ከአሜሪካ እና ኢራን ተኩስ ልውውጥ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ
አሜሪካ እና ኢራን በወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ተኩስ መለዋወጣቸው ከተሰማ በኋላ አርብ ሌሊት የእስያ ገበያ ሲከፈት የነዳጅ ዋጋ ጨምሮ ታየ።
የአሜሪካ ጦር “ትንኮሳ ሳይኖር” የተሰነዘሩ ያላቸውን የኢራን የሚሳዔል፣ ድሮን እና የአነስተኛ ጀልባ ጥቃቶችን ማክሸፉን፤ በምላሹም የራስ መከላከል ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።
ከዚህ ጥቃት በኋላ፤ የዓለም የነዳጅ ዋጋ መለኪያ የሆነው ብሬንት ዋጋው በ1.5 በመቶ ጨምሮ በበርሜል 101.60 ዶላር ተሽጧል። በአሜሪካ ገበያ የሚሸጠው ነዳጅ ደግሞ ዋጋው በ1.1 በመቶ አድጎ 95.87 ዶላር ሆኗል።
በአውስትራሊያ ጀምስ ኩክ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ጂያጂያ ያንግ እንደሚናገሩት፤ የነዳጅ ዋጋ በድጋሚ የጨመረው በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚወሰደው ወታደራዊ እርምጃ በስትራቴጂካዊው የንግድ መስመር የሚጓጓዘው የኤነርጂ አቅርቦትን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል የሚል ስጋት በመጨመሩ ነው።
በሲንጋፖር ናሽናል ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ተመራማሪ የሆኑት ሁይፌንግ ቻንግ በበኩላቸው፤ አሜሪካ እና ኢራን ውጥረቱን ለማርገብ እየሞከሩ ቢሆንም እንኳ ነጋዴዎች ተኩስ አቁሙን “በቀላሉ የሚጣስ” አድርገው ስለሚመለከቱት አካሄዳቸውን በዚያው ልክ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
ከእስራኤል ጋር በመሆን በየካቲት ወር ጦርነት የከፈተችው አሜሪካ፤ ግጭቱን ለመቋጨት ከኢራን ጋር ለምታደርገው ድርድር የሚሆን የስምምነት ማዕቀፍ እያዘጋጀች መሆኑን አስታውቃለች። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጦርነቱ "በፍጥነት ያበቃል" ሲሉ በዚህ ሳምንት ተናግረዋል።
ጥቃት የተከፈተባት ኢራን በአጸፋው ቁልፍ የነዳጅ እና ጋዝ መተላለፊያ የሆነውን ሆርሙዝ ወሽመጥ እንደምትዘጋ ከዛተችበት ከጦርነቱ ጅማሬ አንስቶ የኤነርጂ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። ከዓለም የነዳጅ እና የጋዝ አቅርቦት ውስጥ አንድ አምስተኛው የሚያልፈው በዚህ የባሕር መስመር ነው።