በኬንያ ፀረ- ተባይ ኬሚካል የተረጨበት ቲማቲም ለ15 ዝሆኖች ሞት ምክንያት እንደሆነ ተገለጸ
በደቡባዊ ኬንያ፣ አምቦስሊ ብሔራዊ ፓርክ አቅራቢያ ሞተው የተገኙት 15 ዝሆኖች በአካባቢው ከሚገኝ እርሻ ፀረ-ተባይ ኬሚካል የተረጨበት ቲማቲም በመመገባቸው ሳይመረዙ እንዳልቀረ ተገለጸ።
የአገሪቷ የዱር እንስሳት ጥበቃ አገልግሎት እንዳለው ከዝሆኖቹ በተወሰደ ናሙና ላይ በተደረገ የመጀመሪያ ደረጃ የቤተ ሙከራ ምርመራ ‘ሳይናይድ’ የተባለ ኬሚካላዊ ውህድ ተገኝቷል።
ኬሚካሉ በተወሰኑ እፅዋት እና ምግቦች ውስጥ የሚገኝ እንዲሁም በኢንደስትሪዎች ጥቅም ላይ የሚውል ነው።
ከዝሆኖች መካከል አስሩ የመንቀሳቀስ ችግር አጋጥሟቸው የተገኙ ሲሆን፣ በሁለት ቀናት ውስጥ ሞተዋል።
ቀሪዎቹ አምስቱ ግን ሕይወታቸው አልፎ ነበር የተገኙት። በክስተቱ ላይ የሚካሄደው ምርመራ እንደቀጠለ ነው።
የዝሆኖቹ ሞት ያጋጠመው ከአውሮፓውያኑ ሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24 ባለው አንድ ወር ውስጥ እንደሆነም የዱር እንስሳት ጥበቃ አገልግሎቱ ገልጿል።
ክስተቱ ዝሆኖች ምግብ እና ውሃ ለመፈለግ በሚንቀሳቀሱበት የፓርኩ አቅራቢያ እየተስፋፋ ባለው የእርሻ እንቅስቃሴ ላይ ስጋት እንዲፈጠር አድርጓል።
ፓርኩ እና አካባቢው አምቦስሊ ሥነ ምኅዳር በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ በዱር እንስሳት ሃብቷ ከምትታወቀው ታንዛኒያ ጋር የሚያዋሰን ሰፊ አካባቢ ነው።
ባለሥልጣናት እንዳሉት አደንን በማስቆም የተሳካ ውጤት በተመዘገበበት በቀጠናው፣ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ዝሆኖች ሞት ሲመዘገብ በአስርተ ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያው ነው።
በአምቦስሊ ብሔራዊ ፓርክ እና አካባቢው ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ዝሆኖች እንደሚገኙበት ይገመታል።