የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤
አሜሪካ ያለ ምንም ተጠያቂነት እየተንቀሳቀሰች ነው፤ ኃይሏም ከዓለም አቀፍ ሕግ የበለጠ ዋጋ እንዳለው ታምናለች ሲሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ዋና ጸኃፊው ከቢቢሲ ሬዲዮ 4 ‘ቱዴይ’ ፕሮግራም
ላይ በነበራቸው ቃለ መጠይቅ፤ አሜሪካ የባለብዙ ወገን መፍትሔዎች ጥቅም አልባ ናቸው የሚል "ግልጽ ድምዳሜ” ይዛለች ሲሉ ተችተዋል።
በአሁኑ ወቅት ያለው የዋሽንግተን ፖሊሲ፤
"የአሜሪካን ኃይል እና ተጽእኖ መጠቀም፤ አልፎ አልፎ ደግሞ ዓለም አቀፍ ሕግችን ማክበር" የሚል ነው ብለዋል።
ጉቴሬዝ ይህንን አስተያየት የሰጡት፤ አሜሪካ
ቬንዙዌላ ውስጥ ባካሄደችው ዘመቻ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ከያዘች ከሳምንታት በኋላ እንዲሁም ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን
ለመጠቅለል ደጋግመው እየዛቱ ባለበት ወቅት ነው።
እንደ የአባል አገራት እኩልነት ያሉ የተባበሩት
መንግሥታት ምስረታ መርሆዎች በአሁን ሰዓት በአደጋ ላይ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ጉቴሬዝ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ፕሬዝዳንት ትራምፕ በተባበሩት መንግሥታት
ላይ ጠንካራ ትችቶችን ሲያሰሙ ቆይተዋል።
ባለፈው መስከረም በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት
ንግግሩም የድርጅቱ መኖር ዓላማ ጥያቄ አንስተዋል። "ሰባት ሊቋጩ የማይችሉ ጦርነቶችን" ለብቻቸው ማቆማቸውን የተናገሩት
ትራምፕ፤ የተባበሩት መንግሥታት ግን "በየትኛውም [ግጭት የማስቆም ጥረት] ውስጥ ለመርዳት እንኳ አልሞከረም" ሲሉ
ተደምጠዋል።
"ኋላ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ለእኛ
እንዳልነበረ ተረዳሁ" ሲሉም በኒውዮርኩ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
ይህ ጉዳይ የተነሳላቸው ጉቴሬዝ፤ የሚመሩት ድርጅት
አባል አገራት በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር ላይ ለተዘረዘሩ ዓለም አቀፍ ሕጎች እንዲገዙ የማድረግ ፈተና እንደገጠመው አምነዋል።
ድርጅቱ ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ግጭቶችን ለመፍታት
"በከፍተኛ ሁኔታ ተሳታፊ" እንደነበረ በአጽንኦት ያነሱት ጉቴሬዝ፤ "ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት የማስገደድ
አቅም የለውም፤ ይልቁንም ትልልቅ ኃያላን አገራት የበለጠ ጠንካራ የማስገደድ አቅም አላቸው" ብለዋል።
ይህ የበለጠ የማስገደድ አቅም ለግጭቶች ትክክለኛ
እና ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማምጣት እየዋለ ነው ወይስ ለጊዜያዊ መፍትሔዎች ብቻ ነው? ሲሉም ጠቅዋል። "በሁለቱ ነገሮች መካከል
ትልቅ ልዩነት አለ" ብለዋል።
አክለውም፤ የመንግሥታቱ ድርጅት 193ቱ አባል
አገራት የሚገጥሟቸውን "ከፍተና ችግሮች እና ተግዳሮቶች" ለመወጣት ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።
ዋና ጸኃፊው፤ "የሕግ የበላይነት በኃይል
የበላይነት መተካት አለበት ብለው የሚያምኑ አሉ" ሲሉም ወቀሳቸውን አሰምተዋል።