲህ ዓይነቶቹ ተዋጊ ጄቶች የሚሠሩት ከአየር ወደ ምድር እንዲሁም የአየር ለአየር ተልዕኮዎች እንዲወጡ ተደርጎ ነው።

    የአሜሪካው ጄት ኢራን ውስጥ ድሮኖችን እና ክሩዝ ሚሳዔሎችን ለመምታት ለመከላከያ የአጸፋ የአየር ጥቃት ተጉዞ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

    ጄቱ ከአየር ወደ ምድር ጥቃት በሚፈጽምበት ወቅት ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት ዒላማው ላይ ጨረር የማስቀመጥ እንዲሁም በጂፒኤስ የሚመሩ ትክክለኛ ዒላማ መቺ ተተኳሾችን እና ሌሎች ቦንቦችን የመያዝ አቅም አለው።

    የጦር አውሮፕላኑ ሁለት ሰዎችን መያዝ ይችላል። ጄቱን የሚያበርረው ፓይለት ከፊት የሚቀመጥ ሲሆን የመሣሪያ ሥርዓት መኮንኑ ደግሞ የኋለኛው መቀመጫ ላይ ይሆናል።

    የመሣሪያ ሥርዓት መኮንኑ ከፊት ለፊቱ አራት ስክሪኖች ይኖሩታል። ዒላማዎችን የመምረጥ እና ለጥቃት ዒላማው ተገቢ የሆነው መሣሪያ በአግባቡ መዘጋጀቱን የማረጋገጥ ኃላፊነቶችን ይወጣል።

    ተዋጊ ጄቱ ሁለት ሰዎችን የሚጭን መሆኑ የሥስራ ክፍፍል እንዲኖር ያስችላል። በተለይም አብራሪው ከጠላት ለማምለጥ በሚሞክርበት አስጨናቂ የአየር ከባቢ ውስጥ ጠቃሚ ነው።

    የአሜሪካውን ተዋጊ ጄት እንዲወድቅ ያደረገው ትክክለኛ ነገር ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ያዳግታል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ እንደገለጸው መትቶ ጥሎት ከሆነ ጄቱን የመታው ከምድር ወደ አየር የተወነጨ ሚሳዔል የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው።

    “በኢንፍራ ሬድ’ ጨረር የሚመራው የአጭር ርቀት ሚሳዔል ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ይችላል። በቶሎ ማዘዋወር የሚቻል በመሆኑም ኢራን ውስጥ በሚካሄዱ ዘመቻዎች ላይ ከፍተኛ ስጋትን መደቀኑን ቀጥሏል።

    ጥቃት የተሰነዘረባቸው ተዋጊ ጄቶች የሚቃጠል ጭስ በመልቀቅ ከምድር ላይ የተነሳው ሚሳዔል ዒላማዋን እንዲስት በማድረግ ራሳቸውን ለመከላከል ይሞክራሉ።

    በዚህ ጦርነት ውስጥ የአሜሪካ ወታደራዊ አዛዦች በኢራን የተለያዩ ክፍሎች ላይ የአየር የበላይነት እንዳላቸው ሲናገሩ ነበር።

    ነገር ግን ጄቱ ተመትቶ እንደወደቀ የሚረጋገጥ ከሆነ አሁንም ኢራን ለአሜሪካ የጦር ጄቶች ምን ያህል አደጋ መጋረጥ እንደምትችል ያሳያል።

  8. ዶክተር ቴድሮስ በኢራን ከ20 በላይ የጤና ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አረጋገጡ

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ከ20 በሚበልጡ የኢራን የሕክምና እና የጤና ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸሙን የዓለም ጤና ድርጅት አረጋገጠ።

    በዚህም በተቋማቱ ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ አንድ የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ እና ሌላ የኢራን ቀይ ጨረቃ ማኅበር ሠራተኛን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል።

    የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በኤክስ ገጻቸው ላይ ባወጡት መግለጫ ከጥቃቶቹ መካከል በቴህራን የሚገኘው ፓስተር ኢኒስቲትዩት እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።

    ኢኒስቲትዩቱ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ በኢራን የሕብረተሰብ ጤና አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ሚና እንደነበረው በመግለጽ ከባድ ጉዳት ስለደረሰበት ከዚህ በኋላ የሕክምና እና የጤና አገልግሎቶችን የማይሰጥበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

    ዶክተር ቴድሮስ በተለያዩ የኢራን አካባቢዎች ጉዳት የደረሰባቸው የተወሰኑ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ፣ የመድኃኒት ማምረቻዎች እና ምርምር የሚካሄድባቸው ተቋማትን በስም በመጥቀስ የደረሰውን ጥቃት አስረድተዋል።

    የእስራኤል ጦር፤ በመድኃኒት ማምረቻው ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ በሰጠው ምላሽ ተቋሙ “የኬሚካል ጦር መሳሪያዎችን” ለመሥራት የሚውሉ “ኬሚካሎችን በማስተላለፍ ረገድ ተሳታፊ ነው” ሲል ለጥቃቱ ምንያት አቅርቧል።

  9. ኔትያናሁ የኢራንን 70 በመቶ ገደማ ብረት የምርት አቅምን "አውድመናል" አሉ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔትያናሁ አገራቸው በፈጸመቻቸው ጥቃቶች 70 በመቶ ገደማ የሚሆነው የኢራን ብረታ ብረት የማምረት አቅም መውደሙን ተናገሩ።

    ኔትያናሁ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በለቀቁት ቪዲዮ፤ በዚህ “ታላቅ ስኬት” የእስላማዊ አብዮታዊ ዘቡን የፋይናንስ እና ወታደራዊ ሀብት ደምስሰናል ብለዋል።

    “በእኔ እና በፕሬዝዳንት ትራምፕ መካከል፣ በእስራኤል መከላከያ ሠራዊት እና በአሜሪካ ሠራዊት መካከል ባለው ሙሉ ትብብር አማካኝነት ኢራንን ማድቀቃችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።

    እስራኤል የሊባኖሱን ታጣቂ ቡድ ን"ሄዝቦላህን እግር እግሩን መምታት" እንደምትቀጥልም አክለዋል።

  10. አሜሪካ በኢራን ግዛት ውስጥ ተመትቶ የወደቀ ተዋጊ ጄቷን አብራሪዎችን ለማግኘት ፍለጋ ላይ መሆኗ ተዘገበ

    በኢራን ጥቃት ለመፈጸም ተሰማርቶ የነበረ የአሜሪካ ተዋጊ አውሮፕላን ተመትቶ እንደወደቀ እና አብራሪዎቹን ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢራን እና የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል፤ አሜሪካ የኢራን ግዛት ውስጥ ተከስክሷል የተባለውን ተዋጊ ጄት አብራሪዎች እየፈለገች ነው ሲል ዘገበ።

    በተጨማሪ አክሲዮስ፣ ሮይተርስ እ ኒው ዮክ ታይምስ አንድ የአሜሪካን ባለሥልጣናን ጠቅሰው አውሮፕላኑ ተመትቶ መውደቁን እና አብራሪዎቹን ለማግኘት ፍለጋ እየተደረገ መሆኑን ዘግበዋል።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ፤ የአንድ ተዋጊ ጄት ሆርሙዝ ወሽመጥ ውስጥ በሚገኘው ቃሽም ደሴት ተመትቶ ወድቋል የሚለውን የአብዮታዊ ዘቡን መረጃ ሐሙስ ዕለት አስተባብሎ ነበር።

    የማዕከላዊ ዕዙ መግለጫ ያስተባበለው ከሰሞኑ የወጡ የኢራን ዘገባዎችን ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም። ቢቢሲ ከዕዙ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ጠይቋል።

    ታስኒም ዜና ወኪል ባወጣው ዘገባ፤ የአሜሪካ ኃይሎች ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ የተዋጊ ጄት አብራሪያዎችን ለማግኘት የፍለጋ ዘመቻ እያከናወኑ ነው ብሏል።

    ዎል ስትሪት ጆርናል በበኩሉ አሜሪካ የተዋጊ ጄቱን አብራሪዎችን ለማግኘት የአሜሪካ ኃይሎች ዘመቻ እያካሄዱ መሆናቸውን ዘግቧል።

    የኢራኑ ታስኒም፤ ፍለጋው የሚከናወነው ሄሊኮፕተሮች፣ አውሮፕላኖች እና የቅኝት ድሮኖችን በመጠቀም እንደሆነም ምንጮችን በመጥቀስ ዘግቧል። የፍለጋ ጥረቱ ግን ፍሬ አላፈራም ብሏል።

    በታስኒም ዘገባ መሠረት፤ የአሜሪካ ተዋጊ ጄት ሲመታ አብራሪዎቹ ከአውሮፕላኑ ወጥተው በኢራን ግዛት ውስጥ አርፈዋል።

    አንድ ኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ በበኩሉ አብራሪዎቹን በሕይወት ለያዘ ሰው ሽልማት አንደሚሰጥ ዘግቧል።

    ቢቢሲ እነዚህን መረጃዎች በገለልተኝነት አላረጋገጠም፤ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማሰባሰብ እየሠራ ነው።

    የጦር አውሮፕላኑ ወድቆበታል የተባለው የኢራን ግዛት ባለሥልጣናት አሜሪካዊውያኑን አብራሪዎች ለመያዝ ለነዋሪዎች ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ የአካባቢው ነጋዴዎች ደግሞ አብራሪዎቹን ላገኘ ከ50 ሺህ ዶላር በላይ የሚሆን የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጡ አሳውቀዋል።

  11. ትራምፕ አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥን “በቀላሉ” መክፈት ትችላለች አሉ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ አሜሪካ በኢራን የተዘጋውን የሆርሙዝ ወሽመጥ “ከትንሽ ተጨማሪ ጊዜ ጋር በቀላሉ” ልትከፍተው ትችላለች አሉ።

    ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ “ከትንሽ ጊዜ ጋር፤ በቀላሉ የሆርሙዝ ወሽመጥን መክፈት፣ ነዳጁን መውሰድ እና ሀብት ማግኘት እንችላለን” ብለዋል። አክለውም፤ ወሽመጡ “ለዓለም [ነዳጅ] ‘ጉድጓድ’ ይሆን?” በማለት ጽፈዋል።

    በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የተከፈተባት ኢራን፤ ሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷን ተከትሎ የዓለም የነዳጅ አቅርቦት እና ዋጋ ቀውስ ውስጥ ገብቷል። ይህንን ችግር እንዲፈቱ የሚደረገው ጫና የበዛባቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ሆርሙዝ እንዴት ሊከፈት ይችላል የሚለውን በተመለከተ የተለያዩ ሃሳቦችን ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።

    ምዕራባውያን አገራት የራሳቸውን ወታደራዊ አማራጭ በመጠቀም በወሳኙ ኮሪደር በኩል ነዳጅ እንዲተላለፍ እንዲያደርጉም እየጠየቁ ነው። በርካታ አገራት ይህንን አማራጭ አልተቀበሉትም።

    ትራምፕ ረቡዕ ዕለት ባደረጉት ንግግር በኢራን የሚገኙ የሲቪል ኃይል ማመንጫዎችን እንደሚመቱ ዝተዋል። ከዚህ ንግግራቸው በኋላ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ የጨመረ ሲሆን ኢራንም አጸፋውን እንደምትመልስ ተገዝታለች።

  12. በእስራኤል ጥቃት የተፈናቀሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሊባኖሳውያን ሕይወትን እንዴት እየገፉት ነው?

    ሊባኖስ ውስጥ 1.1 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በእስራኤል ጥቃቶች የተነሳ ከመኖሪያቸው እንደተፈናቀሉ የተባበሩት መንግሥታትመረጃ ያመለክታል።

    እስራኤል በበኩሏ ዒላማ የምታደርገው አማጺውን ቡድን ሄዝቦላህ እና መሠረተ ልማቶቹን እንደሆነ ትናገረች።

    ይሁን እንጂ የእስራኤል መንግሥት ድንበር አካባቢ የሚገኙ እስራኤላውያን ደኅንነት እስከሚጠበቅ ድረስ የተፈናቀሉ ሰዎች እንደማይመለሱ እና በመንደሮቹ የሚገኙ ቤቶችን እንደሚያፈርስ አስታውቋል።

    የቢቢሲ ‘ኒውስዴይ’ ራዲዮ ፕሮግራም ሊባኖስ ውስጥ የማኅበራዊ ሠራተኛ የሆነችውን ራባብ ኻድጃን አነጋግሯል።

    ኻድጃ ከዋና ከተማዋ ቤይሩት በስተምሥራቅ ባለው ማውንት ሊባነን ውስጥ በሚገኝ የተፈናቃዎች ማዕከል ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት እያገለገለች ነው።

    “ከአሁኑ በርካታ ሰዎች ንግዳቸውን፣ ቤታቸውን እና የገቢ ምንጫቸውን አጥተዋል” ስትል ለቢቢሲ ኒውስዴይ ተናግራለች።

    ኻድጃ እንደምታስረዳው ነዋሪዎች የተፈናቃይ ጣቢያዎቹን ምግብ፣ የሚጠጣ ውሃ፣ የንጽህና መጠበቂያ ቁሶችን እና ልብሶችን ለመጠየቅ ይጠቀሙባቸዋል። አብዛኞቹ እነዚህ ወሳኝ ነገሮች የሚሠራጩት በአገሪቱ መንግሥት፣ በአካባቢ አስተዳደሮች እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እንደሆኑ ገልጻለች።

    “እንደ ማንኛውም ጊዜ ሁሉ የሊባኖስ ማኅበረሰብ አንዱ ቁልፍ መገለጫ ማኅበራዊ አጋርነት ነው” ብላለች። “በርካታ ግለሰቦች” የተፈናቃዮችን ፍላጎት ለማሟላት ገንዘብ እያሰባሰቡ መሆኑንም አንስታለች።

    ይሁን እንጂ በግለሰቦች ደረጃ የሚደረግ እርዳታ ለረጅም ጊዜ አይቆይም የሚል ስጋቷን ገልጻለች።

    “ያለው ፍላጎት እና ሰዎች ወደ ቅዬአቸው መመለስ ይችሉ እንደሆነ ባለመወቃቸው የተፈጠረው ፍርሃት እየጨመረ ነው” ብላለች።

    "ተፈናቃይ ያልሆኑት እንኳ የሁኔታው አለመረጋጋት ፍርሃት ላይ ጥሏቸዋል" ስትል ሁኔታውን ገልጻለች።

  13. የአሜሪካ ጫና የበረታባት ኩባ ከሁለት ሺህ በላይ እስረኞችን ልትፈታ ነው

    ከአሜሪካ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ጫና እየደረሰባት ያለችው ኩባ፤ “ሰብአዊነት እና ሉዓላዊነትን” ለማሳየት ስትል 2,010 ታሳሪዎችን እንደምትለቅቅ አስታወቀች።

    ከሚፈቱት ታሳሪዎች መካከል የውጭ ዜጎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ አዛውንቶች እንደሚገኙበት በአሜሪካ የሚገኘው የኩባ ኤምባሲ ገልጿል።

    እንደ ኤምባሲው ገለጻ፤ ይህ እርምጃ የሚወሰደው በአገሪቱ “የፍትሕ ሥርዓት ልማዳዊ አሠራር መሠረት” እስረኞቹ እንዲለቀቁ በሚደረግበት “ቅዱስ ሳምንት ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል አውድ ውስጥ” ነው።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ ፕሬዝዳንት ከሆኑ አንስቶ የኩባ አመራር እንዲለወጥ እንደሚፈልጉ በግልጽ ተናግረዋል።

    በአገሪቱ ላይ የከፋ የነዳጅ እጥረት እና ሠፊ የኃይል መቋረጥ እንዲፈጠር ያደረገ የነዳጅ እገዳም ጥለዋል።

    ከጥር ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ሳምንት ላይ ባለቤትነቱ የሩሲያ የሆነ መርከብ 730 ሺህ በርሜል የሚገመት ድፍድፍ ነዳጅ ጭኖ ወደ ኩባ ተጉዟል።

    የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኑ ሂውማት ራይትስ ዎች እንደሚገልጸው ኩባ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ ታሳሪዎች አሉ። የአገሪቱ መንግሥትን የሚተቹ ሰዎች ለእንግልት እና ለወንጀል ክስ እንደሚዳረጉም ይነገራል።

    አሁን ለመፈታት ብቁ የሆኑት ታሳሪዎች የተለዩት የፈጸሙትን ድርጊት በተመለከተ “በጥንቃቄ በተካሄደ ትንተና” እንዲሁም “እስር ቤት እያሉ በነበራቸው መልካም ጠባይ፣ ከፍርድ ዓመታቸው አብዛኛውን በማጠናቀቃቸው እና በጤና ሁኔታቸው” ላይ በመመሥረት እንደሆነ የኤምባሲው መግለጫ ያስረዳል።

    የኩባ መንግሥት እስረኞችን እንደሚፈታ ሲገልጽ በዚህ ዓመት ይህ ሁለተኛው ነው። በመጋቢት መጀመሪያ የአገሪቱ መንግሥት ከቫቲካን ጋር ከተነጋረ በኋላ 51 እስረኞችን ፈትቷል። 2025 ላይ ደግሞ በቫቲካን እና አሜሪካ አሸማጋይነት 553 ሰዎች ተፈትተዋል።

  14. ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የዓለም የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ጨምሯል - ተመድ

    አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር እያደረጉት ባለው ጦርነት ምክንያት በዓለም ዙሪያ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ መጨመሩን የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ድርጅት አስታወቀ።

    የመንግሥታቱ ድርጅት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) በዓለም ዙሪያ ያለውን የምግብ ሸቀጦች ዋጋን በተመለከተ በየወሩ የሚያወጣው የምግብ ሸቀጦች ዋጋ አመልካች ዝርዝር ላይ በየካቲት እና በመጋቢት ወራት የ2.4 በመቶ ጭማሪ መታየቱን ገልጿል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት በነዳጅ ምርቶች ላይ ከተከሰተው የዋጋ መወደድ የተነሳ የምግብ ሸቀጦች ዋጋም ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ መጨመሩን አመልክቷል።

  15. የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ ባሕር ላይ እየተጉላሉ ያሉት ከ20 ሺህ በላይ የመርከብ ሠራተኞች

    በሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ምክንያት ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ አገራት ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ የነዳጅ፣ የጋዝ እና የማዳበሪያ ምርቶች መንቀሳቀስ አለመቻላቸው እየተነገረ ነው።

    እነዚህን ተፈላጊ ምርቶች ለማጓጓዝ የመተላላፊያው መከፈትን በሚጠባበቁት መርከቦች ላይ የሚገኙ በሺዎች ስለሚቆጠሩ መርከበኞች እንግልት ብዙም እየተባለ አይደለም።

    በኢራን እና በኦማን መካከል የሚገኘው የሆርሙዝ ወሽመጥን መከፈት በመጠባበቅ በባሕር ላይ እየተጉላሉ ባሉት ከሁለት ሺህ በሚበልጡ የጭነት መርከቦች ላይ የሚገኙት መርከበኞች በርካታ ሳምንታትን አሳልፈዋል።

    መርከበኞቹ እና መርከቦቹ ከገጠማቸው መንገላታት በተጨማሪ በአካባቢው በሚካሄደው ጦርነት ለጥቃት የተጋለጡ ናቸው። 35ኛ ቀኑን በያዘው ጦርነት ውስጥ እስካሁን 21 የንግድ መርከቦች በባሕረ ሰላጤው ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

    ዓለም አቀፉ የባሕር ትራንስፖርት ድርጅት እንዳለው በጥቃቶቹ 10 ባሕርተኞች የተገደሉ ሲሆን፣ በርካቶች ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    በሰላጤው አገራት ወደቦች እና የባሕር ክልሎች ውስጥ መልህቆቻቸውን ጥለው ባሉ መርከቦች ላይ ከ20 ሺህ የሚበልጡ ባሕርተኞች ይገኛሉ። ድርጅቱ እንዳለው የመርከቦቹ ሠራተኞች በአሁኑ ወቅት ያላቸው ምግብ እና ውሃ እየተሟጠጠ ሲሆን በመሰላቸት እና በጭንቀት ውስጥ ናቸው።

    ጦርነቱ እንዲቆም እና የሆርሙዝ ወሽመጥ ተከፍቶ መርከቦቹ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ባሕርተኞቹ የሚወጡበት መንገድ እንዲፈጠር የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ ጠይቀዋል።

  16. በኩዌት የውሃ ማጣሪያ እና የኤሌትሪክ ማመንጫ ተቋማት ላይ ጥቃት ተፈጸመ

    የኩዌት ኤሌትሪክ እና ውሃ ሚኒስትር ኢራን የኃይል ማመንጫ እና የውሃ ማጣሪያ ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀ።

    ሚኒስቴሩ አክሎም ጥቃቱን ተከትሎ በተወሰኑ የተቋማቱ ክፍሎች ላይ “ቁሳዊ ጉዳት” መድረሱን ገልጿል።

    ሚኒስትሩ በኤክስ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ የድንገተኛ ሠራተኞች እና የቴክኒክ ባለሙያዎች ወደ አካባቢው መሠማራታቸውን እና "አቅርቦቱን በተገቢው መንገድ ለማስቀጠል” ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

    መግለጫው አክሎም “የኤሌትሪክ እና የውሃ አቅርቦት ሥርዓታችን ደኅንነት እና መረጋጋት ቅድሚያ ከምንሰጣቸው ነገሮች መካከል ነው” ብሏል

    ዛሬ ማለዳ የኢራን ድሮኖች በኩዌት የነዳጅ ማጣሪያ ላይ በተደጋጋሚ የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ እሳት መነሳቱ ተገልጿል።

    መካከለኛው ምሥራቅ በጣም ሞቃታማ በመሆኑ የነዋሪዎቹ የዕለት ተዕለት ሕይወት በኤሌትሪክ ኃይል እና በውሃ ማጣሪያዎች ላይ የተመሠረተ ነው።

    በእነዚህ አገራት ለመጠጥነት የሚውለው 90 በመቶ የሚሆነው ውሃ የሚገኘው ከሚጣራ ጨዋማ የባሕር ውሃ ነው።

    የባሕረ ሰላጤው አገራት ያለ ውሃ ማጣሪያ ማዕከላት ለኑሮ የማይመቹ ይሆናል።

    ለቀጣናው አገራት በውሃ ማጣሪያዎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ከባድ ጭንቀት ነው።

    ለረዥም ጊዜ እነዚህ ትናንሽ አገራት በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ የግጭት አካል ሳይሆኑ በመቆየታቸው ይህ ስጋታቸው አልነበረም። አሁን ግን ሁኔታው ተቀይሯል።

  17. ከ100 በላይ የዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች ስለ ኢራን ጦርነት ያላቸውን ስጋት የሚገልጽ ግልጽ ደብዳቤ ጻፉ

    ከ100 በላይ የሚሆኑ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያዎች በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት አሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ ከፍተኛ ጥሰት መፈጸማቸውን ይህም "ከፍተኛ ስጋት" እንደፈጠረባቸው በማመልከት ግልጽ ደብዳቤ ጻፉ።

    በደብዳቤው ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት ባለሙያዎች የቀድሞ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት እና የዓለም አቀፍ ሕግ ፕሮፌሰሮች መሆናቸው ተጠቅሷል።

    ግልጽ ደብዳቤውን የጻፉት እነዚህ ምሁራን እና የቀድሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክንያት ትኩረታቸው በአሜሪካ አሠራር ላይ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።

    የሕግ ባለሙያዎቹ በጦርነቱ ወቅት የአሜሪካ ድርጊትም ሆነ ንግግር እጅግ አሳሳቢ እና በአንዳንድ ሁኔታዎችም የዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ ነው ብለዋል።

    በኢራን ላይ የተከፈተው ጥቃት የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተር በግልጽ የሚጥስ መሆኑን ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።

    ባለሙያዎቹ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የሚጠቀሙበትን "አስደንጋጭ ንግግር" የጠቀሱ ሲሆን፣ ይህም የፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢራንን የኃይል ማመንጫዎች "ለማውደም" የሰነዘሩትን ዛቻ ያካተተ ነው።

    በተጨማሪም በጦርነቱ የመጀመሪያ ቀን በኢራን ሚናብ በተባለ ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ባለሙያዎቹ በደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰዋል።

    በትምህርት ቤቱ ላይ የተፈጸመው ጥቃት በአሜሪካ ጦር የተፈጸመ መሆኑን ማስረጃዎች ያሳያሉ።

    ባለሙያዎቹ ይህ የአሜሪካ ጥቃት በማስረጃ የሚደገፍ ከሆነ ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከል ነው ያሉ ሲሆን፣ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ግድየለሾች መሆናቸውን ያሳያል ብለዋል።

    የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ለተጻፈው ግልጽ ደብዳቤ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ ትራምፕ "መላውን ቀጣና የበለጠ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና የተረጋጋ እያደረጉ ነው" ብለዋል።

    ቃል አቀባዩ አክለውም "ፕሬዝዳንቱ እነዚህን እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆኑ የብሔራዊ ደኅንነት ውሳኔዎችን የሚወስኑት በእነዚህ 'ባለሙያ' ተብዬዎች አስተያየት ላይ ተመሥርተው ሳይሆን የአሜሪካን ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ ነው" ብለዋል።

  18. አሜሪካንን በ34 ቀናት ውስጥ 38 ቢሊዮን ዶላር ያስወጣው የኢራን ጦርነት

    አስከ ሐሙስ መጋቢት 24/2018 ዓ.ም. ድረስ 34 ቀናት ባስቆጠረው የኢራን ጦርነት ላይ አሜሪካ ወደ 38 ቢሊዮን ዶላር እንዳወጣች ዘገባዎች እያመለከቱ ሲሆን ይህም በቀን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑ ተገልጿል።

    ጦርነቱ ከተጀመረበት ቅዳሜ የካቲት 21 አስከ ሐሙስ መጋቢት 24/2018 ዓ.ም ድረስ አሜሪካ ለጥቃቱ ማካሄጃ እና ከኢራን የሚተኮሱ ሚሳዔሎችን ለመከላከያ ከ26 ቢሊየን ዶላር እስከ 38 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጓ ተገምቷል።

    በዚህም የተነሳ አሜሪካ በኢራን ላይ በምታካሂደው ወታደራዊ ዘመቻ ምክንያት በየቀኑ ከ890 ሚሊዮን ዶላር አስከ 1 ቢሊየን ዶላር ወጪ ታደርጋለች።

    በኢራን ላይ ጥቃቱ በተከፈተባቸው በመጀመሪያዎቹ ቀናት ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቁ የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ እንደዋሉ የስትራቴጂክ እና የዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል አመልክቷል።

    ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ በነበሩት በመጀመሪያዎቹ 100 ሰዓታት ጥቅም ላይ የዋሉትን በአብዛኛው ውድ የሆኑትን የአየር ጥቃት መከላከያ የጦር መሳሪያዎች መልሶ ለማሟላት 3.1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስጣ ማዕከሉ ገምቷል።

  19. የኩዌት ነዳጅ ማጣሪያ ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ለሦስተኛ ጊዜ ጥቃት ደረሰበት

    የኩዌት የነዳጅ ማጣሪያ አርብ ማለዳ በተደጋጋሚ በኢራን ድሮኖች ጥቃት ከደረሰበት በኋላ እሳት መነሳቱ ተገለፀ።

    እስካሁን ድረስ ስለደረሰው የጉዳት መጠን ምንም የተባለ ነገር የለም።

    ሚና አል አህማዲ በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ ግዙፍ የነዳጅ ማጣሪዎች መካከል አንዱ ነው።

    ይህ የነዳጅ ማጣሪያ በቀን 346,000 በርሜል ነዳጅ ያጣራል።

    ኩዌት ሦስት ዋና ዋና የነዳጅ ማጣሪያዎች ያሏት ሲሆን፣ ሚና አል አህማዲ ለአምስት ሳምንት በቀጠለው ጦርነት ውስጥ በኢራን ድሮኖች ለሁለተኛ ጊዜ ጥቃት ደርሶበታል።

    የኩዌት ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን የድንገተኛ እና የእሳት አደጋ ሠራተኞች የተነሳውን እሳት ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ መሆኑን አስታውቋል።

  20. አሜሪካ በኢራን ጦርነት ምን ያህል እያወጣች ነው?

    አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ እያካሄደች ያለው ጦርነት ከፍተኛ ወጪ እያስወጣት ይገኛል።

    ፔንታጎን ጦርነቱ በተጀመረባቸው ስድስት ቀናት ብቻ 11.3 ቢሊዮን ዶላር እንዳስወጣው ለሕግ አውጪዎች ሪፖርት አድርጓል።

    ጦርነቱ እየቀጠለ ሲሄድ ደግሞ አሜሪካ በየዕለቱ የምታወጣው ወጪ እየተለያየ ይሄዳል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለጦርነቱ የሚወጣው ገንዘብ የኢራን የመከላከያ አቅም እየተዳከመ ስለሄደ መቀነሱ አይቀርም ይላሉ።

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ኢራን የምታስወነጭፋቸው ሚሳዔሎች እና ድሮኖች በከፍተኛ ቁጥር መቀነሳቸውን ይናገራል።

    በጦርነቱ አሜሪካ በኢራን በሚገኙ ዒላማዎች ላይ የተጠቀመቻቸው ቶምሀውክ የተሰኘ ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔሎች እያንዳንዳቸው 3.5 ሚሊዮን ዶላር ያወጣሉ።

    ነገር ግን ባለሙያዎች ጦርነቱ 385 ሚሊዮን ዶላር በቀን እንደሚያስወጣ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።