በየመን የሚካሄደው ጦርነት ዋነኛ ተዋናዮች እነማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, EPA
በየመን የሚካሄደው ጦርነት ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ ለዓመታት ቆይቷል። በዚህም በኢራን የሚደገፉት ሁቲ ታጣቂዎች እና ሳዑዲ በምትመራው ጥምረት የሚደገፈው የአገሪቱ መንግሥት የመንን ለሁለት ተካፍለው የበላይነት ለመያዝ ሲፋለሙ ቆይተዋል።
ሁለቱ ወገኖች ለዓመታት በተለያዩ አጋጣሚዎች እየተዋጉ የቆዩ ቢሆንም ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ ግን ግጭቱ እየተባባሰ ነው።
ኢራን ከአሜሪካ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቷ እና ሳዑዲ አረቢያ ለየመን መንግሥት የምታደርገው ድጋፍ መጠናከርን ተከትሎ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ፍጥጫ ሰፍቷል።
ሳዑዲ የሁቲ ተቀናቃኝ የየመን ኃይሎችን ከመደገፍ ባሻገር ባለፉት ወራት የሁቲ ይዞታዎችን በአየር ማጥቃቷ ከሁቲ ኃይሎች ተከታታይ የአጸፋ ጥቃትን አስከትሎባታል።
በአሁኑ ጊዜ ሁቲዎች እየተጠናከሩ በሳዑዲ የሚደገፈውን የየመን መንግሥትን በማዳከም ወሳኝ የባሕር ዳርቻዎችን እና ደሴቶችን እየተቆጣጠሩ ነው።
ለመሆኑ በዚህ የየመን ቀውስ ውስጥ ዋነኛ ተዋንያኑ እነማን ናቸው?
“አንሳር አላህ” የሁቲ ኃይሎች
የኢራን አጋር የሆኑት ሁቲዎች ዋና ከተማዋን ሰነዓን ጨምሮ ሰፊ የአገሪቱን ግዛቶች የሚቆጣጠሩ ናቸው። ሁቲዎች ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን የታጠቁ ሲሆን፣ በቀይ ባሕር ላይ ጉልህ ተጽእኖን ማሳደር የሚችሉ መሆናቸውን አሳይተዋል። ከየመን አልፈውም በቀይ ባሕር ላይ፣ በሳዑዲ አረቢያ እና አስከ እስራኤል የሚደርስ ጥቃት የመፈጸም አቅም አላቸው።
ሳዑዲ አረቢያ
የየመን ተጎራባች የሆነችው ሳዑዲ የአረብ አገራትን ወደታራዊ ጥምረት በመምራት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለውን የየመን መንግሥት ለመደገፍ በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ ናት። በዚህም ሳቢያ ከሁቲ ኃይሎች ጋር በየመን ውስጥ እና ድንበር ተሻጋሪ ግጭት ውስጥ ገብታለች።
ፕሬዝዳንታዊ ምክር ቤት
ፀረ ሁቲ የሆነው እና የሳዑዲ እና የሌሎችም አገራት ዕውቅና ያለው የየመን መንግሥት ነው። በአገሪቱ የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም በየመን ፖለቲከኞች እና ወታደራዊ መኮንኖች የሚመራ ነው። ነገር ግን የሁቲ ታጣቂዎችን ለመቆጣጠር የተሳ ሲሆን ባለፉት ሳምንታት በታጣቂዎቹ በደረሰበት ጫና በርካታ አካባቢዎችን በሁቲ ኃይሎች ተነጥቋል።
የኢስላህ ፓርቲ
ሌላኛው ፀረ ሁቲ ቡድን ኢስላህ ፓርቲ ከየመን መንግሥት ጋር የሚሠራ ሲሆን፣ በየመን ፖለቲካዊ እና ወደታራዊ ቀውስ ውስጥ የራሱ ሚና አለው።
የየመን ብሔራዊ ኃይሎች
ይህ ናሽናል ሬዚስራንስ ፎርስስ የሚባለው ኃይል በሳዑዲ የሚደገፍ የወታደራዊ ኃይሎች ስብስብ ነው። አቋሙ ፀረ ሁቲ ሲሆን ከሌሎች የየመን ፖለቲካዊ ኃይሎች ጋር የሚሠራ ነው።
በጥቅሉ ሲታይ በየመን ውስጥ የተለያዩ ኃይሎች ያሉ ቢሆንም ከሁቲ ታጣቂዎች በስተቀር ቀሪዎቹ አቋማቸው በአንድ ሊጠቃለል የሚችል የፖለቲካ እና ወታደራዊ ስብስቦ ችናቸው። ስለዚህም ሁቲዎች የሚፋለሙት ተመሳሳይ ዓላማ እና ድጋፍ ካላቸው ኃይሎች ጋር ነው ሊባል ይችላል።


























